መንግሥቱ ኃ/ማርያም - የኢትዮጵያ አብዮት 50ኛ ዓመት
ሐሙስ፣ መስከረም 2 201750ኛ ዓመት አብዮት፤ መንግሥቱ ኃ/ማርያም በደራሲዉ ብዕር
የቀድሞው የደርግ ሊቀመንበር የኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ከልጅነት አንስቶ ዛሬ እስካሉበት የስደት ዘመን ድረስ የተጓዙባቸውን ግላዊ ታሪኮች፣ የሕይወት ገጠመኞች እና ወቅታዊና ነባር ፖለቲካዊ ግምገማዎችን -አካተዉ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡ የስደተኛው መሪ ትረካዎች በቅርቡ በመጽሐፍ መልክ ለአንባብያን ቀርቧል። የመጽሐፉ አቅራቢ ደራሲ እና ገጣሚ አቶ ይታገሱ ጌትነት መንግሥቱን በአካል አግኝተዋቸዋል። አቶ ይታገሱ ጌትነት ፤አዲስ አበባ የሚገኘዉ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥነ-ጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር ናቸዉ፡፡
በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ሁለተኛው ቀን ልክ በዛሬዋ እለት ፤ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አፄ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አውርዶ ቤተ መንግሥቱን በመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን ያወጀበት እለት።
የቀድሞዉን የደርግ ሊቀመንበር ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያምን በአካል አግኝተዉ ያነጋገሩት አቶ ይታገሱ በሥነ-ግጥሞቻቸዉ በሥነ-ጽሑፎቻቸዉ አድናቆትን ቢያገኙም ቅሉ ”በሕይወቴ ፈጸምኳቸው ከምላቸው በርካታ ቁም ነገሮች ውስጥ ምናልባት ይኽኛው መጽሐፍ ዋንኛና ቀዳሚዉ ይሆናል ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ስለ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡ የስደተኛው መሪ ትረካዎች መጽሐፋቸዉ ተናግረዋል።
ጥሩ አንደበት ትሁት እና አንደበተ ርዕቱዉ ይታገሱ ጌትነት ከቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሊቀመንበር ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጋር ቃለ-ምልልስ ባደረጉ ከአምስት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በኋላ ነዉ በ 328 ገፆች ጠርዘዉ ከሳምንታቶች በፊት ለአንባብያን ያ,ረቡት። መጽሐፍ ተወዶላቸዋል። ብዙዎችም አስተያየት እየሰጡበት ነዉ። አቶ ይታገሱ እንደሚሉት መንግሥቱ የ 83 ዓመት አዛዉንት ናቸዉ። አቶ ይታገሱ የቀድሞ ሊቀመንበር ኮ/ር መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ያገኝዋቸዉ ወደ ሚኖሩበት ወደ በአገረ ዚምቧቤ፤ ተጉዘዉ መኖርያ ቤታቸዉ ቀጠሮ ይዘዉ ነዉ። እንደ አቶ ይታገሱ ቃለ ምልልሳቸዉ ከአንድ ሳምንት በላይ ወስዷል። ደራሲዉ ለአንባብያን ከሽነዉ እስኪያቀርቡትም ጽሑፋቸዉ አራት አምስት ጊዜ ፈርሶ፤ ለህትመት መብቃቱንም ፀሐፊዉ አቶ ይታገሱ ጌትነት አልሸሸጉም። ከአንድ ሳምንት በላይ ወደ ቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሊቀመንበር ኮ/ር መንግሥቱ ኃይለማርያም መኖርያ ቤት እየተመላለሱ ሙሉቀን በሚባል ደረጃ ቃለ-ምልልስ ያደረጉላቸዉ አቶ ይታገሱ፤ በቃለ ምልልሱ ወቅት መንጌን ጋሼ ሲሉ ይጠርዋቸዉ እንደነበር አጫዉተዉናል።
መንጌ ረጋ ያሉ እና ለተጠየቁት በድንብ የሚመልሱ፤ የማስታወስ አቅማቸዉ የሚደነቅ ሲሉ አቶ ይታገሱ ተናግረዋል። ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሚያሳዝን ታሪክን ሲስቡም በቃለ ምልልሱ ወቅት ዓይናቸዉ እንባ ሲያቀር ከፋ ሲላቸዉም አቶ ይታገሱ አይተዋቸዋል። ስለዚህም ይላሉ አቶ ይታገሱ ፤ መጽሐፉ እስከዛሬ ስለ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ያልሰማነዉን ሰዋዊ ገጽታቸዉን በመጽሐፉ ማግኘት ይቻላል።
በ1969 የዚያድባሬ ሠራዊት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የአቶ ይታገሱ አባት የጅግጅጋን ማስለቀቅ ጦርነት ወቅት ካራማራ ላይ ለአገራቸዉ ወድቀዋል። ይህን ተከትሎ ቆየት ብሎ በ 1976 ዓ.ም ልጅ ይታገሱ ጌትነት የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ የኢትዮጵያ ህጻናት አምባን ተቀላቀሉ። ትምህርታቸዉን በጥሩ ዉጤት እስከ የከፍተኛ የትምህርት ደረጃ አጠናቀዋል። ይሁንና አቶ ይታገሱ የዛሬ አምስት ዓመት ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለማርያምን አገረ ዚምባቤ ድረስ ሄደዉ እንዲህ እንዴት በቀላሉ ሊያገኝዋቸዉ ቻሉ? ዘመድ ናችሁ እንዴ ለሚለዉ ጥያቄ አቶ ይታገሱ ሳቅ ብለዉ እንግዲህ እሳቸዉ ባነፁት አገር አአፍ በሆነ መኖርያ ቤት በማደጌ አባት ሊባሉ ይችላሉ ሲሉ መልሰዋል።
መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡ የስደተኛው መሪ ትረካዎች የተሰኘዉን የአቶ ይታገሱን አዲስ መጽሐፍ ያነበቡት ደራሲ ዘነበ ወላ ካጋሩት ረጅም አስተያየት መካከል፤ «መጽሐፉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም፤ በልጅነት ስላያዩት ውጣ ወረድ ይጀምርና ወደ ፖለቲካ ህይወታቸው የዞን ይዘልቃል። እዚህ ዘንድ ቁጭት ፣ ጸጸት እንዲህ ቢሆን ኖሮ ብሎ ማመላከት ባለበት ሁኔታ ትረካው ይዞን ጅውው ይላል ። ደራሲው ጠያቂ አልሆነም አድማጭ ነበር ። አዛውንቱ ፕሬዚዳንት ደግሞ ማለፊያ ተራኪ ነው የነበሩት ።
ይታገሱ ልጃቸው ነው ። እሳቸው የህጻናት አንባን ባይመሰርቱ ደራሲው የአሁኑ ሰብእና ላይኖረው ይችል ይሆናል ። ስለዚህ አባቱ ያወጉትን ነው ይዞልን የመጣው ። እንዲያም ሆኖ የፕሬዝዳንቱ የማስታወስ ችሎታ ይደንቃል ። አልዋሽም፤ ከልጅነት ህይወታቸው ወጥተው ወደ አብዬት ሲዘልቁ ሊመልሳቸው ይገባ ነበር። በሌላ ጎኑ ኮሎኔሉን አግኝቶ እንዴት አብዮቱን ማውሳት እንደዋዛ ችላ ይባላል? (አብዮት ህይወታቸው ነበራ )
ካለባቸው የጤና ችግር አኳያ ልባቸውን እና ዓይናቸውን አሟቸው ነበር ። መጽሐፉ በርካታ አዳዲስ ሃሳብ አግኝቼበታለሁ ። አገሬ እንዲህ ብትሄድ ብለው ወደፊት ያመላከቱትንም ሃሳብ እጋራዋለሁ። ሆስኒ ሙባረክ አገሬን ጎብኝ ብሎ ያስጎበኛቸው የመድፍ ፋብሪካ አስቆኛል። አላማው መንግስቱን ብርድ ብርድ ሲላቸው ለማየት ነበር ። ሙባረክ የተሳሳተው ያስጎበኘው ለወታደር መሆኑን ረስቶታል ።» ሲል ከመጽሐፉ ቆንጠር አድርጎ በአስተያየቱ አስቀምጧል። ደራሲ ይታገሱ ጌትነት መንጌን ቃለ-መጠይቅ ባደረጉበት ወቅት ያሳዘናቸዉ ያስደሰታቸዉ ያስገረማቸዉ ነገር ነበር?» ሲሉ ጽፈዋል።
ይፍቱስራ ምትኩ የተባሉ ሌላዉ የመጽሐፉ አንባቢ በማኅበራዊ መገናኛዎች ካጋሩት የጽሑፍ አስተያየት መካከል፤ «መጽሐፉን ከገለጥኩበት ሰዓት ጀምሮ እኔ እኔን አልነበርኩም:: የመጽሐፉ አዘጋጅ ከምስጋናው ቀጥሎ ባለው አንድ ገፅ ላይ የስራውን መታሰቢያነት እንዲህ ሲል አስፍሯል»ይላሉ።
«ሕይወትህን ለሀገርህ ሰጥተህ ላሳደግኸኝ ለማላውቅህ አባቴ ጌትነት ገበየሁ" ይቀጥላሉ ዘነበ፤ አንቺ ሀገር ሆይ ስንት ስንት ጉድ፣ ስንት ስንት ናፍቆት፣ ስንት ስንት ሰቀቀን ነው እውስጥሽ ያለው ግን? ይሄ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ንግግር የተፃፈበት ቢሆንም... ጥቅል ነገሩ ግን 'መታሰቢያ'ው ላይ አልቋል ለእኔ::
ብቻ ግን ጅማሯቸውም አጨራረሳቸውም ያሳዝናል:: ወደመንበሩ ከመጡበት ጀምሮ እስከተሰደዱበት ድረስ ያወሩልናል:: የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያውቀው ያደረግሁት የለም' ይላሉ:: እሳቸውን እያነበብኩ፤ የኛን ዘመን ማለቴ (ይሄንን ዘመን) አስባለሁ:: እየተደረገ ያለውን፣ 'እያደረግን ነው' የሚሉትን፣ ድርጊቶችን የምንረዳበትንና እየተፈጠረብን ያለውን ስሜት፣ ሞታችንን፣ ሀዘናችንን፣ ሳቃችንን... በወንበሩ ያሉት እንዴት እንደሚረዱት፤ እንዴት እንደሚተነትኑት፣ እንዴት ችግራችንና ችግራቸው አልገጥም እንዳለን...» ይቀጥላል።
መጽሐፉ እየተነበበ፤ እያወያየ እያነጋገረም ነው፤ ይህ መልካም ነው ያሉት አቶ ይታገሱ ጌትነት «ሕሊና ቢስ ዩቲዩበሮች መጽሐፉ ገና ሳምንት ሳይሞላው ዝርፊያ እየሞከሩ ነው፡፡ `የሌብነት ሥራችሁን አቁሙ!` ለማለት እንወዳለን፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሐገር ገዢ የሆነ የቅጂ መብት ድንጋጌ አለና ዋጋው ኪሳራ ይሆንባችኋል፡፡ ለዩቲዩብም በቀጥታ ጥያቄያችንን አስገብተናል፤ ውጤቱን የምናየው ይሆናል፡፡ ንባቡን ሊያበረታታ በሚችል መንገድ ጉልበትና ጊዜያችሁን ብታውሉ ጠቅማችሁ ትጠቀማላችሁ ብለዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚትገኙ ኃላፊነት የሚሰማችሁ አንባብያን የሌቦችን ማንነትና አድራሻ በውስጥ መስመር እንድታሳውቁን አደራ እንላለን፡፡ ተገቢውን አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ሌሎችንም ደራስያን ከሚደርስባቸው አስነዋሪ ዝርፊያ ለመታደግ አቅም ትሆናላችሁ» ብለዋል። መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡ የስደተኛው መሪ ትረካዎች የተሰኘዉ መጽሐፍ በአማዞን ላይ መግዛት እንደሚቻልም አቶ ይታገሱ ጌትነት ተናግረዋል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ