ግንቦት 15 ቀን፣ 2008 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 23.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ግንቦት 15 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች እግር ኳስ ተጫዋቾች በሚሰለፉበት የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ የጋና አቻውን ያሸነፈው የኢትዮጵያ ቡድን አሠልጣኝ ድክመት ጥንካሬያቸውን አካፍለውናል። አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በግሬት ማንቸስተር የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ፉክክር አሸናፊ ከሆነ በኋላ ቅሬታውን ገልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:20

የስፖርት ዘገባ

የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ አሸናፊ የሆነው ማንቸስተር ዩናይትድ ድሉን ከተጎናጸፈ ከሁለት ቀናት በኋላ አሠልጣኙን እና ረዳቶቻቸውን ማሰናበቱ ታውቋል። የጀርመን የእግር ኳስ ማኅበረሰብን ዋንጫ በእጁ ያስገባው የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝም ከቡድኑ ጋር የነበራቸው የመጨረሻ ቆይታ ትናንት አክትሟል።

እድሜያቸው ከ20 በታች ተጨዋቾችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የዙር ጨዋታ ትናንት አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ከጋና አቻው ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል። የቡድኑ አሠልጣኝ ግርማ ሀብተ-ዮሐንስን ዛሬ በስልክ አነጋግረናቸዋል። በኢትዮጵያ ብዙም ልምድ የሌለው ቡድናቸው ጠንካራ እና ዓለም አቀፍ ልምድ ያካበተውን የጋና ቡድን በማሸነፉ ውጤቱ አበረታች እንደሆነ በመግለጥ የቡድኑ ጥንካሬ እና ድክመትን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡድን የዛሬ ዐሥራ አምስት ቀን የመልስ ጨዋታውን ጋና ውስጥ ያከናውናል። እድሜያቸው ከ20 በታች ተጨዋቾችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ጋናን ጥሎ ወደ ቀጣዩ ዙር ካለፈ የቱኒዝያ እና የሴንጋል አሸናፊን ይገጥማል። ያንንም በድል ካጠናቀቀ ዛምቢያ ውስጥ የሚኪያሄደው ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናል። የአፍሪቃ ሰባት ምርጥ ቡድኖች ከየካቲት 19 ቀን 2009 ዓም እስከ መጋቢት 3 ቀን 2009 ዓም የሚኪያሄደው ውድድር ላይ ለመሳተፍ አዘጋጇ ዛምቢያን ይቀላቀላሉ። የፍጻሜው ምርጥ አራት ቡድኖች በዛው ዓመት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በሚከናወነው የፊፋ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የዓለም እግር ኳስ ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ። ባለፈው የአፍሪቃ ዋንጫ ሦስተኛ ሆኖ የጨረሰው የጋና ቡድን በዓለም ዋንጫ ውድድሩ ኒውዚላንድ ውስጥ ተሳታፊ ነበር። በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫ ለ7 ጊዜያት ተሳትፎ አንድ ጊዜ ዋንጫ አሸንፏል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎችአትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በግሬት ማንችስተር የ10 ኪ.ሜ. ውድድር ትናንት አሸናፊ ሆነዋል። የሦስት ጊዜ የኦሎምፒክ አሸናፊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን በአንደኛነት ካጠናቀቀ በኋላ በሮይተርስ የዜና ምንጭ ለቀረበለት ጥያቄ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምርጫ ቅሬታ እንዳደረበት ገልጧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ቀነኒሳን ተጠባባቂ በማድረጉ አትሌቱ ደስተኛ አለመሆኑን ተናግሯል። «በማራቶን ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ከእኔ አይሻልም» ብሏል ሲልም የዜና ምንጩ ዘግቧል። በምርጫው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከየማነ ጸጋዬ እና ከሌሊሳ ዲሣሳ ጋር ተጠባባቂ ሆኖ መመረጡ ቀደም ሲል ተነግሯል። የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የኢትዮጵያ ዜና ዘጋቢ ኤልሻዳይ ነጋሽ ምርጫውን እና የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ቅሬታን በተመለከተ የሚከተለውን ትንታኔ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ31ኛው የሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር የመምረጫ መስፈርቶች በሚል መግለጫ አውጥቷል። በተለያዩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ፣ በፌዴሬሽኑ ማኅበራዊ ገፅ /ፌስ ቡክ/ ላይ መስፈርቶቹ በግልፅ እንዲታዩ ማድረጉን ገልጧል። አዲስ የወጣው መስፈርት በከፊል ሲቃኝ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ላይ የተገኘ የተሻለ ደረጃና ሰዓት፤ በወጥነት የተመዘገበ ውጤት፤ ከመስከረም ወር አንስቶ እስከ ሚያዝያ የተገኘ ውጤት ዋጋ እንደሚሰጠው ሰፍሯል። ከጥር እስከ ሚያዝያም ቢበዛ ሦስት ተከታታይ ማራቶን በመሮጥ ሦስት ወራት የማገገሚያ ጊዜን መጠበቅ የሚልም ይገኝበታል።

አትሌት አልማዝ አያና

አትሌት አልማዝ አያና

ትናንትና በሞሮኮ መዲና ራባት እና በኔዘርላንድ ሔንጌሎ በተደረጉ የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ርቀቶች አሸናፊ ሆነዋል። በራባቱ የ5000 ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክር አልማዝ አያና አንደኛ ስትወጣ፤ ክብር-ወሰን ለማሻሻል ያደረገችው ጥረት ደህና አሯሯጭ ባለማግኘቷ እንዳልተሳካ ተናግራለች። የኬንያዋ ቪዮላ ዬላጋት ኪቢዎት ሁለተኛ፤ ሰንበሬ ተፈሪ ደግሞ ሦስተኛ ወጥታለች። በ3000 ሜትር የመሰናክል ሩጫም እቴነሽ ዲሮ አንደኛ ወጥታለች። በሔንጌሎ የወንዶች የ5000 ሜትር ፉክክር ደጀን ገብረመስቀል በአንደኛነት አጠናቋል። የኤርትራው አብራር ዖስማን ሁለተኛ፣ የኬንያው ቤትወል ቢርገን ሦስተኛ ሆነዋል። በሴቶች የ5000 ሜትር ለተሰንበት ግደይ፤ በ1500 ሜትር ፉክክር ደግሞ በሱ ሳዶ የአንደኛነትን ድል ተጎናጽፈዋል።

የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ እግር ኳስ ቡድን ቅዳሜ እለት ከክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 በመርታት የኤፍ ኤ ካፕን ለ12ኛ ጊዜ በማሸነፍ ወስዷል። ቡድኑ በድረ-ገጹ ባሰፈረው ማብራሪያ መሠረት በዚህ ውጤት የሚስተካከለው አርሰናል ብቻ እንደሆነ ገልጧል። ከአንድ ክፍለ-ዘመን በፊት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1890 ዓመት በኒውተን ሔልዝ መሪነት ያገኘው የዋንጫ ድል ትናንት በአሠልጣኝ ሉዊ ቫንጋል ዘመን 12ኛው ሆኖ ተመዝግቦለታል። አሠልጣኝ ሉዊ ቫንጋል በማንቸስተር የሁለት ዓመት ዘመናቸው ያገኙት የመጀመሪያ ዋንጫ ቢሆንም ቡድኑን በፕሬሚየር ሊግ ደህና ደረጃ አላደረሱም በሚል ከነረዳቶቻቸው ተሰናብተዋል።

የ53 ዓመቱ የፖርቹጋል ዜጋ ሆላንዳዊውን ተክተው ቡድኑን ይይዛሉ ተብሏል። እሳቸውም ቢሆኑ ግን ቀደም ሲል ያሰለጥኑት የነበረውን የቸልሲ ቡድን ውጤት በማሽቆልቆል ነበር የተሰናበቱት። በእርግጥም ያኔ 16 ጨዋታዎችን ተሸንፈው 15 ነጥብ በመያዝ በደረጃ ሠንጠረዡ 16ኛ ደረጃ ላይ ሲሰፍሩ ቸልሲዎች ብዙም ሊታገሷቸው አልቻሉም። የውል ዘመናቸው ሳያከትም ተሰናበቱ። በማንቸስተር ዩናይድ ቆይታቸውስ ምን ይፈጠር ይሆን?

ከማንቸስተር ዩናይትድ ተሰናባቹ አሠልጣኝ ሉዊ ቫንጋል

ከማንቸስተር ዩናይትድ ተሰናባቹ አሠልጣኝ ሉዊ ቫንጋል

ዘንድሮ በጀርመን የእግር ኳስ ማኅበር የዋንጫ ፍልሚያ ባየር ሙይንሽን ቦሩስያ ዶርትሙንድን 4 ለ3 በማሸነፍ ዋንጫውን በድጋሚ ወስዷል። መደበኛውም ጭማሪውም የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ማለትም 120 ደቂቃው ተጠናቆ በተደረገው የመለያ ፍጽም ቅጣት ምት ነው ለድል የበቃው። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ስቬን ቤንደር አልፈስፍሶ የላካት ኳስ በቀላሉ ተይዛለች። ሶቅራጥስ ከግቡ አግዳሚ በስተግራ ጠርዝ በኩል ወደ ውጪ በመላክ ሲስት፤ ለባየር ሙይንሽን ወሳኟን ግብ ያስቆጠረው ዶግላስ ኮስታ ነው።

የጀርመን የእግር ኳስ ማኅበር የእግር ኳስ ውድድር 64 ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው። ተሳታፊዎቹም ከቡንደስሊጋው እስከታች ሊጎች ድረስ ያሉ ቡድኖች ናቸው። ከአንደኛ እና ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ከእያንዳንዳቸው 18 በአጠቃላይ 36 ቡድኖች በቀጥታ ተሳታፊ ይሆናሉ። ከሦስተኛ ዲቪዚዮን በውድድር ዘመኑ ከአንደኛ እስከ አራተኛ የወጡ ቡድኖችም የመሳተፉ ዕድል አላቸው። የተቀረው 21 ቦታ ከጀርመን በሀገር-አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ የሊግ ውድድሮች ዋንጫ ላሸነፉ ቡድኖች ይሰጣል። ቀሪው ሦስት ደግሞ ከጠቅላላ ውድድሮች ጥሩ ሆነው ለጨረሱ የሚሰጥ ነው።

በፍጹም ቅጣት ምት የተጠናቀቀውን የጀርመን የእግር ኳስ ማኅበር የፍፃሜ ጨዋታ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ ለማየት የተገደደው የባየር ምሽይንሽኑ አጥቂ ማሪዮ ጎይትስ በብሔራዊ ቡድኑ መታቀፉ ተገልጧል። ማሪዮ ጎይትስ በፍጻሜው ፍልሚያ መሰለፍ ያልቻለው አንድ የጎድን አጥንቱ በመሰበሯ ነው።

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫ

የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ከ16 ዓመታት በፊት የአውሮጳ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1998 ደግሞ ከቡድኑ ጋር በመሆን የዓለም ዋንጫን መጨበጥ ችሏል ቲዬሪ ኦንሪ። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን በተመለከተ ተጠይቆ ሲናገር ወሳኝ አጥቂ ይጎድለዋል ብሏል።

«በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ጠንካራ ከነበረው የጀርመን ቡድን ዘንድሮ በርካቶች ብዙ ይጠብቃሉ። ሰዉ ፈረንሣይ የሚከናወነውን የአውሮጳ ዋንጫ መውሰድ ይፈልጋል። ቢያንስ የግማሽ ፍፃሜ ውስጥ መግባት፤ ግን ደግሞ በዋናነት ለፍጻሜ መድረሱን ይሻል። እኔ እንደሚመስለኝ ግን የጀርመን ቡድን አሁን ባለበት ይዘቱ አንድ ወሳኝ ነገር ይጎድለዋል። ሁሌም ቢያንስ አንድ ጠንካራ አጥቂ ይዞ ብቅ የሚለው የጀርመን ቡድን ዘንድሮ ያ ይጎድለዋል።

አሠልጣኝ ዮአሂም ሎይቭ አጥቂው ማሪዮ ጎሜዝን ወደ ቡድኑ አምጥቶታል። በተወሰኑ የማጣሪያ ጨዋታዎች እንዳየነውም ከሆነ ቡድኑ ጥሩ ኳስ ይቆጣጠራል፤ ወደ ግብ ጥሩ ያቀናል፤ ሆኖም ግን ግብ ለማስቆጠር እጅግ ሲቸገሩ ታይተዋል። በእርግጥ አንዳንድ ቡድኖችን በብዙ የግብ ልዩነት 5 ለ3 አለያም 5 ለ2 ሲያሸንፉ አይተናል። ያም ሆኖ አንድ ጠንካራ አጥቂ ያስፈልጋቸዋል ባይ ነኝ። ምናልባት ማሪዮ ጎሜዝ ሊሆን ይችላል ወይንም ደግሞ የሆነ ሌላ አንድ ተጨዋች» ሲል ተናግሯል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ለልምምድ በነገው እለት ወደ ስዊዘርላንድ እንደሚያቀና ተገልጧል።

በስፔን ኮፓ ዴል ሬይ ፍፃሜ ውድድር በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ባርሴሎና ትናንት ሴቪላን 2 ለ0 አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል። ማሼራኖ በ36ኛው ደቂቃ ላይ ተጨዋች ጎትቶ በቀይ በመውጣቱ ነበር ባርሴሎና በ10 ተጨዋቾች ለመጫወት የተገደደው። ሴቪላም ባለቀ ሰአት ሁለት ተጨዋቾችን ለቀይ ካርድ ገብሮ ያጠናቀቀው በ9 ተጨዋቾች ነበር። ባርሴሎና ትናት የወሰደውን ጨምሮ በኮፓ ዴል ሬይ 28 ዋንጫዎችን መሰብሰብ ችሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ


Audios and videos on the topic