ግዕዝ አለ ወይስ ሞቷል? | ባህል | DW | 02.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ግዕዝ አለ ወይስ ሞቷል?

በዓለም ከ7000 በላይ ቋንቋዎች በመግባቢያነት እንደሚያገለግሉ ይነገራል። በዓለም ላይ ከሚገኙ ቋንቋዎች 6 በመቶው የሚሆኑትን 94 በመቶ የዓለም ህዝብ በመግባቢያነት ይጠቀምባቸዋል። የቀሪዎቹ 94 በመቶ ቋንቋዎች ተናጋሪ ግን ከዓለም ህዝብ 6 በመቶ ብቻ መሆኑን ኢትኖሎግ የተሰኘው የዓለም ቋንቋዎች የጥናት ዘገባ ይፋ አድርጓል።

ዛሬ ግዕዝ በኢትዮጵያና ኤርትራ አብያተ ክርስቲያናት የምስጋናና የጸሎት ቋንቋ ነው።ግዕዝ የጥናትና ምርምርም ቋንቋ ነው። ከመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የሥነጽሁፍ ቋንቋ ሆኖ ለ2ሺ ዓመታት እንዳገለገለ ይነገራል። የወቅቱን የታሪክ፤ነገረ ሃይማኖት፤ሥርዓት፤ህግ፤ፍልስፍና፤ወግ፤ስነግጥም፤ሙዚቃ፤የቀን አቆጣጠር እና መዝገበ ቃላት ተጽፈው የሚገኙት በዚሁ የግዕዝ ቋንቋ በመሆኑ ምሁራን ሊጠና እና ሊመረመር ይገባል የሚል አቋም አላቸው። ይሁንና ዛሬ ግዕዝ በቤተ-አምልኮዎችና ውስን የትምህርት ተቋማት በሚሰጠው ግልጋሎት ያለፈ ተወስኗል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ልሳንና ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ «የአፍ መፍቻን እንደ መመዘኛ ካየንው እሳኩን የግዕዝ ሊቃውንት እንጂ አፋቸውን በግዕዝ ብቻ የሚግባቡ ህዝቦች ማግኘት አስቸጋሪ ነው።» ሲሉ የግዕዝ ቋንቋ ያለበትን ሁኔታ ያስረዳሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር በስነ-ልሳን ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩምም «ቋንቋን በተመለከተ አለ ወይም የለም የሚለውን ነገር የሥነ-ልሳን ባለሙያዎች ሲተነትኑ አንድ ቋንቋ በአፍ መፍቻ የሚናገረው ሰው ከሌለ፤ ጥቅም ላይ መዋሉ ካቆመ በዛ ቋንቋ የተጻፉ ጽሁፎች ብቻ ከሆነ ያሉት ያ ቋንቋ ሞቷል እንደገና ህያው ለማድረግ ስራ መስራት ይጠይቃል ይላሉ።» ሲሉ ይናገራሉ።

ቋንቋው አፉን የሚፈታበት ማህበረሰብ የለውም።በለት ተለት የኑሮ እንቅስቃሴ ውስጥም አገልግሎት አይሰጥም።ግዕዝ የትምህርት፤ የአገልግሎትና የሥነ-ጽሁፍ ቋንቋ ሆኖ አገልግሏል። እነዚህ አገልግሎቶቹ በአብያተ-ክርስቲያናት ብቻ ቢወሰንም አሁንም ግን አሉ። ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ «መምህራን ከተማሪዎቻቸው እና ከደቀመዛሙርቶቻቸው ጋር የሚግባቡበት የሚነጋገሩበትም ቋንቋ ስለሆነ» አልሞተም ሲሉ ይናገራሉ። በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናት ትምህርታቸውን በዚሁ ቋንቋ በመጀመራቸው ካደጉም በኋላ ለቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቀሙበት ሊቃውንት አሉ የሚሉት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም «ጽሁፉም መጽሃፍም ይታተምበታል፤መልዕክት ይተላለፍበታል፤ትምህርት ይሰጥበታል። በመሆኑም በየቀኑ አገልግሎት ላይ ስላለ በሥነ-ልሳኑ አተረጓጎም በቃ ሞቷል ለማለት ይከብዳል።» ሲሉ ይናገራሉ።

ግዕዝ እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ዋነኛ የመግባቢያና የቤተ-መንግስት ቋንቋ እንደነበር የሚጠቁሙ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች ይገኛሉ።ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አሁን ኤርትራ በሚባለው አካባቢና ሰሜን ኢትዮጵያ ለትግሪኛ ቦታውን ሲለቅ በማዕከላዊው አካባቢ ደግሞ በአማርኛ ቋንቋ ተተክቷል።

የግዕዝ ቋንቋ ምንጭ ዛሬም ድረስ አከራካሪ ነው። ከሳባ እና የደቡብ አረቢያ ቋንቋዎች ወደ አፍሪቃ ተስፋፋ የሚሉ መላምቶች የነበሩ ቢሆንም ተቀባይነት አጥተዋል። አማርኛና ትግሪኛን የመሳሰሉ ቋንቋዎች ዛሬ የሚጠቀሙባቸውን ፊደላት ለጽህፈት አገልግሎት በመጠቀም ቀዳሚው ነው። የግዕዝ ሥነጽሁፍ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ይዘት አለው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር በስነ-ልሳን ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም የግዕዝ ቋንቋና በግዕዝ የተጻፉ ጥንታዊ ጽሁፎች ጥናት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ።

የግዕዝ ቋንቋ የሴማዊ ቋንቋዎች ጥናት አንዱ ክፍል ነው። ሰሜናዊ ኢትዮ-ሴሜቲክ በሚባለው የቋንቋ አከፋፈል ውስጥ ትግሪኛ፤ትግረና ግዕዝ የጋራ ባህሪ፤ታሪካዊ ዳራ፤የሚመሳሰል የቋንቋ ተናጋሪ አላቸው። አሁን ህልውናው አብያተ-ክርስቲያናት እና የትምህርት ተቋማት ብቻ የተወሰነው ግዕዝን ማጥናት ትግሪኛና አማርኛን ለመሳሰሉ የኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች ከፍ ያለ ግልጋሎት እንደሚያበረክት ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሁለተኛው የግዕዝ አገር አቀፍ ጉባኤ ባለፉት ቀናት በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ ከርሟል። ግዕዝን ማዕከል ያደረገው ጉባኤ ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ይደረግ የነበረ ሲሆን አገራዊ ፋይዳውን ታሳቢ በማድረግ በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነልሳን ትምህርት ክፍል ጋር መተባበር ለሁለተኛ ጊዜ መዘጋጀቱ ተሰምቷል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴት ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ አውላቸው ሹመካ ግዕዝን በማጥናት በጥንታዊ ጽሁፎች ውስጥ ያሉ እውቀቶችን ለማሸጋገር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic