ግብጽ እና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ | ኢትዮጵያ | DW | 30.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ግብጽ እና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን «ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ» በሚል በዐባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን ግድብ በተመለከተ ካርቱም ሱዳን ላይ ያካሄዱትን ስብሰባ ትናንት አጠናቀዋል። የሦስቱ ሃገራት የዉኃ እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባካሄዱት ዉይይትም የፕሮጀክቱን ሁኔታ የሚያጠኑ የዉጭ ኩባንያዎች ምርጫ ላይ መስማማታቸዉ ተገልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:49
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:49 ደቂቃ

በአባይ ወንዝ ፍጥጫ

የግብጽ መገናኛ አውታሮች ኢትዮጵያ በሦስቱ ሃገራት መካከል አንዳች ስምምነት ሳይደረስ ግድቡን በውኃ ላለመሙላት ተስማምታለች ሲሉ ዘግበዋል። ኢትዮጵያን ወክለው ካርቱም ከተማ የተገኙት ተደራዳሪ የመገናኛ አውታሮቹ ዘገባ መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ ከፍተኛ የኃይል ምንጭ ለማምረት በሚል ግድብ መሥራት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ከቃላት ጦርነት ባሻገር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተኪያሂደዋል። ትናንት (ማክሰኞ ታኅሣሥ 19 ቀን፤2008 ዓም) ሱዳን መዲና ካርቱም ውስጥ የተጠናቀቀው ውይይት የተለያዩ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ሆኗል። ኢጂፕሺያን ስትሪት(egyptianstreets.com) እና አል ሞኒተር (al-monitor.com )የተባሉት ድረ--ገጾችን ጨምሮ የግብጽ የመገናኛ አውታሮች በሦስቱ ሃገራት ስምምነት እንደተደረሰ ዘግበዋል። ኢትዮጵያ ሦስቱ ሃገራት አንዳች ስምምነት ላይ ሳይደረሱ ግድቡን በውኃ ላለመሙላት ተስማምታለችም በማለት አስነብበዋል። አቶ ተሾመ አጥናፌ የውኃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፤ በወሰን እና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። ውይይቱን በተመለከተ ሲናገሩ «የግድቡ ግንባታ ከዚህ በፊትም እየተሠራ ነው፤ አሁንም ይቀጥላል» ያሉት አቶ ተሾመ አጥናፌ «ጋዜጦቹ ሌሎች ነገሮችን ለማድረግ የዘገቡት ነው» ብለዋል።

«ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ»

«ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ»አቶ ተሾመ አጥናፌ ኢትዮጵያን ወክለው በድርድሩ ካርቱም ከተማ የተገኙ ሲሆን፤ ከአራቱ ተደራዳሪዎች አንዱ ናቸው። ሮይተርስ የዜና ምንጭ በበኩሉ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን «ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ» በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ሊያስከትል የሚችለዉን ተጽዕኖ የሚያጠኑ ሁለት ኩባንያዎችን መምረጣቸዉን ዘግቧል። እንደዘገባዉ ሦስቱ ሃገራት ለጥናቱ ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎችን የመረጡት ሱዳን መዲና ካርቱም ውስጥ ከተወያዩ በኋላ ነዉ።

ጥናቱን እንዲያከናዉኑ የተመረጡትም BRL እና አርቴሊያ (Artelia) የተባሉት የፈረንሳይ ኩባንያዎች እንደሚሆኑም የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አትቷል። ቀደም ሲል 70 በመቶዉን ጥናት ከሚያከናዉነዉ የፈረንሳዩ BRL ጋር በመሆን ቀሪዉን 30 በመቶ እንዲመረምር የተመረጠዉ የኔዘርላንድ ኩባንያ ዴልታሪስ ከሥራዉ ራሱን ማግለሉ ነዉ አዲስ ኩባንያ በስምምነት እንዲተኩ ያደረገዉ። ሦስቱ ሃገራት የጥናቱ አማካሪዎች መረጣ ላይ የተስማሙ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ተሾመ አጥናፌ፤ ግብጽ «የውኃ ማስተንፈሻው ሊያንስ ይችላል» በሚል ላነሳችው ጥያቄ ምክክር እንዲደረግ መነጋገራቸውን አክለው ጠቅሰዋል።

ግብጽ 90 በመቶ የውኃ አቅርቦቷን የምታገኘው ከዐባይ ወንዝ እንደሆነ ይጠቀሳል፤ ዐባይ የኅልውናዬ መሠረት ነው ስትልም በተደጋጋሚ ትደመጣለች። በጎርጎዮሳዊዉ 1929 እና 1959 የተፈረመዉ ስምምነት ግብፅ እና ሱዳን ከምድራቸዉ ከማይመነጨዉ የጥቁር እና ነጭ አባይ ዉኃ 87 በመቶዉን የመጠቀም መብት እንደሚኖራቸዉ ያመለክታል። የጥቁር ዐባይ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የግድቡን ፕሮጀክት በተመለከተ ለግብፅ እና ለሱዳን አቻዎቻቸዉ «ሦስቱ አገሮቻችንን አይጎዳም» በማለት ማረጋጋታቸዉን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ዕቅድ መሠረት ግድቡ 6,000 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ እንዲያመነጭ ነዉ የታሰበዉ። ሮይተርስ እንደሚለዉ ከሆነም ሃገራቱ የተስማሙባቸዉ የፕሮጀክቱን ተፅዕኖ የሚያጠኑ ኩባንያዎች ተግባራቸዉን ሳይጀምሩ የግድቡ ሃምሳ በመቶ ሥራ ተጠናቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic