ጋዛ ፤ የጋዛ ድብደባ ቀጥሏል | ዓለም | DW | 09.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ጋዛ ፤ የጋዛ ድብደባ ቀጥሏል

እስራኤል ዛሬ በጋዛ 30 ጊዜ ባካሄደችው የአየር ድብደባ 5 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተዘገበ ። በዚሁ በዛሬው እለት የሃማስ ደፈጣ ተዋጊዎችም 6 ጓዳ ሰራሽ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሰዋል።

የፍልስጤም የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዛሬው የአየር ድብደባ የኑሴይራት ሶስት መስጊዶች እንዳልነበሩ ሆነዋል ። እስራኤል እንዳስታወቀችው የተኩስ አቁሙ ከተጣሰበት ከትናንት ጠዋት አንስቶ እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ 100 ጊዜ የአየር ድብደባ ፈጽማለች ። ሃማስ ከትናንት አንስቶ እስከ ዛሬ ወደ እስራኤል የተኮሳቸው ሮኬቶች 44 ደርሰዋል ።ሃማስ ከአሁን በኋላ ከእስራኤል ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት እንደማያደርግ ዛሬ ዝቷል ።

የሃማስ ቃል አቀባይ ፋውዚ ባርሁም ሃማስ ወደ ኃላ እንደማይመለስና ትግሉንም እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ። የእስራኤልና የሃማስ የተኩስ አቁሙ ከተጣሰበት ከትናንት ወዲህ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 10 ሲደርስ የቆሰሉት ደግሞ ከ40 በላይ መሆናቸው ተዘግቧል ።ከአንድ ወር በላይ በዘለቀው የእስራኤል የጋዛ ድብደባ ቢያንስ 1900 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ወገን ደግሞ 67 ተድለዋል ከሐምሌ 1 2006 ዓም አንስቶ ጋዛ ውስጥ ከተገደሉት ፍልስጤማውያን መካከል 447 ህፃናትን ጨምሮ 1354 ቱ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል ።

ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤናሚን ኔታንያሁ ለመገናኛ ብዙኃን ሀገራቸው «ጠንካራ ርምጃ » እንደምትወስድ ከገለፁ ጀምሮ የእስራኤልን ርምጃ ያረጋገጡት ሌተናል ኮሎኔል ፒተር ለርነር የእስራኤልን የግዛት ደህንነት ለማረገጋገጥ የሃማስን እንቅስቃሴና መዋቅሮች ሁሉ መደብደባቸዉን እንደሚቀጥሉ ተናግረው ነበር። እስራኤል ከፍልስጤም ጋር ዘለቄታ ላለው የተኩስ አቁም ግብፅ ውስጥ የጀመረችው ድርድር እንደተቋረጠ ይገኛል።

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ