ግብጽ እና ከፍተኛው የህዝብ ተቃውሞ | ዓለም | DW | 01.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ግብጽ እና ከፍተኛው የህዝብ ተቃውሞ

ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባራክ እንዲወርዱ በመጠየቅ በተለያዩ የግብጽ ከተሞች የተጀመረው የህዝብ ተቃውሞ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። አዲሱ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ኦማር ሱሌይማን ከተቃዋሚ ቡድኖች ጋ ለመወያየት ትናንት ሀሳብ አቅርበዋል።

default

በህግ የታገደው የተቃዋሚ ቡድን የሙስሊሞቹ ወንድማማችነት ሀሳቡን አልተቀበለውም። ቡድኑ ዛሬ በጠራው ግዙፍ ትዕይንተ ህዝብ የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት በተለይ በመዲናይቱ ካይሮ በታህሪር አደባባይ የተሰበሰበው ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ህዝብ ፕሬዚደንት ሙባራክ ስልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቁን ቀጥሎዋል። የግብጽ ጦር ኃይል ከሰልፈኞቹ መካከል አሉ ያላቸውን ሻጥረኞች ማሰሩ ተሰምቶዋል። የግብጽመንግስት ተቃውሞውን ለማሰናከል ኢንተርኔትን፡ ሞባይል ስልኮችን እና አንዳንድ የውጭ ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ዘግተዋል፤ ከነዚህ መካከል የቓታር ቴሌቪዥን ድርጅት አል ጄዚራ አንዱ ነው። በግብጽ የአል ጀዚራን መዘጋት በተመለከተ የዶቼቬለው ካርስተን ኪውንቶፕ የዘገበውን ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።

NO FLASH Al Dschasira in Katar Redaktion in Doha Ferhsehen

የአልጄዚራ ስቱድዮ

ሙባራክ መቀመጫውን ቐታር ያደረገውን ይህን ጣቢያ ከጥቂት ዓመታት በፊት በጎበኙበት ወቅት “የክብሪት ሳጥን ከምታክል ስፍራ የሚያስተጋባ ኃይለኛ አዋኪ ድምፅ “ ሲሉ ነበር የገለፁት ። በአጭር ጊዜ እውቅና ያተረፈው የአልጀዚራ ስቱድዮዎች ግን እስከ አሁን ድረስ እንደነገሩ በተሰራ ጊዜያዊ በሚመስል ቤት ውስጥ ነው የሚገኙት ። ሆኖም ዛሬ ማንም ይህን የዜና ማሰራጫ ድርጅት ዝቅ አድርጎ አይመለከትም ። የዚሁ ጣቢያ የካይሮው ቅርንጫፍ መዘጋትም ይህንኑ አመልካች ነው ። የካይሮ መንግስት አልጀዚራን የግብፅን ህዝብ ለአመፅ በመቀስቀስ ከሶ ግብፅ እንዳይሰራጭ አግዷል ። የዶቼቬለው Carsten Kühntopp እንደዘገበው አልጀዚራ ከመመስረቱ ከዛሬ 14 ዓመት አስቀድሞ በአረቡ ዓለም ፍርሀት የሌለበት ጋዜጠኝነት ፈፅሞ አልነበረም ። በዚህ የተነሳም የህዝቡ ብቸኛ አማራጭ ጣቢያዎች የአረብ ያልሆኑት የውጭ ዓለም ዓቀፍ ዜና ማሰራጫዎች ነበሩ ። አልጀዚራ ሲመሰረት ግን ሁሉንም ነገር ተቀየረ ። « የቢቢሲን የአረብኛ ቋንቋ አገልግሎት ፣ ራድዮ ሞንትካርሎን ወይም የአሜሪካን ድምፅ ራድዮን የእስራኤል ራድዮን ነበር የምናዳምጠው ። በሚያሳዝን ሁኔታ ለረዥም ጊዜ የዓረቡን ዓለም ህዝብ አመለካከት የሚቀርጹት የአረብ ያልሆኑ የመገናኛ ብዙሀን ነበሩ ። አልጀዚራ ሲመጣ ግን ነገሮች መለወጥ ጀመሩ ። »

Al Dschasira in Katar Redaktion in Doha

ፋይሰል አል ቃሲም ከአልጀዚራ ጣቢያ ኮከብ ጋዜጠኞች አንዱ ሲሆን ልዩ ልዩ አስተያየቶች የሚስተናገዱበት የውይይት መድረክ አዘጋጅ ነው ። የቃሲም ተወያይ እንግዶች በአረቡ ዓለም እንደ እርም የሚቆጠሩ ጉዳዮችን በማንሳት ጠንካራ ክርክሮችን ያካሂዳሉ ። ለምሳሌ በዚህ ዝግጅት ዲሞክራሲ እና እስልምና የሚጣጠሙ ስለመሆን አለመሆናቸው ፣ ተወያዮች የጦፈ ክርክር ላይ ናቸው ። ድምፅ ከት 2 እነዚህን የመሳሰሉ ርዕሶችን እያነሳ በሚያወያየው ጋዜጠኛ አል ቂስም አብዛኛዎቹ የአረቡ ዓለም መንግስታት ደስተኛ አይደሉም ። በዚህ የተነሳም የጉዞ እገዳ ጥለውበታል ፤ የግድያ ዛቻም ደርሶታል ። « በብዙ የአረብ መንግስታት ጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍሬያለሁ ። አብዛኛውን የአረብ አገራት መጎብኘት አልችልም ። ፕሮግራሙ በቐታርና በብዙ የአረብ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ፈጥሯል ። 5 የአረብ አገራት አምባሳደሮቻቸውን ከዶሀ ጠርተዋል ። በርካታ ዛቻዎችም ይደርሱኛል ። »

Al Dschasira Fernsehlogo

የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ሙያው በሚጠይቀው አሰራር መሰረት ነው የሚዘግቡት ። ብዙዎቹ በብሪታኒያ ዜና ማሰራጫ ኮርፖሬሽን በምህፃሩ BBC የሰለጠኑ ጋዜጠኞች ናቸው ። ኦሳማ ቢን ላደንን ጨምሮ ሁሉንም ወገን ያዳምጣሉ ። እስራኤሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአረብ ጣቢያ በስፋት የሚናገሩበት የዜና ማሰራጫ አልጀዚራ ነው ። ይህ ደግሞ ከቐታር የውጭ መርህ ጋር የሚጣጣም ነው ። ሁሉንም በማገናኘት ጥረት ላይ የተመሰረተ ነው ፤ ሃማስና እስራኤልን ፣ ኢራንና ዩናይትድ ስቴትስን ። የቐታር መሪ ሼክ ሃማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ይህን ጣቢያ በማቋቋም ትንሽቷ የአሚር ግዛታቸው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲሰጣት አደረጉ ። በውይይት እና ልዩ ልዩ አመለካከቶችን በማስተናገድ ላይ የሚያተኩረው ይኽው ጣቢያ በተዘዋዋሪ መንገድ የቐታር የውጭ መርህ ማስተጋቢያ መሣሪያ ነው ። ሀላፊው Nigel Parson እንደሚሉት አልጀዚራ ራሱን ኃይል የሌላቸው ህዝቦች ድምፅ አድርጎ ነው የሚቆጥረው ። « ካለአንዳች መጠራጠር ፣ እንደ አንድ ጣቢያ ለፍልስጤማውያን አዘኔታ አለው ። ይህ ሚዛንን የመጠበቅ አንድ አካል ነው ። እስራኤሎች ሁሌም መልስ የመስጠት መብት ይሰጣቸዋል ። ሁሉም ሰው ስለ አንድ ዜና መቶ በመቶ ተመሳሳይ አመለካከት አለው ማለት አስመሳይነት ነው ። ሰዎች በታሪኩ ላይ የተለየየ አመለካከት ይኖራቸዋል ። እስራኤሎች ይህን ያውቁታል ማለቴ ነው ። በተመሳሳይ ሁኔታ መልስ የመስጠት መብት እንዳላቸውም ያውቃሉ ። » ሁሉም አልጀዚራን ለማስቀረት ይሞክራሉ ። ቐታር ግን እስካሁን ሙከራውን ተቋቁማለች ። የቐታር አሚር በአንድ ወቅት ከዋሽንግተንን በኩል ሳይቀር ወቀሳ ቀርቦባቸው ነበር ። አሚሩ በያኔው የአሜሪካን ምክትል ፕሬዝዳንት ዲክ ቼኒ ቢሮ በተገኙበት ወቅት ቼኒ ጠረጴዛ ላይ አልጀዚራ የሚል ጎላ ያለ ርዕስ የሰፈረበት የዳጎሰ ፋይል ነበር የጠበቃቸው ። ያኔ በአልጀዚራ የኢራቅ ሽፋን ላይ ከቼኒ ወቀሳ የቀረበባቸው አሚሩ ሼክ ሃማድ ፣ ጥያቄያቸውን ዶሀ ለሚገኙት አዘጋጆች እንዲያቀርቡ ለቼኒ ነግረው በሰባት ሴኮንድ ቢሮውን ለቀው ወጥተዋል ።

ካርስተን ኪውንቶፕ

 ሂሩት መለሰ

 አርያም ተክሌ
 ነጋሽ መሀመድ