ግብፅና የተቃውሞው ግለት፣ | አፍሪቃ | DW | 01.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ግብፅና የተቃውሞው ግለት፣

የቀድሞው የግብፅ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ሆስኒ ሙባረክ፤ በየካቲት ወር 2003 ዓ ም ፤ ሦስት ሳምንት ገደማ በተካሄደ ብርቱ ህዝባዊ አመጽ፣ ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲህ፤ በካይሮና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች፣ ትናንት እጅግ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ

 ያሳተፈ ድብልቅልቅ ያለ አስጨናቂ  ሰልፍ  ተካሄደ።  ሰልፈኞቹ፣ ዛሬ ጧት፣ በካይሮ የሚገኘውን የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር  ፓርቲን ዋና ጽ/ቤት መመዝበራቸውም ታውቋል። ቢያንስ 5 የተቃውሞ ሰልፈኞች መገደላቸውን ራሳቸው ተቃዋሚዎቹ ገልጸዋል።

የግብፅ  ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሙስሊሞች ወንድማማች ማኅበር፣ ዋና ማዕከል፤ ካይሮ ውስጥ ትናንት በተቃውሞ ሰልፈኞች ድንጋይና ቤንዚን በተሞላ ጠርሙስ  ውርወራ ጥቃት የተሠነዘረበት ሲሆን፤ጽ/ቤቱ ምዝበራም ተካሂዶበታል። የዚሁ እስላማዊ  ንቅናቄ ቃል አቀባይ ፣ ጌሃድ ኧል ሃዳድ፣ ታጣቂዎች ጽ/ቤቱን እስከመመዝበር ርቀው መሄዳቸው፣ በቸልታ ሊታለፍ የማይገባው ነው፤ እናም ከእንግዲህ ዲስፕሊን አለው ያሉት ድርጅታቸው አጸፋውን እንደሚወስድ ነው የዛቱት።

ሰልፈኞቹ፣  በበኩላቸው ፣ ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ ከሥልጣን እንዲወርዱ እስከ ነገ ከቀትር በኋላ የ 24 ሰዓት ጊዜ ሰጥተናል ከማለታቸውም ፤ ይህ ተፈጻሚ ባይሆን፤ ህዝባዊው አመጽ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸው ተጠቅሷል።

የቀድሞው አምባገነነ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ከተነሡ በኋላ ፣ ያኔ  ለለውጥ  ተነሣስቶ የነበረው ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍል፤ ተቃውሞውን ያረገበ ቢመስልም 2 ዓመት ከመፈንቅ ገደማ  ሲብላላ የቆየው  ውዝግብ፤ከደሞኑ  አገርሽቶ ቀጥሏል። በካይሮው ታዋቂ አደባባይ ፤  በታህሪር (ነጻነት) አደባባይ በመገኘት አያሌ ህዝብ ለሰልፍ በመውጣቱ ምን እንደተሰማቸው ከገለጡት መካከል፤ የመጀመሪያ ስሙን ብቻ አዴል ብሎ ያስተዋውቀው ግብጻዊ ወጣት ይገኝበታል።

«ደስ ብሎኛል። በአንድ በኩል!በሌላም በኩል፤ አሳስቦኛል። በጣም የተደስትኩበት  ጉዳይ ምክንያቱ፤ ግብጻውያን የማይፈልጉትን ነገር ዝም ብለው ማሳለፍ እንደማይፈልጉ ኣሳይተዋልና! ለዚህም፣ ትናንት፣ ሰኔ 23 ቀን 2005 የሆነው ምሥክር ነው።

በጣም አሳሳቢ አድርጌ የማየው፤ አንዳንድ ግጭቶች መከሠታቸው--ከሙስሊም ወንድማማች  ማኅበር  ደጋፊዎች ጋር በተደረገ ግብግብ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ጉዳይ ነው። የተቃውሞ ሰልፉ ዓላማ በመሠረቱ፣ ማድረግም ያለብን፣ የኃይል እርምጃ የተቀላቀለበትን ሁከት መግታት ነው። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ፣  የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር አባላት ፣  የብዙኀን ድጋፍ እንድሌላቸው አምነው ሲቀበሉ ነው። »

የፕሬዚዳንት ሙርሲ ደጋፊዎች፤ ርእሰ-ብሔሩ ከቀድሞው በብልሹ አሠራር ከታወቀው አገዛዝ   የወረሱአቸው ችግሮች አሉና እ ጎ አ እስከ 2016 የአገልግሎት ዘመናቸውን እስኪያገባድዱ ጊዜ ይሰጣቸው፤ አለበለዚያ መፈንቅለ-መንግሥት እንደማካሄድ  ነው የሚቆጠረው ባዮች ናቸው። ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ፤ ሙርሲ የህዝባዊውን አመጽ ወይም አብዮት ዓላማ በመካድም ሆነ ችላ በማለት፣  ሥልጣን በሙስሊም ወንድማማች ማኅበር እንዲጠቃለል በመጣር ላይ ናቸው፤ ኤኮኖሚውም ተንኮታኩቷል በማለት ብርቱ ወቀሣ ይሠነዝሩባቸዋል።

በመሃሉ ፣ በዛሬው ዕለት 4 ግብጻውያን ሚንስትሮች፤ የቱሪዝም ሚንስትር፣  ሂሻም ዛዙ፣ የመገኛኛና የመረጃ ሥነ ቴክኒክ ጉዳይ ሚንስትር አቴፍ ሄልሚ፣ የህግና የፓርላማ ጉዳይ ሚንስትር ደኤታ፣  ሐተም ባጋቶና  የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ፣ ሚንስትር ደኤታ ኻሌድ አብደል ኧል ፣  በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን  መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ፤ ለጠ/ሚንስትር ሂሻም ቐንዲል አቅርበዋል።

«ታማሮድ» አመጽ ወይም አብዮት እንደማለት ነው በዐረብኛ ፣--- በዚህ ስያሜ የሚታወቀው ነቅናቄ፣ በሙርሲ አስተዳደር ላይ አመኔታ የማያሳድሩ ፣  ከ 22 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ግብጻውዮንን ፊርማ ያሰባሰበ ሲሆን ፣ ፕሬዚዳንቱ ይወረዱ ነው የሚለው።

በዐረብኛ ፣ «ኢራሃል!»(ዞር ይበሉ ፣ ይጥፉ ወይም ከሥልጣን ይውረዱ እንደማለት ነው)ይህን መፈክር ያነገቡ በታህሪር አደባባይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሰልፈኞች፤ በዚያው ድንኳን ተክለው ሌሊቱን ያሳለፉ ሲሆን፤ ከ2 ዓመት ከመንፈቅ በፊት እንደታየው ሁሉ ፣ በሰሞኑ ሰልፍም፣ ሴቶች ጉልህ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ መቅረቡ ተመልክቷል። በሌላ በኩል፤ ከሰልፈኞቹ መካከል፣ ሴቶችን ለመጠበቅ በግል ተነሣሽነት የተሠማሩ መኖራቸው ተመልክቷል። አሁንም ከታህሪር አደባባይ-- አዴል---

«አደባባይ ያገኘኋትን አንዲት ሴትዮ አነጋግሬ ነበር። ሴቶች፤ እንዳይጎዱ የሚጠብቁ ፣ በራሳቸው ተነሣሽነት የተሠማሩ ወንዶች አሉ። ወደ ታህሪር አደባባይ ለመሄድ ማንም መፍራት የለበትም። ዛሬ ጧት ከተሰሙት መልእክቶችም አንዱ፤ በዛ ያሉ ሴቶችና የቤተሰብ አባላት ወደ አደባባዩ እንዲሄዱ የሚጋብዝ ነው።  ምክንያቱም እንደተለመደው፤ ወንዶች ብቻ በርከት ብለው መታየት አይኖርባቸውም። እናም በዛ ያሉ ሴቶችንና ትንንሽ ልጆችን ጭምር እያየን ነን። ምክንያቱም ፤ ሥፍራው አስተማማኝ ነውና!»

የግብፅ ህዝብ አብዛኛው ወጣት ሲሆን የወደፊቱ መጻዔ ዕድላቸው በፕሬዚዳንት ሙርሲ ይቃናል ብለው አያስቡም። አንድ የ 16 ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ት/ት  ተማሪ ---

«ዛሬ እዚህ የተገኘሁት፣ የዝች  ሀገር ይዞታ ፣ ሙሉ በሙሉ የተለወጠ በመሆኑ ነው። ሙባረክ በብልሹ አሠራር የታወቁ ነበሩ። ግን ከሙርሲ ይሻላሉ። አሁን በግልጽ እንደምናየው፤  ሙርሲ ፣ ከሙባረክ  ፣ በብልሹ አሠራር  ይበልጥ  የታወቁ ናቸው።»

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች