ግጭት ያቆረቆዘው ቱሪዝም
ቅዳሜ፣ መስከረም 11 2017ለቱሪስቶች የስጦታ እቃዎችን በመሸጥ የሚተዳደሩ
መንገሻ ይባላል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብሔራዊ ተብሎ በሚታወቅ አከባቢ የተለያዩ የኢትዮጵያ የባህልና ቅርስ ቁሳቁስ የስጦታ እቃዎችን በመሸጥ ይታወቃል፡፡ በዋናነት የስጦታ ቁሳቁሶቹ ገዢ ደንበኞች ጎብኚዎች መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ይህ የመስከረም ወቅት ደግሞ አልፎ አልፎ እስከ ጥርም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውንም ሆኑ የውጪ ዜጎች በብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጡበትና ገቢያቸውም የሚደራበት ወቅት መሆኑን ካለው የዓመታት የስራው ልምዱ ያስረዳል፡፡ ዘንድሮን ጨምሮ በቅርብ ጊዜያት ግን ይህየቱሪስቶች እንቅስቀሰሴእንደቀነሰ ማስተዋሉን አመልክቷልም፡፡
“በዚህ የተለያዩ የባህል እቃዎች ስላሉ ቱሪስቶች ይመጣሉ ይገዙናል” ያለው መንገሻ አሁን ግን እንደ ወትሮው የቱሪስቶች እንቅስቃሴ እጅጉን መደብዘዙን አስረድቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭት ጦርነቶች የቱሪስቶች ፍሰት ገድቦታል የሚል እምነቱን አስረድቷል፡፡
ሆኖም መንገሻ ነገ የተሻለ ይሆናል በሚል ተስፋው ስራውን እንደሚገፋበት ነው የገለጸው፡፡ “ነገ የተሸለ ሆኖ ኢትዮጵያ እንደ አገር እኛም እንደ ዜጋ ከቱሪስት የሚፈለገው ነገር ይገኛል የሚል ተስፋ አለን” ሲል ሃሳቡን ቋጭቷል፡፡
እንደ ላሊበላ ባሉ የቱሪስት መዳረሻ፤ የተጠቃሚዎች እሮሮ
አማራ ክልል ውስጥ በላሊበላ በአስጎብኚነት ይተዳደሩ የነበሩ አስተያየት ሰጪ በፊናቸው አሁን ላይ በአከባቢው ባለው ግጭት አለመረጋጋቱ ምክንያት በዚህን ወቅት በአከባቢው ይጎርፍ የነበረው ጎብኚ በተለይም የውጪ ጎብኚ በእሱ ግምት ከ90 በመቶ ግድም በላይ አሽቆልቁሏል ነው የሚለው፡፡ ይህም በአከባቢው እያንዳንዱ በቱሪዝም ኢንደስትሪው ይተዳደር የነበረውን ማህበረሰብ እና አስጎብኚዎችን በእጅጉ ፈትኗል ይላል፡፡ “አሁን አስጎብኚ ሁሉ እርዳታ ልመና ላይ ገብቷል” የሚሉት አስጎብኚው አሁን ላይ በቀን ከ5-10 የውጪ ጎብኙ ብቅ ቢል ነው ብሏል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ከዚህ በፊት በዚህን ወቅት ላሊበላን በትንሽ ግምት በቀን 200 የውጪ ጎብኚ ይጎበኝ ነበር፡፡ ከዚሁ ከቱሪዝም ብቻ በሚገኝ ገቢ ይተዳደር የነበረው የአከባቢው ማህበረሰብም አስቸጋሪ ያሉት ህይወት እሪየገፋ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ቱሪዝምን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎችአንዱ ዘርፍ በማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎችን መገንባቱን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ይሁንና በግጭት እየተናደች የምትገኘው ኢትዮጵያ ባሁን ወቅት ለቱሪዝም መዳረሻነት የአቅሟን ያህል ተመራጭ እንዳትሆን በተለያዩ አከባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭት አለመረጋጋቶች ፈተና መሆናቸው ነው የሚነገረው፡፡ ዶቼ ቬለ በዚህ በቱሪዝም መዳረሻ ወራት እንደ አገር ቱሪስት ለመሳብ ስለተደረገው ጥረት እና ተግዳሮቶቹ ላይ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንዲሁም ከተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡
በኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በቱሪዝም ሆስፒታሊቲ በአማካሪነትና በባለሙያነት ያገለገሉት አቶ ፍስሃ አስረስ እንደሚሉት ግን የቱሪዝም እንዳስትሪው በውጭ መንግስታት የሚደረጉ የጉዞ እቀባዎች ቢጎዳም ቱሪዝም በአዎንታዊነት ከተበረታታ አሁንም አማራጮች ይኖሩታል ብለዋል፡፡ “ብዙ ጊዜ አሉታዊ ነገር ካስተዋወቅክ ውጤቱም አሉታዊ ይሆናል” ብለዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር