«ግጥም በመሰንቆ» በጎንደር | ባህል | DW | 06.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«ግጥም በመሰንቆ» በጎንደር

«ግጥም በመሰንቆ በጣም ጥሩ ዝግጅት ነዉ አንደኛ ወጣቱ ያለዉን የሥነ-ጽሑፍ ክህሎት እንዲበረታታ፤ በሌላ በኩል ክህሎቱን ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርብ፤ እንዲሁም ልምዱን እንዲለዋወጥ የሚያስችለዉ አይነት አዘገጃጀት ነዉ ያለዉ» በጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት መምህር ጎይቶም ኃይሌ የሰጡ አስተያየት ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:29

«ግጥም በመሰንቆ» በጎንደር

ጎንደር ከተማ ላይ የተጀመረዉ «ግጥም በመሰንቆ» የሥነ-ግጥም ምሽት ወጣት አዋቂዉን በሥነ -ጽሑፍ ገበታ እያሰባሰበ እንደሆነ ተነግሮለታል። ከዚህ ሌላ ከተማይቱ ከሌሎች ከተሞች ይህንኑ የሥነ-ግጥም መድረክ ለመካፈል በሚመጡ ፀሐፍትና የሥነ-ግጥም አድናቂዎች እየተጎበኘች ነዉ። የዚህ ዝግጅት አስተናባሪዎች እንደሚሉት ግጥም በመሰንቆ ዝግጅት የጎንደር ከተማን እሴት ባህልና ወግ ታሪካዊ ዳራዋን ሳይለቅ ለመዘከር፤ ከትዉልድ ትዉልድ ለመቀባበል ነዉ።ግጥም በመሰንቆ ከጥበባዊ ፋይዳዉ በተጨማሪ ከተማችን ከኪነ-ጥበብ ጋር ካላት የጠበቀ ቁርኝት አንጻር የኪነ-ጥበቡን እንቅስቃሴ ለማበረታታት፤ ተተኪ የጥበብ ከያንያንን ለማፍራት የጀመርነዉ የሥነ-ጽሑፍ መድረክ ነዉ ሲሉ ይገልፃሉ ፤ የሥነ-ግጥም መድረኩ አስተባባሪዎችና መስራቾች፤ ወጣት ሀረገወይን ድረስና ትዕግስት ሲሳይ ይባላሉ። ። ግጥም በመሰንቆ ዛሬ ለአስራ ስድስተኛ ጊዜ ተዘጋጅቶል። የመድረኩ አስተናባሪ ወጣት ትዕግስት ሲሳይ መሰንቆ በከተማዋ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠዉ የሙዚቃ መሳርያ በመሆኑና ባህላዊ እሴትም በመሆኑ ከሥነ ግጥም ዝግጅቱ ጋር እንዲቀናበር አደርግን ብላለች።
ሌላዋ የዚህ ፕሮግራም አስተባባሪና መስራች ወጣት ሀረገወይን ድረስ በበኩልዋ ዝግጅታችን በከተማዋ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ በተከታታይነቱም ሆነ የሀገሪቱን ታዋቂ የሥነ-ጽሑፍ ሰዎችን በመጋበዝ የመጀመርያ ነዉ።

ግጥምን ከመሰንቆ ጋር በማዋሀድ የግጥም ምሽትን ማዘጋጀት ገና እየጀመረ ያለ ተወዳጅ አዲስ ስልት ነው፡፡ይህንን ተወዳጅ ባህላዊ እሴቶቻችንን በሚያስተዋውቅ መልኩ የሚዘጋጀውን ዝግጅት እውቅ እና አንጋፋ ጸሐፍት ፣ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሰዎች ከአ.አ ወደ ጎንደር ተጉዘው ጎንደር ከሚገኙ ጸሐፍት ጋር በመቀናጀት የሚሰሩት ነው፡፡


በዚሁ የሥነ ግጥም መድረክ ላይ ፀሐፊ ተዉኔትና ገጣሚ ጌትነት እንየዉ፤ ገጣሚና ሃያሲ አያልነህ ሙላት፤ ጋዜጠኛ ነብይ መኮንን የሥነ-ጽሑፍ ሥራቸዉን ካቀረቡ ታዋቂ ፀሐፍት መካከል ጥቂቶቹ ናቸዉ። በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነዉ ሌላዉ ታዋቂ ገጣሚ አበባዉ መላኩም በዚህ የሥነ- ግጥም መድረክ ላይ ሶስት ጊዜ ተጋባዥ ነበረ ።
መሰንቆ በጎንደር ከተማ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የሙዚቃ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ እሴትም ነው፡፡ በተለይ በመሰንቆ ችሎታቸው አንቱታን ያተረፉ ባለሙያወች የፈለቁባት በመሰንቆአቸው ታጅበው ፈገግ የሚደርጉ ግጥሞችን በማስደመጥ የሚያዝናኑን አዝማሪዎች የሚፈልቁባት ባህላዊ ከያንያንን በማፍራትና በአዝማሪዎቿ የምትታወቀው ጎንደር ከመሰንቆ ጋር ያላት ቁርኝት የጠበቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ግጥም በመሰንቆ ምሽት ላይ የሥነ-ግጥም አፍቃሪዎችን በማሰባሰብ በየወሩ ለመድረክ የሚጋብዙት ሁለቱ ወጣት ሴቶች ዝግጅቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እና ተዘዉታሪ ሆኖላቸዋል። ወጣት ሀረገወይን ዝግጅቱ ባህላዊ መሆኑንም ትገልጻለች። «በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ የጥበብ መናገሻ እንደምሆኗ መጠን የከተማዋን እሴት ባህል እና ወግ ታሪካዊ ዳራውን ሳይለቅ ለመዘከር ከትውልድ ትውልድ ለመቀባብል ኪነ-ጥበብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
ግጥም በመሰንቆ ባህላዊ መሆኑን ከአዲስ አበባ እየተጋበዘ ሥነ-ግጥሞቹን የሚያቀርበዉ ገጣሚ አበባዉ መላኩም ይናገራል።
መምህር ጎይቶም ኃይሌ በጎንደሩ ግጥም በመሰንቆ መድረክ ተከታታይና ተሳታፊና ናቸዉ። ይህ የሥነ-ግጥም መድረክ ወጣቱ በሥነ-ግጥም ያለዉን ዝናባሌ እንዲያዳብር፤ ያለዉንም ለማኅበረሰብ እንዲያቀርብና ልምድም እንዲለዋወጥ የሚረዳ በተለይ ከመድረኩ ወጣቱ ተጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።የጎንደሩን ግጥም በመሰንቆ ፤ በወሎ ላይ የጥበብ ዉሎ በወሎ ፤ ደብረዘይት ላይ ፤ ሆራ ቡላ እንዲሁም የአዲስ አበባዉን ግጥም በጃስ የመሳሰሉ የሥነ-ጽሑፍ የሥነ -ግጥም መድረኮች በተለያዩ ከተማዎች እየተስፋፋ መሆኑን ገጣሚ አበባዉ መላኩ ተናግሯል፤ ወጣቱ ልምዱን እዉቀቱን እየተለዋወጠ መሆኑንም ነዉ የገለፀዉ። በዚሁ ሁለት ወጣት ሴቶች የተመሰረተዉ የጎንደሩን ግጥም በማሲንቆ ድጋፍ የበለጠ እንዲያብብ የሥነ-ጽሑፍ ፍቅር እንዲጎለብት ድጋፍ የሚሰጡትን በማመስገን፤ ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ቅንብሩን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic