ጋቦ፡ ኢኳቶርያል ጊኒ እና የሰብዓዊ መብት ይዞታቸው | አፍሪቃ | DW | 21.01.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ጋቦ፡ ኢኳቶርያል ጊኒ እና የሰብዓዊ መብት ይዞታቸው

የአፍሪቃ ሀገሮች የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ በዛሬው ዕለት ተጀምሮዋል። የአስራ ስድስት አፍሪቃውያት ሀገሮች የእግር ኳስ ቡድኖች ከዛሬ ጀምሮ እአአ እስከ ፊታችን የካቲት ስድስት ድረስ ለዋንጫ ይወዳደራሉ።

default

የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ 2012

አስተናጋጆቹ ሀገሮች ኢኳቶርያል ጊኒ እና ጋቡ ግጥሚያውን የተሳካ ለማድረግ እጅግ በብዙ ሚልየን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተዋል። ይሁንና፡ የዶይቸ ቬለለ ባልደረባ ዲርከ ከፕ እንደምትለው፡ በነዚህ ሁለት ሥርዓተ ዴሞክራሲ በተጓደላቸው ምዕራብ አፍሪቃውያቱ ሀገሮች ውስጥ የሰብዓዊ መብቱ ይዞታ እጅግ አሳሳቢ ነው።

እአአ በ 1936 ዓም የዓለም ኦሊምፒክ ጨዋታ በናዚ ትመራ በነበረችው ጀርመን፡ እአአ በ1978 ዓም በየዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በወታደራዊ አመራር ሥር በነበረችው አርጀንቲንያ፡ እአአ በ 2008 ዓም የዓለም ኦሊምፒክ ጨዋታ በቻይና ተካሂደዋል። የሰብዓዊ መብትን እንደሚረግጡ እየታወቀ ዓበይት የስፖርት ውድድሮች የተካሄዱባቸው ሀገሮች ስም ዝርዝር ቢቆጠር እጅግ ብዙ ነው። ለምሳሌ በ1978ዓም በላቲን አሜሪካዊቱ ሀገር አርጀንቲንያ መዲና ቡየነስ አይረስ የመጨረሻው የዋንጫ ውድድር ከተካሄደበት ስቴድየም ጥቂት ኪሎሜትር ራቅ ብሎ በቁም ሥቅል ማሳያው ተግባር በዓለም እጅግ አስከፊው መሆኑ የተነገረለት ማዕከል መገኘቱ ወይም በ 2008 ዓም በቤይዢንግ የኦሊምፒክ ጨዋታ ወቅት የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዳይታዩ መደረጋቸው ይታወሳል።

Sport Fußball African Nations Cup Bata Stadion

የኢኳቶርያል ጊኒ የባታ ስቴድየም


አሁን ደግሞ በአፍሪቃ ማዕከል በፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸው እና በሰብዓዊ መብት ረገጣ ተግባራቸው በሚታወቁት ጋቦ እና ኢኳቶርያል ጊኒ ውስጥ በዛሬው ዕለት የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ተጀምሮዋል። ፕሬዚደንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ሰባት መቶ ሺህ ነዋሪ ያላትን ኢኳቶርያል ጊኒን እአአ ከ 1979ዓም ወዲህ በጠንካራ አገዛዝ በመምራት ላይ ይገኛሉ። ኦቢያንግ በ 2009 ዓም በተካኬደ አከራካሪ ፕሬዚደንታዊ ምርጫም ዘጠና አምስት ከመቶ የመራጩን ድምፅ አገኘሁ በማለት አመራራቸውን ቀጥለዋል። በለንደን የሚገኘው የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢኳቶርያል ጊኒ ጉዳይ ተመራማሪ ማሪዝ ካስቶር የፕሬዚደንት ኦቢያንግ አገዛዝ አስከፊ መሆኑን ገልጸዋል።
« በኢኳቶርያል ጊኒ የሰብዓዊ መብቱ ይዞታ ሁሌም ቢሆን መጥፎ እና በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚገኘው። የተቃዋሚ ወገኖችን መጨቆን፡ የቁም ሥቅል ፍዳ ማሳየት፡ የተቃዋሚ ወገኖችን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውን ካለፍርድ አስሮ ፍትሃዊ ያልሆነ ችሎት ማካሄድ ፡ የሞት ቅጣት መበየን፡ እንዲሁም፡ አስተያየት በነጻ የመግለፅ፡ የመሰብሰብ እና ባጠቃላይ የፕሬስ ነፃነትን ማፈን የተለመደ አሰራር ነው።»

Äquatorialguinea Präsident Teodoro Obiang Nguema neu

የኢኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ


ይሁንና፡ በመንግሥቱ ክትትል ያላረፈበትም ግለሰብ ቢሆን፡ ከሰሀራ በስተደቡብ ከሚገኙት ሀገሮች መካከል በነዳጅ ዘይት አምራችነት የሦስተኛነቱን ቦታ በያዘችው በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው ሀገሩ ውስጥ የደላ ኑሮ የለውም። ምክንያቱም፡ ፕሬዚደንቱ እና ቤተሰባቸው ከነደጋፊዎቻቸው ከሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት የሚገኘውን ገቢ ሀገሪቱን ለማሻሻያ ሳይሆን ለራሳቸው መበልፀጊያ ነው እንደተጠቀሙበት በፓሪስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፡ የአፍሪቃ ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍሎረንስ ጊል አስረድተዋል።
« ምንም እንኳን ኢኳቶርያል ጊኒ በተፈጥሮ ሀብት ብትታደልም፡ ሕዝቧ አሁንም በፍፁም፡ ተቀባይነትን ባላገኘ የከፋ ድህነት ውስጥ ነው የሚኖረው። የዚችው ንዑስ አፍሪቃዊት ሀገር የገንዘብ አቅም ሲታይ ግን፡ የትምህርቱ እና የጤና ጥበቃው ዘርፍ አሁን የሚገኝበት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መገኘቱን ለማመን እጅግ ያዳግታል። »
ሌላዋ የአፍሪቃን የእግር ኳስ ዋንጫን የምታስተናግደዋ ጋቦ ሁኔታም ግን ከኢኳቶርያል ጊኒ እምብዛም የተለየ አይደለም፡ እንደ ፍሎረንስ ጊል አመለካከት።
« የመንግሥት ሥልጣን ቦታ የማያማልላቸው የተቃዋሚ ወይም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይጨቆናሉ። የሲቭሉ ማህበረሰብ አሁንም በጣም ደካማ ነው። ይሁን እንጂ ፡ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይ ሙስናን እና በመንግሥቱ አሠራር ላይ የተጋደለውን ግልፅነት በመታገሉ ረገድ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ይገኛል። »
በጋቦ የአንድ የሲቪል ማህበረሰብ አባል የሆኑት ሚስተር ማርክ ኦና ከሀገራቸው የተፈጥሮ ሀብት በሚገኘው ገቢ አጠቃቀም ላይ ተጨማሪ ግልፅነት እንዲኖር ከብዙ ዓመታት ወዲህ ይታገላሉ። ጋቦ አሁን የአፍሪቃን የእግር ኳስ ዋንጫ ለማስተናገድ ስትል ስቴድየሞችዋን ለማሳደስ በብዙ ሚልየን የሚቆጠር ገንዘብ ማፍሰሷ ትክክለኛ እንዳልሆነ ማርክ ኦና ይናገራሉ፤ ምክንያቱም ይህ ከድሀው ሕዝብ አፍ ተነጥቆ የተወሰደ ነውና። እንደ ኦና ቢሆን ኖር፡ በጋቦ በሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ረገጣ የተነሳ ይህችው ሀገር ይህንን ዓቢይ የስፖርት ውድድር ማስተናገድ ባልተገባት ነበር።

Gabun Fussballfans

የጋቦ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች


« የዋንጫው ግጥሚያ በሀገራቸው መደረጉን በደስታ ቢቀበሉም፡ ተማሪዎች በአደባባይ ተቃውሞ እያካሄዱ ነው። ይኸው ተቃውሞአቸውም በፖሊስ የኃይል ርምጃ ተደምስሶዋል። ተማሪዎቹ የተሻለ የትምህርት ሁኔታ እና ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ የተቋረጠው ከመንግሥት የሚያገኙት የኪስ ገንዘብ እንዲሰጣችው በመጠየቃቸው ዩኒቨርሲቲው ተዘግቶዋል። በዚህ ፈንታ፡ የጋቡን መንግሥት በብዙ የከተማይቱ አካባቢዎች የውኃ እጥረት ቢኖርምና ተማሪዎቹ ተቃውሞአቸውን ቢቀጥሉም፡ ለዋንጫው ግጥሚያ ዝግጅት ማደራጂያ 600 ሚልየን ዩሮ አውጥቶዋል። የጦር ኃይሉ በከተማይቱ ባካሄዱት ዓመፅ ወቅት ሰዎች ታስረዋል ወይም ተገድለዋል። አንድ ሀገር ይህን የመሰለ ዓለም አቀፍ ግጥሚያ የምታስተናግድበትን ዕድል በመስጠቱ ውሳኔ ላይ መልካም አስተዳደር መሟላት ያለበት አንዱ ቅድመ ግዴታ ሊሆን አይገባም? »
እአአ ባለፈው ግንቦት 2011ዓም ማርክ ኦና እና ሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ታጋዮች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያን እንዲያስተናግዱ ተመረጡት ጋቦ እና ኢኳቶርያል ጊኒ ውስጥ የተጓደለውን የመልካም አስተዳደርን ለማሳወቅ ለዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽንና ለአፍሪቃ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፉት ደብዳቤ ይኸው ውሳኔ እንዲሻር ጠይቀው ነበር። ግን ለደብዳቤአቸው መልስ ሳይገኙ ግጥሚያው ዛሬ ተጀምሮዋል።

ዲርከ ከፕ

አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 21.01.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13nbY
 • ቀን 21.01.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13nbY