ግብር የሚሸሹት አፍሪቃውያን | ኤኮኖሚ | DW | 03.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ግብር የሚሸሹት አፍሪቃውያን

በጎርጎሮሳዊው 2010 ዓ.ም. የገና በዓል የፓናማው የጥብቅና ተቋም ሞዛክ-ፎንሴካ የመልካም ምኞት መልዕክት የሰፈረባቸው 409 ካርዶችን በአፍሪቃ ለሚገኙ ደንበኞቹ ልኮ ነበር። እነዚህ የሞዛክ-ፎንሴካ ደንበኞች ገንዘባቸውን ከአገራቸው በማሸሽ በሌሎች አገራት የሸሸጉ ባለስልጣናት እና የኩባንያ ባለቤቶች ነበሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:00

ግብር የሚሸሹት አፍሪቃውያን

ዛሬ ወደ ሶስት እጅ የሚጠጋው የአፍሪካውያን ባለጠጎች ሐብት አነስተኛ ግብር በሚያስከፍሉ አገሮች ይገኛል። ይህ አህጉሪቱን በየአመቱ ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር የግብር ገቢ ያሳጣታል። የ44 የአፍሪቃ አገሮች ባለጠጎች እና ባለስልጣናት ገንዘባቸውን ከገዛ ህዝባቸው እያሸሹ በውጭ አገራት እንደሚሸሽጉ በፓናማ ሰነዶች ላይ በተደረጉ ምርመራዎች የተገኙ አዳዲስ ግኝቶች ጠቁመዋል። ይህ ለአፍሪቃውያን ሌላም የራስ ምታት ይዞ ብቅ ብሏል። አብዛኞቹ ከአፍሪቃ ጥሬ ሐብት ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው። በጥናቱ መሰረት አፍሪቃ ከግብር ማግኘት የነበረባትን ገቢ በማጣቷ ድህነት ሥር እየሰደደ ኢ-ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍሉም ቅጥ እያጣ እንደሆነ ጠቁሟል። ቻርሎቴ ቤከር የኦክስፋም የዘመቻዎች አስተባባሪ ናቸው።


«የቅርብ መረጃዎች የተገኙት ግብር ማሸሽ በአፍሪቃ አገሮች ላይ ያለውን የከፋ ተፅዕኖ ከሚያሳየው እና ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የፓናማ ሰነዶች የምርመራ ውጤት ነው። በአህጉሪቱ የሚሰሩ ኩባንያዎች እና የአፍሪቃ ባለጠጎች የሚከፍሉት ግብር እጅግ አነስተኛ ነው አሊያም ጨርሶ አይከፍሉም። የአፍሪቃ መንግስታት የአመታዊ ወጪያቸውን በደሐው ዜጋ ጫንቃ ላይ ጭነውታል። ይህም በመላ አህጉሪቱ ለሚስተዋለው የእኩልነት እጦት ቀውስ ከፍተኛ ድርሻ አለው። አነስተኛ ግብር በማስከፈል ገንዘብ የሚሸሽጉት አገራት ደግሞ የዚህ አሳፋሪ ተግባር ማዕከል ናቸው። የአገራቱ ኤኮኖሚም ተጎድቷል። የፋይናንስ ሥርዓቱ ሚስጥራዊነት ባለጠጋ አፍሪቃውያን እና ኩባንያዎች በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዲያጭበረብሩ አግዟቸዋል። ኩባንያዎች ከግብር በሚያሸሹት ገንዘብ ምክንያት የአፍሪቃ አገሮች በየዓመቱ 38 ቢሊዮን ዶላር እያጡ ነው። አፍሪቃ ግለሰቦች ከግብር በሚያሸሹት ገንዘብ ምክንያት የምታጣው 14 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሳይሆን ኩባንያዎችም አስተዋጽዖ አላቸው።»በዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት እና በጀርመኑ ዙድ ዶቸ ሳይቱንግ ጋዜጣ በመመርመር ላይ የሚገኙት የሞዛክ-ፎንሴካ የፓናማ ሰነዶች በዘር፤ሀይማኖት እና ፖለቲካዊ ጥቅም የተሳሰሩ አፍሪቃውያን ከገዛ ህዝባቸው ገንዘብ የሚያሸሹበትን ሥልት አጋልጠዋል። አንዳንዶቹ ዘመዶቻቸው፤ ወዳጆቻቸው አሊያም የጥቅም አጋሮቻቸው ዛሬም በየአገሮቻቸው ሥልጣን ላይ ናቸው። ገንዘብ የሚያሸሹበት፤ከግብር የሚያመልጡበት መንገድ ውስብስብ መሆን ብቻ ሳይሆን መንግስታቱም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የላቸውም። አፍሪቃውያን ይህን ማስቆም ይችሉ ይሆን?

«በመጀመሪያ ደረጃ አንድን ነገር ለማሳካት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያሻል። አሁን ይፋ እየሆኑ ያሉት ግብር የማሸሽ አሳፋሪ ተግባራት በመንግስታት ላይ ጫናውን ያሳድገዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በቀዳሚነት ግን መሰራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ። የኩባንያዎችን ባለቤቶች ማንነት በግልጽ የሚያሳውቅ በጣም ግልጽ የፋይናንስ ሥርዓት ያስፈልጋል። መንግስታት ተገቢውን ግብር ለመሰብሰብ የኩባንያ ባለቤቶችን በግልጽ ማወቅ አለባቸው። ግለሰቦች እና ኩባንያዎች አነስተኛ ግብር በሚከፈልባቸው አገራት የሚሰሩትን የምስጢር ሥራ ማወቅ እስካልተቻለ ድረስ መቆጣጠር አይቻልም። ይህ ሊለወጥ ይገባል። ግዙፍ ኩባንያዎች ሥራ ላይ በተሰሩባቸው አገራት ያገኙትን ትርፍ እና የሚከፍሉትን ግብር መጠን ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ከተቻለ ድብቁ የፋይናንስ ሥርዓት መሰረቶችን መናድ ይቻላል። ምስጢራዊነትን ማስወገድ ከተቻለ ዜጎች መንግስታቸውን ተጠያቂ ማድረግ ይችላሉ።»

የአፍሪቃ አስር ባለጠጎች ጠቅላላ ኃብት ከኬንያ አመታዊ የምርት መጠን (GDP) ጋር እኩል ነው። እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ ከጎርጎሮሳዊው 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የአፍሪቃ ቢሊየነሮች ቁጥር በእጥፍ ሲያድግ በድህነት አረንቋ የሚማቅቁት ዜጎች ከጎርጎሮሳዊው 1990 ዓ.ም. ጀምሮ በ50 ሚሊዮን ጨምሯል። ከዓለም አገራት የከፋ ኢ-ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል ከሚገኝባቸው አገራት ሰባቱ አፍሪቃ ውስጥ ይገኛሉ። ከዓለም የወርቅ እና ፕላቲኒየም አምራች አገሮች ቀዳሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪቃ በዚህ ግንባር ቀደም ነች።

የፖናማ ሰነዶች አዳዲስ የምርመራ ውጤቶች አፍሪቃ በእጅ መንሻ ፤ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ከግብር በሚሸሹ ባለጠጎች በቢሊዮን ዶላር እየተዘረፈች መሆኑን ይፋ አድርገዋል። የአፍሪቃ መንግስታት የባንክ እና የፋይናንስ ተቋማት መረጃ ልውውጥን በመቆጣጠር ከጉያቸው የሚሸሸውን ገንዘብ ማዳን የቻሉም አይመስልም። ለመሆኑ በባንኮች እና መንግስታት መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ ምን ይመስላል?አሁንም ቻርሎቴ ቤከር

«ይህ እንደየአገራቱ ይለያያል። ነገር ግን በቂ የመረጃ ልውውጥ የለም። በአፍሪቃ የሚሰሩ ኩባንያዎች የሚያገኙት ትርፍ እና የሚከፍሉት ግብር ላይ በቂ የመረጃ ልውውጥ የለም። የበለጠ ግልጽነት ያስፈልጋል።»

በአልጄሪያ የተፈጸመ የ10 ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ እና ጋዝ ሥምምነት በፓናማ ሰነዶች ምርመራ ይፋ ከተደረጉ ጉዳዮች ውስጥ ይገኙበታል። በአልጄሪያ የነዳጅ እና ጋዝ የማምረት ፈቃድ አግኝተው ገንዘብ ያሸሹና በጣልያን በምርመራ ላይ ከሚገኙ 17 ኩባንያዎች መካከል የአስራ ሁለቱ ዶሴ የተከፈተው በሞዛክ-ፎንሴካ አማካኝነት ነው። የኩባንያዎቹ ባለቤቶች በአልጄሪያ የስራ ፈቃድ ለማግኘት ለአገሪቱ ባለስልጣናት 275 ሚሊዮን ዶላር እጅ መንሻ ከፍለዋል። የቀድሞው የአልጄሪያ የኢነርጂ ሚኒስትር እና የኦፔክ ፕሬዝዳንት ቸኪብ ቸህሊል ክፍያ ከተፈጸመላቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው።

የላይቤሪያ የአልማዝ አምራቾች፤ የናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት ሚኒስቴር ባለስልጣናት የድብቅ ኩባንዎች ባለቤቶች መሆናቸውን የፓናማ ዶሴዎች አጋልጠዋል። የናይጄሪያ የቀድሞ የነዳጅ ሚኒስትር ዲዛኒ አሊሰን ማዱኬ አምስት ድብቅ ኩባንያዎች እንዳሏቸው የተጋለጠ ሲሆን ግብር ያልከፈሉበትን ገንዘብ በስዊዘርላንድ፤ብሪታኒያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ሸሽገዋል። የ46 አመቱ ባለጠጋ ኩላ አሉኮ ከባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ከናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት ሽያጭ 1.8 ቢሊዮን ዶላር የማሸሽ ክስ ቀርቦባቸዋል። ኩላ አሉኮ የተሰማሩበት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ከመጋለጡ በፊት የናይጄሪያ መንግስት እና መገናኛ ብዙኃን በሥራ ፈጣሪነት እና እርዳታ በመስጠት ምግባራቸዉ ያሞካሿቸው ነበር።


የአፍሪቃ ኤኮኖሚስቶች አነስተኛ ግብር የሚያስከፍሉ አገራት እና የፋይናንስ ተቋማት መጥፋት አለባቸው ሲሉ ይወተውታሉ። ይህ ግን የሚሳካ አይመስልም። አገራቱንም ሆነ ተቋማቱን በህግ ከለላ የሚሰጧቸው የበለጸጉት አገራት ናቸው። ቻርሎቴ ቤከር ገንዘብ የሚሸሽጉ እና ከግብር የሚሸሹ ግለሰቦች እና ተቋማትን ለማጥፋት ምስጢራዊ አሰራር ሊቀየር ይገባል። ይቻላልም የሚል እምነት አላቸው።

« ምስጢራዊ አሰራርን ማስወገድ ከተቻለ አነስተኛ ግብር የሚያስከፍሉ አገራት እና ተቋማት ህልውና ማጥፋት ይቻላል። ችግሩ በአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚገኝ ነው።»

ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት መንግስታት በተለይም ኃያላኑ መንግሥታት ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ቢወተወቱም ከስብሰባ የዘለለ የፈየዱት ነገር የለም። 30 በመቶ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ከሚኖሩባት ናይጄሪያ የተፈጥሮ ሐብት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዘርፈዋል ተብለው የተወነጀሉት ኩላ አሉኮ ገንዘባቸውን ያስቀመጡት ስዊዘርላንድ፤ሉክሰምበርግ፤ፈረንሳይ ብሪታኒያ እና ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ባንኮች ነው። ሰውየው በፈረንሳይ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችን ለዝነኞች ያከራያሉ። በሆሊውድ እና ሎስ አንጀለስ ከከባለጠጎች እና ታዋቂ ሰዎች ጋር ይዝናናሉ።

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic