″ጋንዲ″ ስደተኞችን የሚረዳው ድርጅት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 16.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

"ጋንዲ" ስደተኞችን የሚረዳው ድርጅት

ከዛሬ አምስት ዓመት ተኩል ወዲህ ደግሞ ጋንዲ በሲና በረሃ በግብፅ በሊቢያና በቱኒዝያ እስር ቤቶች የሚሰቃዩ ባመዛኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን እየረዳ ነው ። ጋንዲ ሲና በረሃ የታገቱ በርካታ ስደተኞችን ከአፋኞቻቸው ነፃ ለማውጣት በቅቷል ።

ከምሥራቅ አፍሪቃ ድንበር አቋርጠው ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች በጉዞ ላይ ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ ችግሩን የቀመሱ ይናገራሉ ። በሱዳንና በግብፅ በረሃዎች በደላሎች ከሚንገላቱት በተጨማሪ በሊቢያ በግብፅና ና በቱኒዝያ እስር ቤቶች የሚሰቃዩት ስደተኞች ቁጥርም ቀላል አይደለም ። ዶክተር አልጋነሽ ፍስሃ ከዛሬ 41 ዓመት በፊት ከአስመራ ለትምህርት ወደ ኢጣልያ የመጡ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በሚላን ኢጣልያ የተከታተሉና እዚያው ኢጣልያ በትላላቅ ድርጅቶች ውስጥ በሃላፊነት የሰሩ አሁን ደግሞ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት የሚመሩ ኤርትራዊት ናቸው ። ድርጅታቸው በተለይ ሴቶች ህፃናትና ስደተኞችን በመርዳት ላይ ይገኛል ። ኢጣልያ ፣ ቋንቋ ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም ዓቀፍ ህግ ፤ህንድ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ህክምና ወይም AYURVEDA ተመርዋል ። ይበልጥ የሚታወቁት ግን ጋንዲ በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅታቸው ነው ። በሠላማዊ ትግል በሚታወቁት በህንዶች የነፃነት አባት እና የወላጅ አባታቸው ቅፅል ስም በሆነው ጋንዲ የተሰየመው ድርጅታቸው ተንከባባካቢ ያጡ የአፍሪቃ ህፃናትንንና ገቢ የሌላቸውን ሴቶች እንዲሁም ስደተኞችን የመርዳት ዓላማ ይዞ የተቋቋመው የዛሬ 10 ዓመት ነው ።

ዋና ፅህፈት ቤቱ አቢዣን ኮት ዲቯር ነው ። ዶክተር አልጋነሽ በአቢዣና አንድ ያሉትን በጎ አድራጎት በቤኒን በቶጎ ና በካሜሩንም ቀጥለው በ 2005 ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ሺመልባ ትግራይ የተጠለሉ ኤርትራውያን ስደተኞችን መርዳት ጀመሩ ።

« በ2006 በሽመልባ የመጀመሪያውን ወፍጮ ተከልን ።ልጆች ቢያንስ በቀን አንድ ኩባያ ወተት እንዲጠጡ 27 ላሞችን በመስጠት 1 ሺህ ህፃናትን መርዳት ችለናል ። የትምህርት መሣሪያዎችን መድሐኒትም ለግሰናል ። በኋላም በማይ-አይኒ ተመሳሳይ ሥራ ቀጠልን ። በማይ-አይኒ አሁን ሴቶች የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ አመቻችተናል እድሜያቸው ከ 3 እስከ 6 አመት ለሚደርስ 600 ህፃናት በቀን አንዴ ምግብ እናድላለን ። በእድሜ ለገፉ 150 ሰዎችም እርዳታ እንሰጣለን ። በማይቀብሪም ሴቶች ገቢ ማግኘት የሚያስችላቸውን ሥራ አስጀምረናል ።»

ከዛሬ 5 ዓመት ተኩል ወዲህ ደግሞ ጋንዲ በሲና በረሃ በግብፅ በሊቢያና በቱኒዝያ እስር ቤቶች የሚሰቃዩ ባመዛኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን እየረዳ ነው ። የዶክተር አልጋነሽ ድርጅት ሲና በረሃ የታገቱ በርካታ ስደተኞችን ከአፋኞቻቸው ነፃ ለማውጣት በቅቷል ። ይህም ከሚረኩበት ሥራቸው አንዱ ነው ።

« ምንም እንኳን ከባድ ቢሆንም ደስተኛ ነኝ ። በተለይ በግብፅ ያገኘነው ውጤት በጣም ያስደስተኛል ። ምንም ገንዘብ ሳንከፍል በበድዊኖች የተያዙ 500 ሰዎችን ነፃ አውጥተናል ። 1500 የሚሆኑትን ደግሞ ከግብፅ እስር ቤቶች አስለቅቀን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ አድርገናል ። »

ዶክተር አልጋነሽ እንደሚሉት በበደዊን በሙሉ ስደተኞችን አያግቱም ። ብዙሃኑ ሰዎች መታገታቸውን ይቃወማሉ ። የድርጊቱ ፈፃሚዎች ጥቂቶች ናቸው ። ጋንዲ ስደተኞቹን ከአጋቾቻቸው ከበድዊኖች ነፃ ሊያወጣ የቻለውም ራሳቸው በደዊኖች ባደረጉለት ትብብር ነው ።

« አንዳንድ ዘዴዎች አሉ ። እኔ ከ 3 አመት ተኩል በላይ በቅርብ የማውቃቸው አንዳንድ በደዊኖች አሉ ። የሚኖሩት ሲና ነው እነርሱ ከኛ ጋር ይሰራሉ ። ምን ማድረግ እንዳለብን ና እንዴት ማከናወንም እንዳለብን እንዴትም ሊሳክልን እንደሚችል ይነግሩናል ። በተረፈ እንዴት እንደምንሰራ ዝርዝሩን ላብራራልሽ አልችልም »

በሱዳንም ሆነ በግብፅ በረሃ ሰዎች እንደሚታገቱ ጉዞውም አደገኛ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚነገር ቢሆንም አሁንም ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ድንበር የሚያቋርጡ ኤርትራውያን ቁጥር አልቀነሰም ። ዶክተር አልጋነሽ ምክንያቱን በኤርትራ ካለው ችግር ጋር ያያዙታል ።

« ኤርትራ ያለችበት ሁኔታ ይታወቃል ። አጠቃላይ ጭቆና አለ ፣ ነፃነት የለም ፣ ትምህርትም የለም የጤና አገልግሎት የለም በቂ ምግብም የለም ። ስለዚህ ሰዎች ሥራ ፍለጋ ይወጣሉ ። ወደ ሱዳን ጁባ ለመሄድ ወይም የትም ይሁን የት አገራቸውን ጥለው የሚሄዱበትን መንገድ ይፈልጋሉ ። ። »

ሆኖም ሁሉም ያሰቡበት አይደርሱም ። ብዙዎቹ በጉዞ ላይ የደላሎች ና የአጋቾች ሰለባ ሆነው ለሞት ለስቃይና እንግልትይዳረጋሉ ።

« ከዛሬ 3 ና 2 ዓመት ተኩል በፊት ሰዎች ወደ እስራኤል ለመሄድ ከድንበር አሻጋሪዎች ጋር ይዋዋሉ ነበር ። ማለትም ገንዘብ ከፍለዋቸው እስራኤል እንዲያስገቡዋቸው ። አሁን ግን ሁኔታው ተለውጧል ። አጋቾቹ ኤርትራ ውስጥም አሉ ። ሰዎቹን እስከ ሱዳን ድንበር ወስደው ለሱዳን የፀጥታ ኃይሎች ያስረክቧቸዋል ። ሱዳኖቹ ደግሞ እዚያ ላሉት ራሻይዳዎች ይሰጧቸዋል ። ራሻይዳዎቹ ደግሞ ግብፅ ላሉት በድዊኖች ይሸጧቸዋል ። »

ስደተኞቹን የሚያግቱት ፣ ውጭ የሚገኙ የታጋቾች ዘመዶች ጠቀም ያለ ገንዘብ ካልከፈሉ እንደሚገደሉ አለያም የሰውነት አካላቶቻቸውን አንደሚያወጡ በማስፈራራት ይዝቱባቸዋል ። በመካከሉ የሚገደሉ ለህመም የሚዳረጉ በርካቶች መሆናቸው ይሰማል ። እነዚህን በአጋቾች የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ጋንዲ ለመንግሥታት ቢያሳውቅም ምንም አልፈየዱም ይላሉ ዶክተር አልጋነሽ ።

« ለሚመለከታቸው መንግሥታት ለህዝቡ ጉዳዩን ስናስረዳ ወንጀሉን እንዲያስቆሙ ስናሳስብ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል ። የሱዳን የሊቢያ የግብፅም ሆነ የእስራኤል መንግሥታት አንድም እርምጃ አልወሰዱም ። እስራኤል አሁን ድንበሯን ዘግታለች ። ሃገርዋ የገቡትንም ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር ልታባርር ነው ። ማን እንደሆነ የማይታወቀው ሃገር ከእስራኤል ገንዘብ ተሰጥቶት ስደተኞቹን ይቀበላል ። አንድ የማይገባኝ በሱዳን ወንጀሉ አለመቆሙ ነው ።ሱዳን በህገ ወጥ ድንበር አሻጋሪዎች ላይ እርምጃ እየወሰደች ነው ሆኖም የሃገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች አሁንም በዚህ ተግባር ተሳታፊ ናቸው ። በግብፅም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው ። »

ሆኖም ይላሉ ዶክተር አልጋነሽ ስደተኞቹ የሚገኙባቸው ሃገሮች ለችግሮችን መግትሄ መፈለግ ቢገባቸውም በዋነኛነት ሊተኮርበት የሚገባው ሰዉን ለስደት የሚዳርጉ ችግሮችን ማቃለሉ ነው ።

« በኤርትራ በመጀመሪያ ወጣቱ እድሜውን በሙሉ በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት እንዲያጠፋ ከማድረግ ይልቅ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት እንዲማር ማድረግ ነው ። ይህ ምን ዓይነት ህይወት ነው ? ህይወት የላቸውም ተስፋ የላቸውም ። የህይወታቸው የትምህርታቸው ጉዳይ እንዴት ነው የሚታየው ። የጤናቸው ጉዳይስ ? የመናገር ነፃነታቸውስ ? በኤርትራ ይህ ሁሉ መጀመሪያ መፍትሄ ማግኘት አለበት ።»

በቅርቡ ከ 400 በላይ የሚሆኑ የሶማሊያ ና የኤርትራ ስደተኞች ማልታ ገብተዋል ።በስደተኞች የተጨናነቀችው ማልታም እነዚህን ስደተኞች ጠርዛ በአውሮፕላን ወደ መጡበት ልትመልስ ነበር ። ሆኖም የአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት የማልታን እቅድ የሚቃወም ውሳኔ በማሳለፉ ስደተኞቹ እዚያው እንዲቆዩ ተደርጓል ። ማልታ ሁለት ጊዜ የሄዱት ዶክተር አልጋነሽ ማልታም ይሁን ሆነ የኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ የሚሄዱ ስደተኞች እጣ አሳዛኝ ነው ይላሉ ። በማጎሪያ ካምፖች እንዲቆዩ የሚደረጉት እነዚህ ስደተኞች መሥራትም ሆነ መማር አይችሉም ።

« ማልታ ሲደርሱ እስር ቤት ይገባሉ ። ምንም አያደርጉላቸውም ። አያስተምሩዋቸውም ቤት አይሰጧቸውም ምንም እርዳታ አያደርጉላቸውም ። በኢጣልያም ተመሳሳይ ነው ። በኢጣልያ ለ 3 ወር እስር ቤት ካቆዩዋቸው በኋላ ኢጣልያ መቆየት የሚችሉበት ፈቃድ ይሰጧቸዋል ። እስቲ ኢጣልያ ውስጥ ያለ ቤት ያለ አንዳች ድጋፍ መኖር ይቻላል ? ስደተኞቹ ሲቸግራቸው ወደ ስዊድን ወደ ኖርዌይ ለመሄድ ይሞክራሉ ። ሆኖም በአሻራቸው ይዘው ወደ መጡበት ይመልሷቸዋል ። ይህ በጣም የሚያሳዝን አዙሪት ነው ። »

Destination Europe – Kapitel-Nr. 4

እንደ ዶክተር አልጋነሽ ይህ በአውሮፓ ህብረት ደረጃ መፈታት ነበረበት ። ወጣት ዜጎች በየባህሩና በየበረሃው ሲረግፉና ሲሰቃዩ የአፍሪቃ ህብረትም ዝም ብሎ መመልከት አልነበረበትም ። ህብረቱ ወይም ችግሩን መረዳት አይፈልግም አለያም አያውቀውም ይላሉ ።

ዶክተር አልጋነሽ ስደተኞችን በመርዳት ሂደት ውስጥ ጥቃት ደርሶባቸዋል ከመካከላቸው ቱኒዝያና ግብፅ ውስጥ የደረሳባቸውን በምሳሌነት ያነሳሉ።

«በ2005 ዓም ቱኒስያ ውስጥ ስደተኞችን ደብድበው ለ 3ቀናት ህፃናት ምግብ እንዳያገኙ ከልክለዋቸው ምግብ ለመስጠት ሄጄ ነበር ። ለህፃናቱ ወተትና ዳቦ ስሰጥ ደብድበውኝ ቀኝ እጄን ሰብረውት ነበር ። ባለፈው ዓመትም ሊቢያ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞኛል ። ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከእስር ቤት ለማስወጣት ስሞክር 5 ሊቢያዎች ግራ እጄን ሰብረውኛል ። ምክንያቱም ጥቁር አፍሪቃውያን ደግሞ ለደጋፊ ተገዝተው ተዋግተዋል በሚል ጥቃት ያደርሳሉ ። በድዊኖቹም ቢሆኑ ካገኙኝ እንደሚገድሉኝ ይዝታሉ »

ዶክተር አልጋነሽ አውሮፓውያን ሸክሙን በጋራ መጋራት እንደሚገባቸው ያሳስባሉ

« የስደተኛው ሸክም በማልታ በኢጣልያና በግሪክ ላይ ብቻ መሆን የለበትም ። ሌሎች የአውሮፓ ሃገራትም ስደተኞችን ሊቀበሉ ይገባል ። ምክንያቱም ማልታ ኢጣልያም ሆነ ግሪክ ከአቅማቸው በላይ ነው ። ማልታ ትንሽ ደሴት ናት ። ግሪክም ያለው ቢሆን እጅግ አስከፊ የስደተኞች መጠለያ ነው ። ሌሎቹ ሃገራትም በራቸውን መክፈት አለባቸው ። ለስደተኞች የያዙትን ኮታ ከፍ ማድረግ አለባቸው ።»

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic