ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪና ካሊድ አህመድ በአመክሮ ተለቀቁ | ኢትዮጵያ | DW | 10.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪና ካሊድ አህመድ በአመክሮ ተለቀቁ

ከ4 ዓመት በፊት በጸረ ሽብር ሕጉ ተከሰው ተፈርዶባቸው የነበሩት ጋዜጠኛ ዳርሴማ ሶሪ እና ካሊድ አህመድ የአመክሮ ጊዜያቸውን ጨርሰው ዛሬ ምሳ ሰአት ላይ መለቀቃቸው ተገለጠ። ጋዜጠኞቹ መለቀቅ ከነበረባቸዉ ጊዜ ከአንድ ወር በላይ «አለአግባብ በእስር ላይ» መቆየታቸዉን ጠበቃ ሰኢድ አብደላ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:57

«በሞያዬ ወደፊትም እቀጥላለሁ» ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ

ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪና ካሊድ አህመድ በፀረ-ሽብር ሕጉ አንቀጽ 7 ንዕስ አንቀጽ 1 መሰረት በሽብር ድርጅት ዉስጥ መሳተፍ በሚል ወንጀል ተከሰዉና በዚሁ ወንጀልም ጥፋተኛ ናችሁ በሚል ተፈርዶባቸዉ ላለፉት 4 ዓመታት በዕስር ቆይተዋል። በዛሬዉ ዕለት ግን የዕስር ጊዜያቸዉን ጨርሰዉ መለቀቃቸዉን የጋዜጠኞቹ ጠበቃ አቶ አብደላ ሰኢድ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪንና ካሊድ አህመድን ጨምሮ የ19 ሰዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ አብደላ ሰኢድ፦ ጋዜጠኞቹ ከዕስር የተለቀቁት የይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳያቸዉን ዐይቶ እንደኾነ ተናግረዋል። ጠበቃ ሰኢድ፦ አብዛኞቹ ታሳሪዎች የተፈረደባቸው የ5 ዓመት ከ 6 ወር የዕስር ቅጣት ወደ 3 ዓመት ሲቀየር፤ የጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ ደግሞ ወደ 3 ዓመት ከ 7 ወር ዝቅ ያለው ፍርድ ቤቱ በወሰነው መሰረት ነዉ ብለዋል።

በዛሬዉ እለት ከእስር ነፃ የሆነዉ ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ እነንደሚለዉ ከእስር በመፈታቱና ከቤተሰብ በመቀላቀሉ ደስተኛ ነዉ። ይሁን እንጅ ታስሮ የነበረው ያለ አግባብ መኾኑን ለዶይቸ ቬለ ተናግሯል። «ከዚህ አኳያ ከቤተሰቦቼ ጋር መቀላቀሌ ደስ ቢለኝም፤ ግን ያለአግባብ ነበር የታሰርኩት ብዬ ስለማስብ አግባብ ባልሆነ መንገድ መታሰሬ የፕሬስ ሕጉንም የሀገሪቱን ሕግም የሚጥስ ነዉ» ብሏል። 

ጋዜጠኝነቱ ዋጋ እንዳስከፈለው ቢገልጥም ወደፊትም ቢሆን በዚሁ ሞያዉ እንደሚቀጥል አብራርቷል። «የሀገሪቱ ሕግ ስታይዉ አንድ ጋዜጠኛ በሠራዉ ሥራ በጋዜጠኝነት ሥራዉ አይከሰስም አይታሰርም የሚል ሕግ አለ። ሕግ ተጥሶ ነዉ የታሰርነዉ። እኔ አሁን ዛሬ አነጋግረዉኝ ነበር። ወደፊት እኔ በዚህ ሞያ ነዉ የምቀጥለዉ።»

የሁለት ልጆቹ እናትና ባለቤቱ ወይዘሮ ነኢማ ሸምሱ የባለቤቷን መፈታት ለማመን እንደተቸገረችና እንዳስደነገጣት ተናገራለች። «ደስታ ነው፤ አለማመንም አለ። አኹንም በቃ መልሰው ሊያስገቡት ይኾን የሚል ፍራቻ ነበረኝ» ብላለች።

ከጋዜጠኞቹ ጋር ላለፉት አራት ዓመታት ብዙ ዉጣ ዉረድ እንዳሰለፉ የሚናገሩት ጠበቃ ሰኢድ ጋዜጠኞቹ የተፈቱት መፈታት ይገባቸዉ ከነበረበት ጊዜ በአንድ ወር ዘግይተዉ ነዉ። ያም ሆኖ ግን እንደ ጠበቃ ብቻ ሳይሆን እንደአንድ ኢትዮጵያዊ የጋዜጠኛ ዳርሰማና የካሊድ መፈታት እንዳስደሰታቸዉ ነዉ የተናገሩት።

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ
 

 

Audios and videos on the topic