ግብር የሚሸሹት ባለጠጎች  | ኤኮኖሚ | DW | 08.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ግብር የሚሸሹት ባለጠጎች 

ሐብታቸዉን ግብር ወደ ማይከፈልባቸው አገሮች፤ ግዛቶች እና አስተዳደሮች ያሸሻሉ የተባሉት የዓለም ግዙፍ ኩባንያዎች ባለቤቶች፤ የአገራት መሪዎችና ፖለቲከኞ ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገ ዶሴ ተጋልጠዋል። ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥምረት ይፋ ያደረገው ሰነድ ሐብት፤ሥልጣን እና ኃይል ያላቸው ጥቂት ልሒቃን ግብር ላለመክፈል የሔዱትን ርቀት አሳይቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:03 ደቂቃ

ግብር የሚሸሹት ባለጠጎች

የፓራዳይዝ ሰነዶች አፕልቤይ የተባለውን የሕግ ተቋም ጨምሮ በተለያዩ አገራት የንብረት አስተዳደር ሥራ ላይ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ሾልከው የወጡ 13.4 ሚሊዮን ዶሴዎች ይዘዋል። ሰነዶቹ ዝቅተኛ ግብር በሚያስከፍሉ አገራት ከተመዘገቡ 19 ኩባንያዎች ያፈተለኩ መረጃዎችንም ይዘዋል። መረጃዎቹን ይፋ ያደረጉት ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥምረት እና 95 የመገናኛ ብዙኃን አጋሮቹ ናቸው።ጀርመናዊዉ ኒኮላስ ራይሽተር ለወራት ሰነዶቹን ከመረመሩ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው። 

"የፓራዳይዝ ሰነዶች ከታክስ ገነቶች የወጡ ምሥጢራዊ ሰነዶች ጥርቅም ነው። ገንዘባቸውን ግብር በማይከፈልባቸው አገሮች የደበቁ አሊያም መክፈል የነበረባቸውን የግብር መጠን ለመቀነስ ግብር የማይከፈልባቸውን አገሮች የተጠቀሙ ሰዎችን ታሪኮች ይናገራሉ።"

በፓራዳይዝ ሰነዶች የኤሌክትሮኒክ መልክዕት ልውውጦች፤ የንግድ ሥምምነቶች እና የባንክ ሰነዶች ጭምር ይገኙበታል። ግማሽ ያክሉ አፕልባይ ከተባለው ኩባንያ የወጡ ናቸው። ኩባንያው በጎርጎሮሳዊው 1898 በቤርሙዳ የተመሰረተ ሲሆን በቨርጅን እና ካይማን ደሴቶች በሆንግ ኮንግ፣ ሞሪሽየስ፣ሲሸልስ እና ሻንጋይ ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉት። የፍትኃዊ ታክስ ጥምረት ኃላፊ እና ተንታኙ ማርኩስ ማይንዘር የአሁኖቹን  ከአንድ አመት ገደማ በፊት ይፋ ከተደረጉት የፓናማ ሰነዶች ጋር ያመሳስሏቸዋል። 

"በዓለማችን ላይ ከፍ ያለ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ዴሞክራሲ የጣለባቸውን ሕግጋት እንዲያጭበረብሩ ሲያግዝ እጅ ከፍንጅ የተያዘው የሕግ ተቋም ነው። በሙስና ፤ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ግብር ባለመክፈል ተግባር  የተሰማሩ ከፍተኛ ገንዘብ እና ኃይል ያላቸው ኩባንያዎች ወይም ፖለቲከኞች ናቸው። ይኸ አጠቃላይ የሥርዓት ችግር እንጂ የጥቂት ግለሰቦች ጉዳይ አለመሆኑንም ይጠቁማል።"

መቀመጫውን በሲንጋፖር ያደረገው ኤዥያ ሲቲ ትረስት የተባለው የሕግ አማካሪ ተቋም ሌላው የሰነዶቹ ምንጭ ነው። በኩባንያው ድረ-ገፅ እንደሰፈረው በሖንግ ኮንግ፣ ዱባይ፣ ኒውዚላንድ፣ ፓናማ እና ሳሞዓ ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉት። አፕልባይ የተባለው ኩባንያ ባለፈው ወር የመረጃ ሰንዱቆቹ ከዓመት በፊት በሰርጎ ገቦች ተሰርስረው የደንበኞቹ መረጃ ሳያፈትልክ እንዳልቀረ ገልጦ ነበር። 

የጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ዙድዶይቼ ዛይቱንግ ሾልከው የወጡት ሰነዶች የደረሱት የመጀመሪያ መገናኛ ብዙኃን ነው። ከአመት ገደማ በፊት በርካታ አፍሪቃውያንን ጨምሮ የናጠጡ ነጋዴዎች እና ኩባንያዎችን ያጋለጡት የፓናማ ሰነዶችም ቀድሞ የደረሱት ለዚሁ ጋዜጣ ነበር። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልን በኃላፊነት የሚመሩት ሮቢን ሖደስ ሰነዶቹ ያፍረጠረጡትን መረጃ አስደናቂ ይሉታል።

"እንዲህ ምስጢራዊ መረጃ ሲያፈተልክ በግዙፍነቱ ይህ ከፓናማ ሰነዶች ቀጥሎ ሁለተኛው ነው። እጅግ አስደናቂ ነው። ምክንያቱም ባለፈው ዓመት በዓለም ላይ ስላሉት ድብቅ ኩባንያዎች እና ስውር አሰራር ላይ ሰፊ ውይይት ተጀምሮ ነበር። ይኸኛም ግዙፍ ኩባንያዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች በንብረታቸው ላይ የሚከተሉትን ምሥጢራዊነት ያሳያል።"

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥምረት አሁን ይፋ በተደረጉት ሰነዶች ከ50 አገሮች የ120 ፖለቲከኞች ስሞች መገኘታቸውን አስታውቋል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሬክስ ቲለርሰን፤ የንግድ ምኒስትሩ ዊልበር ሮስ እና የካናዳው ጠቅላይ ምኒሥትር ጀስቲን ትሩዶ የቅርብ አማካሪ በሰነዶቹ ከተጠቀሱ ስሞች መካከል ናቸው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪዎች፣ የካቢኔ አባላት እና የገንዘብ ደጋፊዎቻቸው የዓለምን ቀልብ ከሳቡት ሰነዶች መካከል ስማቸው ሰፍሯል። የሮክ ሙዚቀኛው ቦኖ እና የፎርሙላ ዋን መኪና አሽከርካሪው ልዊስ ሐሚልተንም ተካተውበታል። ግዙፎቹ የናይክ፣ አፕል፣ኡበር እና ፌስቡክ ኩባንያዎች የግብር ሕግጋት ያሉባቸውን ክፍተቶች በመጠቀም ሊከፍሉ ይገባ ከነበረ ግብር አምልጠዋል። 

የቅንጡ ስልኮች አምራቹ አፕል በውጪ አገር ከሚገኝ ጥሪቱ ከፍ ያለውን ከአየርላንድ ዝቅተኛ ግብር ወደ ሚከፈልባት የብሪታኒያዋ ጀርሲ ደሴት አዘዋውሯል። አፕል ዝቅተኛ ታክስ ከሚከፍልባት አየርላንድን ትቶ ጀርሲን ማማተር የያዘው የአውሮጳ ኅብረት አየርላንድ የግብር ሕጓ ያለበትን ክፍተት በመድፈን እንድታስተካክል ጫና ሲያሳድር ነበር። 

ለኩባንያዎቹ እና የናጠጡት ሐብታሞችን ጥሪት ከግብር የማሸሹን ሥራ ከሚያቀላጥፉት አፕልባይን መሰል ድርጅቶች የምሥጢር ሰነዶች ሲያፈተልኩ የመጀመሪያው አይደለም። ከአንድ አመት ገደማ በፊት ሞዛክ-ፎንሴካ ከተባለ ተመሳሳይ ተቋም ያፈተለኩ መረጃዎች ቁጣ ቀስቅሰው ነበር። ቁጣ እና ንዴቱ ግን የታሰበው ያክል ፍሬ አለማፍራቱን ማርኩስ ማይንዘር ይናገራሉ።

"የፓናማ ሰነዶች ይፋ ከሆኑ በኋላ በርካታ ፖለቲካዊ ውትወታ ታዝበናል። እንደ አለመታደል ሆኖ የተወሰደው እርምጃ ከጥያቄው ጋር አይስተካከልም። በጀርመን እና በአውሮጳ ኅብረት ደረጃ የኩባንያዎች ትክክለኛ ባለቤቶችን የመመዝገብ አሰራር እንዲጠናከር ጥረት ተደርጓል። አሁንም በግዙፍ ኩባንያዎች ዘንድ ያለው ምሥጢራዊ አሰራር እንዲቀንስ ግልፅነት እንዲሰፍን ከጀርመን መንግሥት ጫና እየተደረገ ይገኛል።"

ለመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለቤተሰቦቻቸው፤ የምሥጢር አጋሮቻቸው ድብቅ ድርጅቶች በመመሥረት ገንዘብ ለማዘዋወር፤ ሕጋዊም ይሁን ሕገ-ወጥ ግብይት የሚፈፅሙትን ኩባንያዎች የመቆጣጠሩ ተግባር በመንግሥታት እጅ ነው። የአገራት ሕግጋት ያሉባቸውን ክፍተቶች ሥልጣኑንም ገንዘቡንም የያዙት ሰዎች ሊፈቱ የመሞከራቸው ነገር አጠራጣሪ ቢመስልም እንደ ሮቢን ሖደስ ያሉ ሰዎች የለውጥ እርማጃ አለ ብለው ያምናሉ። ማንነታቸው እና ምንነታቸው በግልፅ የማይታወቅ አጠራጣሪ ኩባንያዎችን ትክክለኛ ባለቤት መለየት እና መመዝገብ ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሆን ሖደስ እምነታቸው ነው። 

"ወደ ፊት ይደረጋል ብቻ ሳይሆን አሁንም እየተደረገ ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ይኸ ተጀምሯል። ዴንማርክ እና ዩክሬንን ጨምሮ በመላው ዓለም ያሉ አገሮች የኩባንያ ባለቤቶችን ትክክለኛ ማንነት ለመመዝገብ ጥረት እየተደረገ ነው። ከኩባንያዎቹ ጀርባ ማን እንዳለ ማወቅ እና በግዙፎቹ ኩባንያዎች ማን እንደሚጠቀም ማወቅ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።"

የብሪታኒያዋ ንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የግል ገንዘብ በካይማን ደሴቶች እና በቤርሙዳ መገኘቱን የፓራዳይዝ ሰነዶች ጠቁመዋል። ገንዘቡ ለሕገ-ወጥ ተግባር ስለመዋሉም ሆነ ንግሥቲቱ የግብር ግዴታቸውን ቸል ስለማለታቸው የተገለጠ ነገር የለም። ቢሆንም የብሪታኒያ መንግሥት የበላይ ሆነው ሳለ ገንዘባቸው ከዶሴው ጋር መያያዙ አነጋጋሪ ሆኗል። 

አሁን ይፋ የተደረጉት ሰነዶች ገና ምሥጢራዊውን የአሰራር ሥርዓት የሚያጋልጡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ናቸው። በመጪዎቹ ሳምንታት ከፍ ያለ ስልጣን ያላቸው ሹማምንት፣ የሥራ አጋሮቻቸው እና እጅግ ጥቂት የሚባሉት የናጠጡ ሐብታሞች ገንዘቦቻቸውን ለማሸሽ የሚከተሏቸውን አሰራሮች የሚያጋልጡ ሰነዶች ይጠበቃሉ። 

ማርኩስ ማይንዘር የሚመሩት የፍትኃዊ ግብር ጥምረት አገሮች ግዙፎቹን ኩባንያዎች የዓለም ትርፍ ግብር እንዲያስከፍሏቸው ጥሪ አቅርቧል። አሁን ባለው የግብር ሥርዓት አገሮች በድንበራቸው ውስጥ ብቻ የሚገኙ ቅርንጫፎችን ብቻ በማስከፈል የተወሰነ መሆኑን የገለጠው ድርጅቱ አሰራሩ አፕል እና ናይኬን የመሳሰሉ ኩባንያዎች ዝቅተኛ ገቢ ወዳለበት እንዲነጉዱ ፈቅዶላቸዋል ሲል ተችቷል። ማርኩስ ራሳቸው ግን መንግሥታት ባለጠጎች እና ግዙፍ ኩባንያዎች ከግብር ዘወር እንዲሉ የያስችለው አሰራር እንዲቀር ስለመቻላቸው ጥርጣሬ አላቸው። "አሰራሩ እንዲዘልቅ የሚሹ መንግሥታት እና የመንግሥታት ክፍልፋዮች አሉ። ምክንያቱም እጅግ አስደናቂ የገንዘብ ማምረቻ አሰራር ነው። ለባለጠጎቹ ከዕይታ ለመሰወር፣ ተጠያቂነትን ለማምለጥ እና ኃላፊነትን ለመሸሽ ይረዳቸዋል። ስለዚህ አሁንም አሰራሩ እንዲቀጥል የሚሻ ጠጣር ፖለቲካዊ ፍላጎት አለ።"

የባለጠጎቹን ገንዘብ ከግብር ባለሥልጣናት፤ ተቆጣጣሪዎች እና የወንጀል መርማሪዎች አርቀው ቢደብቁም እንኳ የግብር ገነት የሚባሉት አገራት የሚከተሉት አሰራር ሕጋዊ ነው። ሰነዶቹን ከመረመሩት መካከል አንዱ የሆነው የብሪታኒያው ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ እንደሚለው ግን የሕግጋት ክፍተት በአገሮች እና ፖለቲከኞች ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ለመሻገር ባለወረቶች እና ኩባንያዎች ያላቸውን ሕገ-ወጥ ግንኙነት ለመደበቅ ጭምር ሥራ ላይ ሲውል ይታያል። 

በባለፈው አመት የፓናማ ሰነዶች ይፋ ከሆኑ በኋላ አሰራሩ ውስብስብ ከሚገመተውም በላይ ግዙፍ መሆኑ ገሐድ እየሆነ መጥቷል። የአሰራሩን የሚዘውሩት ተቋማትም ይሁን ከግብር የሚሸሹት ባለወረቶች ምሥጢር መጋለጡ የሚፈይደው ነገር መኖሩ ሌላ ጥያቄ ነው። ፍትሕ እና ታሪክ ግን ሁልጊዜም ገንዘብ እና ጉልበት ላላቸው ያደላል። 


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic