ጋምቢያ እና አዲሱ ፕሬዚደንቷ | አፍሪቃ | DW | 28.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ጋምቢያ እና አዲሱ ፕሬዚደንቷ

በጋምቢያ ባለፈው ታህሳስ አንድ፣ 2016 በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ያሸነፉት አዳማ ባሮዎ ከትናንት በስቲያ ወደ ሃገራቸው ተመለሱ። ያለፉት ሁለት ወራት ገደማን በጎረቤት ሴኔጋል መዲና ዳካር የቆዩትና ከጥቂት ቀናት በፊት በዚያው ቃለ መሃላ የፈፀሙት ባሮውም ከብዙ መጠበቅ በኋላ ከሕዝባቸው ጋር መቀላቀል በመቻላቸው መደሰታቸውን በትዊተር ገልጸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:07

አዳማ ባሮው

ባሮው በተመድ  የምዕራብ አፍሪቃ እና የሳህል አካባቢ ሃገራት ልዩ ተጠሪ መሀመድ ኢብን ቻምባስ ታጅበው መዲናይቱ ባንጁል አየር ማረፊያ ሲገቡ ሕዝቡ ደማቅ አቀባበበል ነበር ያደረገላቸው። ሃገሪቱን ላለፉት 22 ዓመታት የመሩት እና በምርጫ ቢሸነፉም ስልጣን ለመልቀቅ አሻፈረን ብለው የቆዩት የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜ በምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ «ኤኮዋስ» ግፊት  ባለፈው የሳምንት መጨረሻ ወደ ኢኳቶርያል ጊኒ በተሰደዱበት ድርጊት በሃገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብ ሊያበቃ ችሏል።
አዳማ ባሮው ያህያ ጃሜህ ጋምቢያን እንደለቀቁ ወዲያው ወደ ባንጁል ያልተመለሱበት ጥያቄ ብዙዎችን ሲያነጋግር ሰንብቷል። ጊዜው ረጅም እንዳልነበረ የገለጹት የአዲሱ ፕሬዚደንት ቃል አቀባይ ሃሊፋ ሳላህ ባሮው ከመመለሳቸው በፊት ከ«ኤኮዋስ» ተወካዮች ጋር የበሚመለሱበት ሂደት ላይ መወያየት እንደነበረባቸው አስረድተዋል። በሴኔጋል የሚገኘው የጀርመናውያኑ የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ቶማስ ፎልክ ውይይቱ በተለይ በጋምቢያ የፀጥታ ጥበቃ ጉዳይ ላይ ያተኮረ እንደነበረ ገልጸዋል።  
እስከጥቂት ጊዜ በፊት ድረስ የጋምቢያ የጦር ኃይል አባላትን እና የያጅያ ጃሜህን ደጋፊዎች በጠቅላላ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ አሸናፊ አዳማ ባሮው መሆናቸውን የማሳመን ስራ መካሄድ ነበረበት። ይህ ቀላል አልነበረም። ባሮው ጃሜህን 50,000 የመራጭ ድምፅ በመብለጥ ነበር ሳይታሰብ ያሸነፉት። ጃሜህ ሃገሪቱን ለቀው እንደወጡ ቀደም ሲል ደም መፋሰስ እንዳይኖር በመስጋት ወደጎረቤት ሃገር ጌደው የነበሩ ጋምቢያውያን ወዲያውኑ መመለስ ጀምረዋል።

በአዳማ ባሮው ዘመነ ስልጣን በጋምቢያ እና በሴኔጋል መካከል የተሻሻለ ግንኙነት እንደሚፈጠር የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ቶማስ ፎልክ ይገምታሉ።  
«  እንደሚታወቀው፣ በጋምቢያ ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የታየበት አምባገነናዊ አገዛዝ አሁን አብቅቷል፣ ይኸው የሃገሪቱ ሁኔታ ከየሁለቱ የጋምቢያ ዜጎች አንዱ ሃገሩን እየለቀቀ እንዲወጣ አድርጓል። በጋምቢያ አንፃር ጎረቤት ሴኔጋል በምዕራብ አፍሪቃ  መረጋጋት የሰፈነባት ሃገር ናት። የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በማጠናከር ላይ ያለች በአርአያነት የምትጠቀስ ሃገር ናት። »
የቀድሞው ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜህ እና የሴኔጋል አቻቸው ማኪ ሳል ግንኙነት ችግር አላጣውም ነበር። በተለይ በሴኔጋል እጎአ ከ1980 ዓም ወዲህ በካዛሞንስ አካባቢ የቀጠለው ውዝግብ ለጋምቢያ እና ለሴኔጋል ግንኙነት መሻከር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። በዚሁ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት ዓማፅያን  ለግዛቱ ነፃነት በመታገል ላይ ይገኛሉ። ያካባቢውን ሁኔታ የሚከታተሉ  ብዙ ታዛቢዎች የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚደንት ጃሜህም እነዚህን የሴኔጋል ዓማፅያንን የጦር መሳሪያ ያስታጥቁ ነበር ሲሉ ይወቅሳሉ፣ ይሁን እንጂ፣  ይህ ወቀሳቸው በማስረጃ መረጋገጡን የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ተቋም ባልደረባ ቶማስ ፎልክ ተጠራጥረውታል።  
የፕሬዚደንት አዳማ ባሮው ቃል አቀባይ ሃሊፋ ሳላህ  ከጋምቢያ ጋር ለሚዋሰነው የካዛሞንስ አካባቢ ውዝግብ በቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚደንት ጃሜህ  ዘመነ ስልጣን ሊጠናከር መቻሉን ቢያረጋግጡም፣ የጃሜህ ጣልቃ መግባታ አለመግባት ችግሩን ለማብቃት የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ እንደማያሰናክል ገልጸዋል።
« የካዛሞንስን ውዝግብ ለማብቃት ሀቀኛ  ጥረት ቢደረግ ኖር፣ ጃሜህ በዚሁ መፍትሔ የማፈላለግ ጥረት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ ፈለጉ አልፈለጉ፣ ችግሩ እስከዛሬ መፍትሔ ማግኘት በቻለ ነበር። »


የካዛሞንስ አካባቢ ዋነኛ የሴኔጋል እህል አምራች አካባቢ ቢሆንም፣ ያካባቢው ሕዝብ ልማቱን በተመለከተ ከማዕከላዩ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት አላገኘም በሚል ያጅያ ጃሜህ ረድተዋቸዋል የሚባሉት ዓማፅያን ግዛቱ የራሱን ነፃ መንግሥት እንዲያቋቋም ዛሬም ትግላቸውን ቀጥለዋል።  በሌላ በኩል ደግሞ ንዑሷ ሃገር ጋምቢያም ከትልቋ ጎረቤቷ ሴኔጋል በእድገትዋ ሂደት ላይ ጫና እንዳረፈባት በቅሬታ ትገልጻለች።  ይሁንና፣ የ«ኤኮዋስ» ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማርሴል አላ ሱዛ ሴኔጋል ጋምቢያ እንደምትለው፣ ያን ያህል ተፅዕኖ ታሳርፋለች ብለው አያምኑም። 

በጋምቢያ ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ በኋላ የተፈጠረውን ውዝግብ በማብቃቱ ጥረት ላይ ትልቋ ጎረቤት ሴኔጋል ከፍተኛ ድርሻ ነበራት።  ሽንፈታቸውን ተቀብለው የነበሩት እና የኋላ ኋላ ምርጫው ተጭበርብሮዋል በሚል ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባልሆኑበት ጊዜ አዳማ ባሮው የሄዱትም ወደ ሴኔጋል ነበር፣ የ«ኤኮዋስ» ጦርም  ድንበር ተሻግሮ ጋምቢያ በገባበት ጊዜ እርግጥ ነው የሴኔጋል ወታደሮች ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። በወቅቱ ወደ 2,500 የሚጠጉ የ«ኤኮዋስ » ጦር ፣ ብዙዎቹም  የሴኔጋል ወታደሮች የሃገሪቱን ፀጥታ ለማስጠበቅ አሁን ጋምቢያ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ  ግን  «ኤኮዋስ» አባል ሃገራት በደረሱት የጋራ ስምምነት መሰረት ነው የሆነው። ምን ያህል ጊዜ በዚያ እንደሚቆi ግልጽ አይደለም፣ ፕሬዚደንት አዳማ ባሮው ግን ወታደሮቹ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲቆዩ ጠይቀዋል።


እንደ ሀሊፋ ሳላህ አስተያየት፣  የጋምቢያ እና የሴኔጋል ግንኙነት አዳጋች በነበረበት  በያህያ ጃሜህ ዘመነ ስልጣንም ወቅት፣  አንድ ዓይነት ባህል ያላቸው የሁለቱ ሃገሮች ሕዝቦች ራሳቸውን እንደ አንድ ሕዝብ ነው የሚያዩት።  

"ይህም በዴሞክራሲያዊው መንገድ በተመረጡት አዲሱ ፕሬዚደንት አዳማ ባሮው መንግሥት እና በሴኔጋል መካከል ግንኙነቱ ከበፊቱ ከነበረው በተለየ ሁኔታ በሚሻሻልበት ድርጊት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ጀርመናዊው የኮንራድ አድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ቶማስ ፎልክ አስረድተዋል።  ይሁን እንጂ፣ ይላሉ ፎልክ፣  ከዚያ በፊት ፕሬዚደንት ባሮው በሃገራቸው ማስተካከል ያለባቸው ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል።
« ጊዜው የጋምቢያን አንድነት እንደገና የማረጋጋጥ ወቅት ነው። ከዚህ በተጨማሪም፣ ለጋምቢያ የተሳካ አዲስ ዘመን መፍጠር የሚያስችለውን ሁኔታ ሂደት ማነቃቃት ነው። »
ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ፕሬዚደንት አዳማ ባሮው አንዳችም ሳይዘገዩ ወደ ስራ እንደሚገቡ ያስታወቁ ሲሆን፣ የሃገሪቱ ኤኮኖሚ መልሶ ግንባታ ትልቁን ትኩረታቸውን እንደሚያገን ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic