ግብፅን ያስደነገጠዉ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ | አፍሪቃ | DW | 09.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ግብፅን ያስደነገጠዉ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ

የግብፅ መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሬ አደረገ። የሀገሪቱ የዜና አገልግሎት አል- አህራም እንደዘገበው ግብፃዉያን ከዛሬ ጀምሮ በየነዳጅ ማድያው ከ40 እስከ 80 በመቶ ጭማሪ ገንዘብ በማዉጣት ነዳጅ ይሸምታሉ።

በነዳጅ ላይ የተደረገዉን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ፤ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢብራሂም ሜህሌብ ፤ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ አድርጎ ለህዝቡ በሚያቀርባቸው በሌሎች መሰረታዊ ነገሮች ላይ ግን የዋጋ ጭማሬ እንደማይደረግ አሳስበዋል። የግብፅ አንድ ሶስተኛ የመንግሥት ባጀት ለምግብ እና ለነዳጅ ድጎማ እንደሚዉል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያትታል።

በሌላ በኩል የግብፅ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት መሃመድ ሙርሲ ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ ብይን አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ የሙሥሊም ወንድማማችነት ማኅበር ዋና ተጠሪ ሞሃመድ ባዴ እና ሌሎች ሰላሳ ስድስት የማኅበሩ አባላት ላይ ዛሪ እድሜ ይፍታህ ፍርድ አስተላልፎዋል። ባለፈዉ ሚያዝያ ወር በግብፅ የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት፤ ባዴና ሌሎች 183 አክራሪ ሙስሊሞች ላይ የሞት ቅጣት ብይን አስተላልፎ እንደነበር ይታወሳል።

የቀድሞው የግብፅ ጦር ዋና አዛዥና፤ አዲሱ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ፤ ከአረብ የፀደይ አብዮት ሶስት ዓመት በኋላ እና፤ የረዥም ዓመታት የሀገሪቱ መሪ ከሆስኒ ሙባረክ በኋላ፤ ዳግም ከግብፅ ጦር በመሪነት ሲሰየም አል ሲሲ የመጀመሪያው ናቸው። በግንቦት ወር በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አል ሲሲ 97 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል። አዲሱ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በሀገሪቱ መረጋጋት አስፍነው እንደ ወትሮው የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቱ ይመጣሉ ብለው በርካታ ግብፃዊያን ተስፋ ያደርጋሉ። ተንታኞች ግን እንደሚሉት ዳግም በሀገሪቱ ብጥብጥ እንዳይነሳ ያሰጋል። ይህም ከአንድ ዓመት በፊት የቀድሞው ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ከስልጣን እንዲወርዱ አል ሲሲ ሚና በመጫወታቸው ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከ40 000 በላይ የተቃውሞ ሰልፈኞች ታስረዋል።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ