ጋዛ፥የለጋሾች ጉባኤና የክሊንተን ጉብኝት | ዓለም | DW | 03.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ጋዛ፥የለጋሾች ጉባኤና የክሊንተን ጉብኝት

ቃሉ ገቢር ሆኖ፥ ቅድመ-ግዴታዉ ተከብሮ፥ የይገባኛል ዉዝግቡ ተቃለል-ጋዛ ዳግም ትገነባለች ነዉ-ተስፋዉ።ዳግም የምትገነባዉ ዳግም ላለመፍርሷ ግን ምንም ዋስትና የለም

default

ጉባኤዉ

ትናንት ሸርም አል-ሼይኽ ግብፅ ተሰብስበዉ የነበሩት የለጋሽ ሐገሮች ባለሥልጣናት በእስራኤል ጦር ድብደባ የወደመዉን የፍልስጤሞች ግዛት ጋዛ ሰርጥን መልሶ ለመገንባት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት ቃል ገቡ።ከጉባኤተኞች መካካል አንዳዶቹ እንዳሉት ለእስራኤል-ፍልስጤሞች ግጭት፥ ዉዝግብ ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልተገኘ ገንዘብ ማዋጣቱ ወይም ዳግም ግንባታዉ ብቻዉን ዘላቂ ዉጤት አይኖረዉም።የዩናይትድ ስቴትሷ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን «ፖለቲካዊ» ለተባለዉ መፍትሔ ፍለጋ ከጉባኤዉ በሕዋላ ወደ እየሩሳሌም ሔደዋል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝሩን አጠናቅሮታል።

ገንዘቡ ብዙ ነዉ።የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳደር ከጠየቀዉ 2.8 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በጣም ብዙ ነዉ።አንዲት ስዑዲ አረቢያ ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች። የአዉሮጳ ሕብረት አራት መቶ አርባ ሚሊዮን ዩሮ፥ ጀርመን እንደ ሕብረቱ አባልነቷ ከምታዋጣቷ በተጨማሪ አንድ-መቶ ሐምሳ ሚሊዮን ዩሮ፥ ዩናይትድ ስቴትስ ለጋዛ ዳግም ግምባታ ሰወስት ሚሊዮን፥ ለሌላ ርዳታ ስድስት መቶ ሚሊዮን በድምሩ ዘጠኝ መቶ ሚሊን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።

ሁሉ በሁሉ አራት ቢሊዮን ተኩል ዶላር።ቃሉ ይከበር ይሆን ወይ? ላሁኑ-ያዉ ጥያቄ ነዉ።የጋዛ ሰርጥን ዳግም ለመገንባት የተዋጣዉ ገንዘብ የሚፈሰዉ ማሕሙድ አባስ በሚመሩት የፈትሕ መስተዳድር በኩል እንጂ ጋዛን በሚቆጣጠረዉ ሐማስ በኩል አለመሆኑ ደግሞ መዋጮዉ ለታለመለት ለጋዛ ሕዝብ እንዴት ይደርሳል የሚል ሌላ ጥያቄ አጭሯል።

የአሜሪካዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ለጥያቄዉ በርግጥ ትክክለኛ መልስ የላቸዉም። የመንግስታቸዉ መዋጮ የሚሰጠዉ ለአባስና ለተከታዮቻቸዉ መሆኑን ግን አልሸሸጉም።

ድምፅ

«እጅግ የሚያስፈልጉትን የሰብአዊ፥ የበጀት፥ የፀጥታና የመሰረተ ልማት አዉታሮችን ለማሟላት ከፍልስጤም ወዳጆቻችን ጋር ተባብረን እንሰራለን፥ ከፕሬዝዳት አባስና ከጠቅላይ ሚንስትር ፈያድ ጋር።ገንዘባችን ለማንና የት እንደሚዉል የምንቆጣጠርበትን የጋራ ሥልት ከፍልስጤም መስተዳድር ጋር ቀይሰናል።

ሐማስ ገንዘብ ሊደርሰዉ ቀርቶ በመዋጮዉ ጉባኤ ላይ እንኳን አልተጋበዘም።የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላይ ሳርኮዚ እንዳሉት ሐማስ በፖለቲካዊዉ ሒደት መሳተፍ ከፈለገ አድርግ የሚሉትን ማድረግ አለበት።

«ሐማስ እንደ ሕጋዊ ተሻራኪ ተቀባይነት ማግኘት ከፈለገ፥ የፍልስጤም መንግሥት ሊመሰረት የሚችልበት ብቸኛዉ ፖለቲካዊ መንገድ ከእስራኤል ጋር የሚደርግ ድርድር መሆኑን መቀበል አለበት።ሐማስ ተቀባይነት እንዲኖረዉ ከፈለገ ተቀባይነት ያለዉ አቋም መያዝ አለበት።»

እስራኤል ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት አሽባሪ የሚሉት ሐማስ አንንዳድ ያላቸዉ ተሳታፊዎች የገንዘብ መዋጮዉን ጉባኤ የሐማስን አቋም ለማስቀየር ወይም ለማሳጣት ተጠቅመዉበታል በማለት ወቅሷል።

Hillary Clinton bei Schimon Peres in Israel

ክሊንተን ከፔሬስ ጋር

ማሕሙድ አባስ እንደ ወይዘሮ ክሊንተን ሁሉ ቃል-የተገባዉ ገንዘብ በሙሉ ለሚመሩት መንግሥት ገቢ መሆን አለበት ባይ ናቸዉ።ሐማስ እንደሚለዉ ግን ገንዘቡ አንድም አዲስ ለሚቋቋመዉ ተጣማሪ መንግሥት አለያም ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚወከሉበት ልዩ ኮሚቴ መሰጠት አለበት።

ቃሉ ገቢር ሆኖ፥ ቅድመ-ግዴታዉ ተከብሮ፥ የይገባኛል ዉዝግቡ ተቃለል-ጋዛ ዳግም ትገነባለች ነዉ-ተስፋዉ።ዳግም የምትገነባዉ ዳግም ላለመፍርሷ ግን ምንም ዋስትና የለም።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዳግም ጥፋት ከወዲሁ መገታት አለበት ይላሉ።

ድምፅ

«ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ከተደረገዉ ካዲሱ የለጋሽ ሐገሮች ጉባኤ በሕዋላ ዳግም የሚገነባዉ ዳግም አይጠፋም የሚል ተስፋ አለን።በዚሕም ምክንያት የለጋሾቹ ጉባኤ ፍላጎትና እምነት ሙሉ በሙሉ ግቡን የሚመታዉ ዳግም ግንባታዉ በፖለቲካዊ ሒደት ሲታጀብ ነዉ-እንላለን።ፀጥታ ሲከበር፥ ግጭትና ሁከት ዳግም እንዳይቀሰስ ሲገታ ነዉ።»

የአሜሪካዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ዛሬ እየሩሳሌም የገቡት «ፖለቲካዉ ሒደት» የተሰኘዉን ለመጀመር ወይም ለመቀጠል ነዉ።ክሊንተን እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ባካባቢዉ በሚያደርጉት ጉብኝት እስከ ነገ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር ተራበተራ ይነጋገራሉ።ነገ ደግሞ ወደ ረመላሕ ሔደዉ ከፍልስጤም ባለሥልጣናት ጋር ይነጋገራሉ።

Saoub/Engelbrecht,Afp

Negash Mohammed

Tekle Yewhala

►◄