ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ሲታወስ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 06.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ሲታወስ

የቀድሞው የዶይቼ ቬለ ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ 4 ዓመት ከ6 ወራት ተቆጠሩ። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው ታደሰ ፖለቲካዊ፤ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን እየተከታተለ ለዶይቼ ቬለ ይዘግብ ነበር። ዶይቼ ቬለ ለጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው መታሰቢያ አዘጋጅቷል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:36

የጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ዝክር

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጥንቅጥ፤ የበዓል ገበያዎች እና ኤኮኖሚያዊ ርዕሰ-ጉዳዮች፤የፍርድ ቤት ውሎዎች ፤ ተቃውሞዎች፤የሹማምንቱ የምክር ቤት ውሎዎች ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ለዶይቼ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ከሰራቸው ዘገባዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለጋዜጠኝነት አስቸጋሪ በነበረባቸው ዓመታት የፖለቲከኞች ትችቶችን፤ ክሶች እና ብያኔዎች እየተከታተለ ዘግቧል። የጋዜጦች እና መፅሔቶች ውጣ ውረድ ፈትሿል። የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባዎች እና ውይይቶች እንዲሁም የምስራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ተከታትሏል። በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አስተያየት ሰብስቧል። ታደሰ በጋዜጠኝነት ባገለገለባቸው ዓመታት ወደ ግዙፉ የዶሎ አዶ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ድረስ ተጉዞ ዘገባዎች ሰርቷል። 
ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ዶይቼ ቬለ በሙያቸው በማገልገል ላይ ሳሉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ጋዜጠኞችን በቦን እና በርሊን በሚገኙ ቢሮዎቹ አስቧል። ጋዜጠኞቹ ታደሰ እንግዳው፤ዮዓኺም ካኔጊይትሰር፤ ኡልሪሽ ሔበርሊንግ፤ካረን ፊሸር፤ክርቲያን ሽትሩቨ፤ሳጋር ሳርዋር እና ሜህሩን ሩኒ ናቸው። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከበርካታ ሰራተኞች ጋር የታደሙት የዶይቼ ቬለ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ሊምቡርግ ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ሳሉ ህይወታቸውን ያጡ ጋዜጠኞችን ማሰብ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
«በምንም መልኩ ሕይወታቸው ይለፍ በአደጋም ይሁን ተገድለው አሊያም ደግሞ የሽብር ጥቃት ደርሶባቸው ሁሉም ለእኛ ለዶይቼ ቬለ የተሰማሩ ሰዎች ናቸው። እነሱን በተገቢው መልኩ መዘከር ይገባል። ዛሬም የምናደርገው ይኸንን ነው።» 


የአማርኛ ክፍል ኃላፊው ሉድገር ሻዶምስኪም የዶይቼ ቬለን ተግባር አወድሰው ታደሰ መቼም የማይዘነጋ የተቋሙ ባልደረባ እንደነበር አስታውሰዋል። 
«የዶይቼ ቬለ ሥራ አመራር በሥራ ላይ ሳሉ ህይወታቸውን ያጡ ባልደረቦቹን ለማሰብ በመወሰኑ ታላቅ ምሥጋና አለኝ። የተዘጋጀለት መታሰቢያ ታደሰ በሕይወት ሳለ የሰራውን ላቅ ያለ ሥራ በአማርኛው ክፍል ለሚገኙ የሥራ ባልደረቦቹ  ብቻ ሳይሆን ለመላ ድርጅቱ የሚያስታውስ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በመላው ዓለም በተለይም በአፍሪቃ ጋዜጠኞች ያለባቸውን አስቸጋሪ አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ የሥራ ሁኔታ ማስረጃም ነው። ይሕ በተለይ ለኢትዮጵያ እውነት ነው። በአማርኛው ክፍል የምንገኝ የሥራ ባልደረቦቹ ታደሰን ታታሪነት እና ለሙያዊ መርኆዎች ባለው ጽኑ አቋም በእያንዳንዷ ቀን እናፍቀዋለን።»

ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር በድንገኛ የመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው። መስከረም 1965 ዓ.ም. በጎንደር የተወለደው ታደሰ የእንግሊዘኛ ሥነ-ፅሁፍ እና ጋዜጠኝነትን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምሯል። በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች ላይ በሙያው ይሰራ የነበረው ታደሰ እንግዳው በ1996 ዓ.ም. የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ቋንቋን ክፍልን ተቀላቅሎ እስከ ሕልፈተ-ሕይወቱ ድረስ ሰርቷል። ሥራው ግን ሁሌም አልጋ ባልጋ አልነበረም። 

በዶይቼ ቬለ  የፌስቡክ ማሕበራዊ ድረ-ገፅ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት ቲጂ በለጠ «እጅግ በጣም የማደንቀው ምርጥ ጋዜጠኛ ነበር ድምፁ ለጋዜጠኝነት የተፈጠረ ነበር» ብለዋል። በርካቶች በዚሁ በፌስ ቡክ ገፃችን ታደሰ በሰላም እንዲያርፍ ምኞታቸውን ገልጠዋል። 


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic