ግብፅ የህገ-መንግስት ህዝበ ውሳኔ | አፍሪቃ | DW | 23.12.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ግብፅ የህገ-መንግስት ህዝበ ውሳኔ

ግብፅ ውስጥ አጨቃጫቂውን ህገ-መንግስት ለማፅደቅ ትናት በተከናወነው ሕዝበ-ውሳኔ መሰረት የቅድሚያ ውጤቶች ህገ መንግስቱን አብዛኛው መራጭ እንደተቀበለው ማመላከታቸው ተዘገበ።

የቅዳሜዉ ምርጫ ግብፅ ውስጥ በሚገኙ 17 አውራጃዎች ላይ የተከናወነ ሲሆን በርካታ መራጭ ሕዝብ ወጥቶ እንደነበረም ተጠቅሷል። የምርጫው ጣቢያዎች ከምሽቱ አንድ ሠዓት ላይ መዘጋት የነበረባቸው ቢሆንም ባለስልጣናቱ ምርጫው እስከ ምሽቱ አራት ሠዓት ድረስ እንዲዘልቅ ማድረጋቸውም ተነግሯል። በሁለተኛው እና በመጨረሻው ዙር ምርጫ ረቂቅ ህገመንግስቱን ከ70 በመቶ በላይ መራጩ ሕዝብ እንደተቀበለው የቅድሚያ ውጤቶች አመላክተዋል። የሀገሪቱ እስላም ወንድማማችነት ፓርቲ ይህን የቅድሚያ ውጤት በድረ-ገፁ ላይ እንደለጠፈው ተዘግቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት የምርጫ ጣቢያዎች ከመዘጋታቸው አራት ሠዓታት ቀደም ብሎ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ስልጣን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። ይፋዊው የምርጫ ውጤቱ ሲገለፅ አብላጫው መራጭ ለረቂቅ ሕገመንግስቱ ይሁንታውን ከገለፀ አዲሱ ህገ መንግስት የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታን እስከወዲያኛው እንደሚያስወግድ ታውቋል። ስልጣን የለቀቁት የግብጽ ምክትል ፕሪዚደንት ባለፈዉ ህዳር ወር ስልጣን መልቀቅ ፈልገዉ እንደነበር እና በአገሪቱ ባለዉ አለመረጋጋት፤ እንዲሁም በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በታየዉ ግጭት ምክንያት ማራዘማቸዉን የመንግስቱ ቴሌቭዝን ጨምሮ ዘግቦአል።

ከእስላም ወንድማማቾች ፓርቲ የመጡት ፕሪዝዳንት ሙርሲ መራጩ ህዝብ የሕገ-መንግሥት ረቂቁን እዲደግፍ መጠየቃቸዉ ተዘግቦ ነበር። የነፃ ተቃዋሚዉ ፓርቲ በበኩሉ የሕገ-መንግሥትረቂቁን አልተቀበለዉም። በግብፅ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ከሚኖረዉ ሕዝብ ይልቅ በአነስተኛ ከተሞች አና በገጠር የሚኖረዉ ነዋሪ የእስላም ወንድማማቾች ፓርቲን እንደሚደግፍ ይገመታል። ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ በተደረገዉ የመጀመርያ ዙር የሕዝብ ድምፅ አሰጣጥ ዉጤት 57 በመቶዉ ሕዝብ የሕገ-መንግስቱን ረቂቅ ደግፎአል። የተቃዋሚዉ ፓርቲ በበኩሉ የስላም ወንድማማች ፓርቲ የድምፅ አሰጣጡ ላይ አጭበርብሮአል ሲል ከስዋል። ግብፅ ዉስጥ ትናንት በተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግጭት ከ30 በላይ ሰዎች መጎዳታቸዉ ነዉ የታወቀዉ። ዛሪ በተደረገዉ ሕዝበ-ውሣኔ አሰጣጥ ላይ 130 ሽህ የጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች በ120 ሽ ወታደሮች በመደገፍ ለፀጥታ ተሰማርተዉ እንደነበር ተመልክቶአል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 • ቀን 23.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17865
 • ቀን 23.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17865