ጋምቢያ-ተጠርጣሪዎች እየታሰሩ ነዉ | አፍሪቃ | DW | 03.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ጋምቢያ-ተጠርጣሪዎች እየታሰሩ ነዉ

የጋምቢያ መንግሥት ባለፈዉ ማክሰኞ መፈንቅለ መንግሥት ከሞከሩ የጦር መኮንኖች ጋር ግንኙነት አላቸዉ ብሎ የጠረጠራቸዉን የጦር መኮንኖች ማሠሩን ጥሎአል።

በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጡ 20 ዓመታቸዉን የያዙት ፕሬዝዳንት ያሕያ ጃሜሕ ሴራዉን የዶለቱት ዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመንና ብሪታንያ የሚኖሩ ናቸዉ በማለት አዉግዘዋል። እንዲሁም የኬንያ መንግሥት ከሁለት ሳምንት በፊት ያፀደቀዉ የፀረ-ሽብር ሕግ አንዳድ አንቀፆች ተግባራዊ እንዳይሆኑ የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ማገዱ ይታወቃል። የኬንያ ፀረ ሽብር ሕግና የፍርድ ቤቱ ርምጃ የዕለቱ ትኩረት በአፍሪቃ መሰናዶ የመጀመርያዉ ርዕስ ነዉ። የዕለቱ ትኩረት በአፍሪቃ ሁለተት ርዕሶችን ይዞአል።


በምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር በጋምቢያ ከከሸፈዉ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በርካታ ወታደራዊ ኋይላትና ሲቢል ማሕበረሰቦች መያዛቸዉ ተገልፆአል። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ አሸባሪነት ነዉ ያሉት ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜህ ሙከራዉ ድጋፍ ያገኘዉ ከዩኤስ አሜሪካ ከጀርመንና ከብሪታንያ ነዉ ሲሉ ኮንነዋል።
የጋምቢያ ባለሥልጣን መስርያ ቤት እንደገለፀዉ ከቀናቶች በፊት መንግሥትን ለመገልበጥ ሊደረግ የነበረዉን ሙከራ እቅድና በመዲና ባንጁል የባህር ወደብ በቆሙ ግዙፍ የቃ መጫኛ ሳጥኖች ዉስጥ እጅግ በርካታ አዉቶማቲክ የጦር መሳርያና ፈንጂዎችን ማግኘቱንና በቁጥጥር ስር ማድረጉን አስታዉቆአል። እንደ ጋምቢያ የደህንነት መስርያ ቤት፤ ይህ እጅግ በርካታ የጦር መሳርያ ምናልባትም የፕሬዚዳንቱን መቀመጫ ለማጥቃት ጥቅም ላይ ሊዉል እንዳልሆነ ነዉ የተመለከተዉ። በዚህም ይህንን ለማጣራት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ወታደራዊ ኃይሎችና ሲቢሎች ላይ ምርመራ ይካሄዳል። በጋምቢያ መዲና ባንጁል በሚገኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የጋዜጠኝነት ትምህርቱን በመከታተል ላይ ያለ ስሙ እንዳይገለፅ ያልፈለገ አንድ የአይን እማኝ ባለፈዉ ማክሰኞ የጋምቢያዉ ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ በሌሉበት የመንግሥት ግልበጣ ሙከራዉ እንደተካሄደ በስልክ ለዶይቼ ቬለ እንደገለፀዉ ማለዳ ላይ ከፍተኛ የጦር መሳርያ ፍንዳታ ነዉ የተሰማዉ።


« ማለዳ ጠዋት ከእንቅልፋችን እንደተነሳን የተነገረን ከባድ የመሳርያ ፍንዳታ እንዳለ ነዉ። የተኩስ ልዉዉጡ በፕሬዚደንቱ መቀመጫ በጃሜህ ታማኞችና ከጎረቤት ሴኔጋል በመጡት ጥቃት አድራሾች መካከል ነዉ። ሃገሪቱ ከማለዳ አንስቶ ዉጥረት ዉስጥ ነበረች። ሰዎች ከስራ ቦታ እንዲመለሱ ታዘዙ፤ ነዋሪዎች ሁሉ ከየቤታቸዉ ወደ ዉጭ ለመዉጣት ሁሉ ፈርተዉ ቤታቸዉን ዘጉ። እንዲሁም በሃገሪቱ ጎርጎረሳዉያኑ 1994 ዓ,ም ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የተከሰተዉ ዓይነት ሁኔታ ዳግም እንዳይከሰት በመፍራት ጥቂት ሰዎች ሩዝና ሌሎች የምግብ አይነቶችን ለመግዛት ወደ ሱቅ የወጡም ነበሩ። ብዙዎች ፈርተዋል። ሱቆች፤ ባንክና ሌሎች የብዙሃኑ መጠቀምያ መስርያ ቤቶች ሁሉ ተዘግተዉ ነበር፤ ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁሉ ነገር ተረጋጋ ፤ ሁላችንም ከቤታችን ከሰዎችና ከጓደኞቻችን ጋር ለመነጋገር ወደ ጎዳና ወጣን። አሁን ሁሉ ነገር ወደ ቀድሞዉ ሁኔታ ተመልሶአል»

በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ ለማክሰኞ አጥብያ ሌሊት የታጠቁ የሃገሪቱ የቀድሞ ወታደራዊ ኃይል አዛዥ የላሚን ሳኔህ ደጋፊዎች በፕሬዚዳንቱን መቀመጫና አንድ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ላይ በከባድ መሳርያ ጥቃት በማድረስ ዘልቀዉ ገብተዉ ነዉ ጥቃት የጣሉት። እንዲያም ሆኖ የፕሬዚዳንቱ ወታደራዊ ኃይሎች በከባድ የተኩስ ልዉዉጥ ጥቃቱን ለመከላከልና ሁኔታዉን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ ዕድል ይቀናቸዋል። በጋምቢያ መዲና በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የጋዜጠኝነት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘዉ ጋምቢያዊዉ የዓይን እማኝ እንደገለፀዉ ለመንግሥት ግልበጣዉ ተጠያቂ ሴኔጋል ዉስጥ ይኖሩ የነበሩት የቀድሞዉ ወታደራዊ ኃይል አዛዥ ናቸዉ።

« ባለን መረጃ መሰረት፤ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራዉ የተደረገዉ በቀድሞ የቅርብ ወታደራዊ መኮንን በላሜን ሳኔህ እንደሆነ ነዉ የሚታመነዉ። ይህን መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ሳኔ በጎረቤት ሃገር ሴኔጋል የሚገኙ ሲሆን ፤ በባንጁ ፕሬዚዳንት መቀመጫ የቀድሞ የብሔራዊ ጦር አዛዥ እሳቸዉ ናቸዉ። ከቀድሞ የጦር መኮንኖች ጋር በመተባበር ነዉ መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩት።»


በምዕራባዊትዋ ሃገር በጋምቢያ የተሞከረዉን የመንግሥት ግልበጣ ለማክሸፍ በተካሄደ የተኩስ ልዉዉጥ የቀድሞዉን ወታደራዊ አዛዥ ሴናህን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸዉ ተገልፆአል። እንደ ዓይን እማኞች በፕሬዚዳንት መቀመጫ ቅፅር ግቢ ዉስጥ በነበረዉ ከፍተኛ የተኩስ ልዉዉጥ ምክንያት ወደ ከተማዉ እንብርት የሚወስደዉ ጎዳና በፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ለረጅም ሰዓታት ተዘግቶ ቆይቶአል። የጋምቢያ መንግሥት ባለፈዉ መንግሥት ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ጋር ግንኙነት አላቸዉ ብሎ የጠረጠራቸዉን የጦር መኮንኖች ማሠሩን እንደቀጠለ ነዉ። የጋምቢያ የሥለላ ድርጅት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ከከሸፈዉ መፍንቅለ መንግሥት ሞካሪዎች ጋር በአባሪ ተባባሪነት የተጠረጠሩ ወደ ሃያ የሚጠጉ የጦር መኮንኖችና የሲቢል ፖለቲከኞች ናቸዉ እስካሁን የታሰሩት።የጋምቢያዉ ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ካቢኔያቸዉንና ዉታደራዊ ሃሎችን በአዲስ ማዋቀር ላይ እንደነበሩ ተመልክቶአል። ምናልባት ይህ የመንግሥት ግልበጣ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ይኖረዉ ይሆን?


«እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ መንግሥት በዚህ ጉዳይ እጅግ የተጨነቀ ይመስላል። እዚህ ሃገርዉስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፤ በፖለቲካ ምክንያት ብቻ ሰዎች ያለምንም ምክንያት ይዋከባሉ ይታሰራሉ። በርካታ ነገሮች አሉ እናም፤ ይህ አንዱ ምክንያት ይመስለኛል፤ ፕሬዚዳንቱ በሌሉበት ስልጣናቸዉን ለማስለቀቅ ሙከራ የተደረገዉ»
በጋምብያ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ሲደረግ ከሃገር ዉጭ የነበሩት ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ሙከራዉ ከሽፎ ሃገሪትዋ በያህያ ወታደሮች በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ በማግሥቱ ፕሬዚዳንቱ ቻድን አቋርጠዉ ሃገራቸዉ መመለሳቸዉ ተዘግቦአል። ያህያ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ በተደረገበት ወቅት በፈረንሳይ ይሁኑ አልያም በዱባይ በግልፅ የተነገረ ነገር የለም። የጋምቢያዉ ፕሬዚደንት ሥልጣን ከአሁን ወድያ ምን ያህል አስተማማኝ ይሆን? የጋምቢያዊዉ የዓይን እማኝ በሃገሪቱ በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱን ይገልፃል።« በሃገሪቱ ይህ አይነት የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ሲደረግ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ፤ እስከዛሬ ግን አልተሳካም። ፕሬዚዳንቱ ራሳቸዉ ወደዚህ ስልጣን የመጡት በመፈንቅለ መንግሥት ነዉ። ያህያ ስልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ በርካታ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶአል። ተቃዋሚዎቹ ሃገሪቱ በጣም ከባድ ሁኔታዎች ላይ እንዳለች ነዉ የሚያስቡት። ሰዎች ደህንነት አይሰማቸዉም በዚህ ወቅት የደህንነት ሰራተኞች ህዝቡ ዉስጥ በመግባት የተለያየ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የመሳሰሉ ነገሮች ይፈፀማሉ ይፈፀማሉ። አገዛዙ እጅግ ጨካኝ ነዉ። በዚህም ምክንያትም ይመስለኛል መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ እሳቸዉን ከስልጣን ለማባረር ጥረት እየተደረገ ያለዉ።»

ጋምቢያ በጎርጎረሳዉያኑ 1965 ዓ,ም ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በኋላ ለ29 ዓመታት የፕሬዚዳንት መንበሩን ተቆናጠዉ የቆዩትን የመጀመርያ የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ዳዋዳ ጃዋራ፤ አሁን ለ20 ዓመታት የፕሬዚዳንትነት በትረ ሥልጣኑን ይዘዉ በሚገኙት በፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን መወገዳቸዉ ይታወቃል። ጃሜህ በስልጣን ለመቆየት በተለያየ ጊዜ ፖለቲካዊ አቋማቸዉን በመቀየራቸዉ በሃገሪቱ በተካሄዱ ምርጫዎች ዳግም ተመርጠዋል። ጃሜህ ለማህበረሰቡ ቀረቤታ እንዳላቸዉም ለማሳየት ሙከራ ቢያደርጉም፤ በሃገሪቱ የፕሪስ ነፃነት ላይና ተቃዋሚዎች ላይ በሚደረገዉ ጫና ተደጋጋሚ ትችት ገጥሞአቸዋል። በአሁኑ ወቅት የጋምቢያ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምን ያህል ይሆን?
« መንግሥት ግልበጣዉ ከሽፎ ሁኔታዎች ሁሉ በቁጥጥር ሥር ከሆኑ በኋላ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ዉጥረት ነግሶ ይታያል። ግን ይህ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም፤ ምክንያቱም እጅግ ጨካኔ የተሞላ ሰዉ ባለበት፤ ሰዎች በግልፅ መናገር ይፈራሉ፤ እጅግ አደገኛ ቢሆንም ለሁኔታዉ በአሁኑ ወቅት እኔ ለራድዮ ቃለ- ምልልሥ የምሰጠዉ የመጣዉ ይምጣ ብዬ ነዉ። ምክንያቱም ስለሆነዉ ነገር ሰዎች በትክክል ማወቅ አለባቸዉ። እና ሰዎች በጣም ፈርተዋል። ይህ ሁኔታ የጋምቢያን ምንነት የሚገልፅ አይደለም። ሃገራችን እጅግ ሰላም የሰፈነባት ነበረች። አሁንም ሁሉ ነገር በጥሩ ሁኔታ እንዲያልፍ እየፀለይን ተስፋ እናደርጋለን።»የመንግሥት ብዙሃን መገናኛዎች ስለ መፈንቅለመንግሥት ሙከራዉ ምን ዘግበዉ ይሆን?
« ስለ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ መንግሥት በሚቆጣጠረዉ የብዙሃን መገናኛ አንድም ቃል አልተዘገበም። መንግሥትም ስለ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ እስካሁን በይፋ የገለፀዉ ነገርም የለም። ስለዚህ ህዝቡ ከዲፕሎማትና ሌላ ምንጮች በመደገፍ ከዉጭ መረጃን ያገኛል»
እንድያም ሆኖ ፕሬዚዳነት ያህያ ጃሜህ መፈንቅለ መንግሥቱ በተደረገ በሁለተኛ ቀን በሰጡት መግለጫ ዩኤስ አሜሪካ፣ ጀርመን እና ብሪታንያ የሚገኙ ኃይሎች ያሏቸዉ ድጋፍ ያለበት የአሸባሪዎች ጥቃት ነዉ የተካጌደዉ ሲሉ ማዉገዛቸዉ ተዘግቦአል። የዩናይትድ ስቴትስ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣዉ መግለጫ በጋምቢያዉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እጁ እንደሌለበት፤ እንዲህ ባለ መንገድ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረትንም እንደሚያወግዝ አስታዉቋል።


ቀጠን ባለ ወሽመጥ አትላንቲክ ዉቅያኖስን በጥቂቱ የምትዋሰነዉና 1, 7 ሚሊዮን ነዋሪዎች የሚገኙባት ምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ትንሽ ሃገር ጋምቢያ፤ በሴኔጋል አዋሳኝነት ብቻ ታቅፋ የምትገኝ ሃገር መሆንዋ ይታወቃል። ዘጠና በመቶ የሚሆነዉ ነዋሪዋ ደግሞ የእስልምና ሐይማኖት ተከታይ ነዉ። በቅርቡ የተመድ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ በትንሽቱ ምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር በጋምቢያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም አመልክቷል።

ናይሮቢ-የኬንያ ፀረ ሽብር ሕግና የፍርድ ቤቱ ርምጃ

የኬንያ አዲሱ የደህንነት ሕግ አንዳንዳ አንቀፆች እስኪ መረመሩ ድረስ ተግባራዊ እንዳይሆኑ የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አግዶአል። ከሁለት ሳምንት በፊት የፀረ- ሽብር ሕጉን የኬንያ ምክር ቤት በድምፀ ብልጫ ካሳለፈ በኋላ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በፊርማ ማፅደቃቸዉ ይታወቃል ። የመብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕጉ ከሃገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የማይጣጣምና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ነዉ ሲሉ ተቃዉመዉታል። የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ጆርጅ ኦዱንጋ ትናንት አርብ እንዳስታወቁት «ከሕጉ-አንቀፆች ስምንቱ የኬንያን የሰብዓዊ መብት ሕጎች የሚጥሱ ናቸዉ የሚል ሥጋትን ቀስቅሶአል። የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ካገዳቸዉ ስምንት ሕግ ጋቶች መካከል አንዱ የመንግሥትን ስም በሚያጠፉ ጋዜጠኞች እንዲሁም የፖሊስ ምርመራን የሚተቹ ዘገባዎችን ያቀረቡ ጋዜጠኞች የሶስት ዓመት እስራት አልያም 56 ሺህ ዶላር ቅጣትን ይደነግጋል። በፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ የስደተኞች ቁጥርን የሚወስን አንቀፅ እንደተካተተበትም ተመልክቶአል። የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ጆርጅ ኦዱንጋ እንደገለፁት « ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ብለን ነፃነትና መሰረታዊ መብቶችን ልንገድብ አንችልም»። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሁለት ሳምንት በፊት ያፀደቁትንና አርብ ዕለት በታገደዉ የፀረ- ሽብር ሕግ ዉሳኔ ላይ ተካፋይ የነበሩት ኬንያዊዉ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ባለሙያ ቦብይ ሙካንግ ፀረ-ሽብር አንቀፆቹ መሻር እንዳለባቸዉ ገልፀዋል።


«(ፍርድ ቤቱ ያገዳቸዉ) የፀረ-ሽብር ሕጉ ክፍሎች መሻር አለባቸዉ።ምክንያቱም በኬንያ ሕገ-መንግሥት መሠረት ሕገ-መንግሥቱን የሚቃራን ማንኛዉም ሕግ ተቀባይነት አይኖረዉምና።»
የዛሬ ሁለት ሳምንት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አዲሱንና አወዛጋቢዉን ፀረ- ሽብር አዋጅ ሲፈርሙ ሕጉ ከየትኛዉም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ወይም የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ጋር አይጋጭም ሲሉ ተናግረዉ ነበር። እንደ ኡሁሩ ሃገሪቱ የተደቀኑባትን የሽብርተኝነት ስጋቶች ለመዋጋት ሕጉ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ያሟላል፤ ሕጉን መፍራት ያለባቸዉም ወንጀለኞች ብቻ ናቸዉ ሱሉም ተናግረዋል። ተቃዋሚዎቻቸዉ በበኩላቸዉ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ያለምንም ክስ ከ 90 እስከ 360 ቀናት ያለምንም ክስ መያዝን የሚፈቅደዉ ሕግ ነፃነትና የሃሳብ መግለፅ መብትን ደፍጣጭ ነዉ ሲሉ ተቃዉመዋቸዉ ነበር።
CORD በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የኬንያ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ዉሳኔ በደስታ ነዉ የተቀበለዉ። የፓርቲዉ መሪና የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ እንደሚሉት በዴሞክራሲ ስም የኬንያዉያን መብትና ደሕንነት ለድርድር መቅረብ አይኖርበትም።


አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic