ግጭት በአማራና በአፋር አጎራባች ቀበሌዎች | ኢትዮጵያ | DW | 23.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ግጭት በአማራና በአፋር አጎራባች ቀበሌዎች

በአማራና በአፋር ክልል በሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች  መካከል  ግጭት መፈጠሩን የአካባቢዉ ነዋሪዎች ገለፁ። በግጭቱ  የሰዉ ህይወት የጠፋ ሲሆን ግጭቱን ለማርገብ  በአጎራባች  ቀበሌዎቹ  መካከል የፌደራል ፖሊስ ሰፍሮ እንደሚገኝ ተገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:04
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:04 ደቂቃ

«በግጭቱ የሰዉ ህይወት ጠፍቷል »


ነዋሪዎች እንደሚሉት በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳና  በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን  በሀብሩ ወረዳ  የሚኖሩ የሁለቱ ብሔረሰብ ተወላጆች በየጊዜዉ ይጋጫሉ። ጉዳዩን ለአካባቢዉ የአስተዳደር አካላት ቢያሳዉቁም  አሁንም ድረስ ችግሩ እልባት  አላገኜም ነዉ የሚሉት።
ባለፈዉ ሰኞም በሀብሩ ወረዳ  ቀበሌ 16፣24 እና 26 በተባሉ አካባቢዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭት መነሳቱን አመልክተዋል።  በግጭቱ ከሁለቱም ወገኖች  የሰዉ ህይወት መጥፋቱን የአካባቢዉ ነዋሪወች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።ተጨማሪ  የንብረትና የህይወት ጉዳት ይደርስብናል የሚል ስጋት እንዳላቸዉም  ነዋሪወቹ ገልፀዋል።
እንደ ነዋሪወቹ ገለፃ የሁለቱ አጎራባች ክልል ነዋሪዎች በሰላም አብረዉ ይኖሩ ነበር።  ካለፈዉ አመት ሀምሌ ወር ጀምሮ ግን በግጭቶቹ የሰዉ ህይወት በመጥፋቱ  ሳቢያ በገበያ ቦታ እንኳን እንደማይገናኙ አስረድተዋል።የግጭቱ መንስኤም የድንበር ጉዳይ ነዉ ይላሉ።
የአፋር ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልሰመድ መሀመድን ለማነጋገር ብንሞክርም በጉዳዩ ላይ መረጃ የለኝም ከማለት ዉጭ ማብራሪያ ሊሰጡን አልቻሉም። በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ልባሴ አሊጋዝ  በበኩላቸዉ  ካለፈዉ ሚያዚያ ወር ጀምሮ ግጭቱ መከሰቱንና የሰዉ ህይወት መጥፋቱን  አምነዉ የግጭቱ መንስኤ  የዉሃና የግጦሽ መሬት ፍለጋ መሆኑን አስረድተዋል።ይህም ቢሆን በተወሰኑ ግለሰቦች የተደረገ ነዉ ብለዋል።


እንደ ሀላፊዉ ችግሩን  ለመፍታት የሁለቱ ክልል አመራሮች ና የሀገር ሽማግሌወች በተደጋጋሚ ዉይይት አድርገዋል።በመጪዉ ነሀሴ 18 ም ሌላ ዙር ዉይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።  አጥፊወቹን  ለማጋለጥና ወደ ህግ ለማቅረብም  የመረማሪ ኮሚቴ መቋቋሙን ይናገራሉ።
ባለፈዉ ሰኞ  የተቀሰቀሰዉን ግጭት ለማረጋጋት  በሁለቱ አጎራባች ወረዳዎች መካከል  የፌደራል ፖሊስ ሰፍሮ እንደሚገኝም ሀላፊዉ ጨምረዉ አመልክተዋል።

ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ማዕቀፉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

 

Audios and videos on the topic