ጋምቢያ ከምርጫዉ ደስታ ማግሥት | አፍሪቃ | DW | 20.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ጋምቢያ ከምርጫዉ ደስታ ማግሥት

አፍሪቃ ዉስጥ እንዲህ ያለ ተስፋ የታየበት ምርጫ ብዙም አልታየም። አዳማ ባሮዉ የጋምቢያ ፕሬዝደንትነትን መንበረ ሥልጣን በሕዝብ ምርጫ ከተረከቡ ስድስት ወር ሆናቸዉ። ብዙዎች የእሳቸዉ ድል ለሀገራቸዉ ለጋምቢያ የአዲስ ዘመን መባቻ ይሆናል በሚል ተስፋ አድርገዉ ጠብቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:34

የምርጫዉ ድል ደስታና እና የጋምቢያዉያን ተስፋ፤

ባለፈዉ ታኅሳስ ወር በሺዎች የሚገመቱ ጋምቢያዉያን እጅግም በማይታወቁት የንግድ ሰዉ የምርጫ ድላቸዉ በዋና ከተማ ባጁል ጎዳናዎች ላይ በመዉጣት ደስታቸዋን ገልጸዋል። መኪናዎች በአጀብ ተሰልፈዉ በመላ ከተማዋ ተመዋል፤ ብዙዎች ጎዳናዉ ላይ በጋራ እየደነሱ የአዳማ ባሮዉን ስም ጮክ ብለዉ ሲጠሩ ተደምጠዋል። ምርጫዉ የአምባገነኑ የያህያ ጃሜ ፕሬዝደንትነት አክትሞ ወደተሻለ የወደፊት ሕይወት የሚያሸጋግር የዘመንን መለያ አንዳች ምልክት እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል። አሁን አዳማ ባሮዉ የጋምቢያ ፕሬዝደንት ከሆኑ ስድስት ወራት ተቆጠሩ። ያ ሁሉ ደስታ አሁን ብዥ ብዥ ማለት ጀምሯል። አዲሱ ፕሬዝደንት ከላይ ብዙ ነገሮችን ለመለወጥ ይፈልጋሉ። ለጋምቢያዉያን ነፃነት፤ ዴሞክራሲ፤ እድገት እና ንልፅግናን ለማምጣት ቃል ገብተዋል። እስካሁን ግን ቃል ከገቡት አንዳች የተደረገ ነገር የለም። አዲሲቱ ጋምቢያ አሁን ገና ከሩቅ ናት። አልተደረሰባትም።

«ልማትን በተመለከተ ያን ያህል የተሠራ ነገር ያለ አይመስለኝም። ቢያንስ ሕዝብ እንኳ እንዲያስተዉለዉ ማለት ነዉ፤ ይህን ነዉ መንግሥት ማድረግ የሚፈልገዉ። ነገር ግን ሁሉም ነገር አይንቀሳቀስም። ወደ የት እንደሚያመራ እንኳ የማይታወቅ እጅግ የበዛ ትርምስ እና ጭለማ ነዉ ያለዉ። ጃሜህ የሉም፤ ከስልጣን እንዲወርዱ ፈልገን ነበር ለቀዋል። እንደሚመስለኝ መንግሥት በሀገራችን ለተደረገዉ ነገር ሁሉ እሳቸዉን ተጠያቂ ማድረግ የለበትም፤ ሆኖም ግን ከእነዚያ ችግሮች ተምረን፤ ችግሮቹን ለመፍትሄነት የምንጠቀምበትን ስልት መፈለግ ይኖርበታል።»

ትላለች የጋምቢያ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ተማሪዋ ማርያማ ዳንሶ። እንዲያም ሆኖ በዚህ ላይ የጋምቢያዉያን  አስተያየት የተለያየ ነዉ።

አንዳንዶች የማርያማ ዳንሶን ሃሳብ ይጋራሉ፤ ሌሎች ደግሞ በያህያ ጃሜህ ዘመነ ስልጣን ላለፉት 22 ዓመታት የተፈፀመዉን ንቅዘት እና የአስተዳደር ብልሽት ለማስተካከል አቅም እና ጊዜ ይጠይቃል ሲሉ ይሞግታሉ። ላሚን ሳይዲካን አንዱ ነዉ።

«እስካሁን ብዙ ነገሮች እንደተሳኩ ይሰማኛል። እናስበዉ የነበረዉ አሁን የለም እናም በነፃነት ሃሳባችንን መግለጽ ጀምረናል። ለመጀመሪያ ጊዜም የዲሞክራሲ መርሆዎች ሲከበሩም እያየን ነዉ።»

ባሮዉ አስቸጋሪ ዉርስ ነዉ የጠበቃቸዉ። ከእሳቸዉ አስቀድመዉ የነበሩት ፕሬዝደንት ጃሜህ ሀገሪቱን አጎሳቁለዋታል። ተቃዋሚዎቻቸዉን ሲጨቁኑ፤ የሚተቿቸዉን ዲፕሎማቶች ከሀገር ሲያባርሩ፤ አገዛዛቸዉን የሚተቹትንም ደብዛ ሲያጠፉ ከርመዋል። ጋዜጠኞች ይታሰሩ ወይም ተመልካች በሌለበት ቀን ይገደሉ ነበር። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ቢሆን ፈላጭ ቆራጩ መሪ የማያደርጉት አልነበረም። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም በተካሄደዉ ምርጫ 79 በመቶ ድምጽ አገኙ፤ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ደግሞ 39,6 በመቶ ያገኙ። አዳማ ባሮዉ ግልጽ በሆነ ልዩነት በ46,3 በመቶ ድምጽ አሸነፉ።

በመጀመሪያ ጃሜህ ተቃዋሚዎቻቸዉንና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን ባስገረመ መልኩ መሸነፋቸዉን በይፋ ተቀበሉ። ከሳምንት በኋላ ሃሳባቸዉን ቀየሩ፤ በምጫዉ ያሸነፉት ባሮዉ ወደ ሴኔጋል ተሰደዱ። የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ትብብር ኤኮዋስ ጃሜህን በጉልበት ከተቀመጡበት መንበር ለማስወገድ ሠራዊት ላከ። በጥር ወር ማለቂያ ገደማ ጃሜህ ሀገር ለቀዉ ለመሰደድ እጅ ሰጡ። ከስደታቸዉ አስቀድሞዉ ግን ወትሮም ከደቀቀዉ የሀገሪቱ አቅም ላይ 10 ሚሊየን ዩሮ መንትፈዉ መሄዳቸዉን የጋምቢያ ማዕከላዊ ባንክ ይፋ አድርጓል። የኤኮኖሚ አማካሪዉ ናያንግ ናጂ፤ ቃል ገብቶ ስልጣን የተረከበዉ የባሮዉ መንግሥት እንዲህ ያለ የፋይናንስ ይዞታን መዉረሱ አቅሙን እንደሚፈታተን ነዉ የሚናገሩት፤

«የባሮዉ ትልቁ ፈተና ጠንካራ የኤኮኖሚ አስተዳደር መገንባት ነዉ፤ ይህ ጠንካራ የኤኮኖሚ አስተዳደር ደግሞ የመንግሥት የተቋማት መዋቅር ማስተካከል፤ የኤኮኖሚ ተቋማትን እና የኃይል ተቋማትን አጠናክሮ ተፅዕኖ መፍጠር ይጠበቅበታል። ይህ ደግሞ ጋምቢያን ሥራዎች በቅደም ተከተል የሚሠሩባት እና የኃይል አጠቃቀምም ገደብ የሚያገኝባት ሀገር ያደርጋታል።» 

ጋምቢያ አሁን ብዙም የተለወጠ ነገር አይታይባትም። የፕረስ ነፃነት በእርግጥ ተከብሯል። የሀገር ዉስጥ የፀጥታዉ ጉዳይ ግን አሳሳቢ ነዉ። የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች እንቅስቃሴ ስጋት ፈጥሯል፤ በመሣሪያ የታገዘ አሰሳ በተደጋጋሚ ይካሄዳል። ታዛቢዎች አሁን ለሀገሪቱ እንደአደጋ የሚያዩት ልምድ የሌላቸዉ ሰዎች ስልጣን መያዛቸዉን ነዉ። ባሮዉ ከንግድ ሰዉነታቸዉ የዘለለ የመንግሥት ፖለቲካዊ አስተዳደር እዉቀታቸዉ ዉሱን ነዉ። እሳቸዉ እና አስተዳደራቸዉ ነገሮችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚታገሉበት በዚህ ሰዓት በርካታ የጋምቢያ ዜጎች በምርጫ ወቅት የገቡላቸዉን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ትዕግሥት አጥተዉ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እና ሥራ ፈላጊዉ ብዙ ነዉ። አብዛኛዉ ዜጋ ወጣት በሆነባት ጋምቢያ ብዙሃኑ በቀን በአንድ ዩሮ ኑሮ ይገፋባታል።

ሸዋዬ ለገሠ/ ጉዌንዶሊን ሂልሰ

አዜብ ታደሰ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች