ጋምቢያውያን እና ፍትህ የማግኘት ተስፋቸው | አፍሪቃ | DW | 16.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ጋምቢያውያን እና ፍትህ የማግኘት ተስፋቸው

በጋምቢያ ባለፈው ጥር ያበቃው የቀድሞው መሪ ያህያ ጃሜህ የ22 ዓመት አገዛዝ ቁም ስቅል፣ ግድያ እና በደል የበዛበት ጊዜ ነበር። እና በፕሬዚደንት አዳማ ባሮው የሚመራው አዲሱ የሀገሪቱ መንግሥት በጃሜህ ዘመን የተፈጸሙትን የመብት ጥሰቶች የሚያጣራ፣ በሀገሪቱ እርቀ ሰላም ለማውረድና ለሰለባዎቹም ካሳ እንዲከፈል የሚጥር አንድ ኮሚሽን አቋቁሟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:04
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:04 ደቂቃ

ጋምቢያ

ይሁንና፣ ካትሪን ጌንስለር እንደታዘበችው፣ በሕይወት የተረፉት ጋምቢያውያኑ የመብት ጥሰት ሰለባዎች ኮሚሽኑ ፍትህ ያስገኛል ብለው ብዙም አይጠብቁም።

ጋምቢያዊው ዩሱፍ ምባዬ  ለመንቀሳቀስ በአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበር ይጠቀማል። የ34 ዓመቱ ወጣት በእህቱ ወይም በእናቱ ርዳታ ላይ ጥገኛ ነው። በጎርጎሪዮሳዊው ሚያዝያ 10 እና 11፣ 2000 ዓም የተከሰተው ሁኔታ ለዚህ መጥፎ እጣ እንደዳረገው በቅሬታ ያስታውሳል።
« ያ ቀን በሕይወቴ በፍፁም የማልረሳው ቀን ነው። በጣም አሳዛኝ ቀን ነው። በዚያን ቀን ነው ሕይወቴ የተቀየረው። ያኔ ተማሪዎች ነበርን፣ በዚያን ጊዜ የእሳት አደጋ ሰራተኞች አንድ አቻ ተማሪን አሰቃይተው ገደሉ፣ አንዲት የ13 ዓመት ተማሪንም በኃይል ደፈሩ። ይህን ተከትሎ መንግሥት በተጠያቂዎቹ የእሳት አደጋ ሰራተኞ ላይ ርምጃ እንዲወስድ በመጠየቅ ደብዳቤ ጻፍን። መንግሥት ግን አንድም ርምጃ ሳይወስድ ቀረ። በዚህም የተነሳ ተቃውሟችንን ለማሰማት አደባባይ ወጣን። »


በተቃውሞው ወቅት የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚደንት መንግሥት ፀጥታ ኃይላት 14 ሰዎችን ተኩሰው ገደሉ። ዩሱፍ ምባዬም ጀርባውን በጥይት ተመታ። ለብዙ ወራት ግብፅ ውስጥ ህክምና ቢያደርግም አካል ጉዳተኛ ሆኗል። ትምህርቱንም መጨረስም ሆነ ስራ መያዝ አልቻለም። ጓደኞቹ እና የርዳታ ድርጅቶች በሚሰጡት ገንዘብ ላይ ጥገኛ ነው።  ባለፈው ታህሳስ ወር በጋምቢያ በተካሄደ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የ22 ዓመቱን የያህያ ጃሜን አገዛዝ ያበቁት አዲሱ የፕሬዚደንት አዳማ ባሮው መንግሥት ይህን ዓይነቱን የዩሱፍ ሁኔታ ለመለወጥ እንደሚፈልግ አስታውቋል። ጃሜህ ከአዳጋች ድርድር እና ዛቻ በኋላ ባለፈው ጥር ወር ወደ ኢኳቶርያል ጊኔ ተሰደዋል። ትተዋት የሄዱት ሀገር ግን አለመተማመን የሰፈነባት እና በዘመናቸው የተፈፀሙ መልስ ማግኘት ያለባቸው በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚታዩባት ናት። አዲስ የተቋቋመው የሀቅ፣ የእርቀ ሰላም አፈላላጊ እና የካሳ ጉዳይ ተመልካች ኮሚሽን ይህ ኃላፊነት እንደተሰጠው የጋምቢያ ፍትህ ሚንስትር አቡበከር ታምባዱ ገልጸዋል።

Versöhnung in Gambia (Banjul) (DW/Katrin Gänsler)

አቡበከር ታምባዱ


« ሀቁን ለማውጣት እንፈልጋለን። ዜጎችን በማሰቃየቱ ተግባር የተሳተፉትን ለይተን ማወቅ እንፈልጋለን። ያን ለምን ፣ ከምን ዓይነት ሁኔታ በመነሳት አደረጉ? በማን፣ በመንግሥት ወይም በአንድ ቡድን ወይም በአንድ ግለሰብ የታቀደ ነበር? እነዚህ ልናውቃቸው የሚገቡ መረጃዎች ናቸው። »
ኮሚሽኑ ያለፈው መንግሥት ርምጃ ሰለባዎችን ፣ ለምሳሌ፣ ጡረታ ወይም ለእጓለ ማውታን ደግሞ ነፃ የትምህርት እድል በመስጠት  ለመርዳት ይፈልጋል። ሰዎች ምን ያህል ርዳታ  እንደሚያስፈልጋቸው በሚቀጥሉት ወራት ይጣራል። ግን እስካሁን ለዚሁ ተግባር እንዲውል የተመደበው ገንዘብ 1,4 ሚልዮን ዶላር በመሆኑ፣ የኮሚሽኑ ዓላማ የሚፈለገውን ውጤት ማስገኘቱን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ኤሳ ንጂየ አብዝተው ይጠራጠራሉ።

Versöhnung in Gambia ( Banjul) (DW/Katrin Gänsler)

ኢሳ ንጂየ


« ጠንካራ ኤኮኖሚ ከሌለህ ይህን ዓይነቱን ዓላማ ማሳካቱ ሁሌም አዳጋች ነው። ፍትህ እስካልተገኘ ድርስ እርቀ ሰላም ማውረድ አይቻልም። ለሰለባዎቹ ካሳ መክፈል አስፈላጊ ነው። ግን፣ አሁን እንደሚታየው፣  የሀገሪቱ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ መንግሥትን ካሳ መክፈል የሚያስችለው አይደለም። »
አዲሶቹ ፖለቲከኞች ለዚሁ እቅዳቸው በየቦታው ማስታወቂያ ማድረግ ይዘዋል፣ ይሁንና፣ በጋምቢያ የስልጣን ለውጥ ከተደረገ ዛሬ ከሰባት ወራት በኋላም ዩሱፍን የመሳሰሉ ሰለባዎች ከዚህ  ዓይነቱ ፕሮዤ ብዙም አይጠብቁም። ዩሱፍ ባለፈው ጥር ወር ፕሬዚደንት ባሮውን በግል አግኝቷቸው ነበር፣ ግን፣ ከዚያን ወዲህ የሰማው ነገር እንደሌለ ይናገራል።
«  ምናልባት ካሳ ይሰጥ ይሆናል፣ ላይሰጥም ይችላል። እስካሁን ፣እኛ ሰለባዎቹ ፣ ምንም ያገኘነው ነገር የለም፣ በጣም ብዙ ደብዳቤዎች ብንጽፍም። እና በጋምቢያ መንግሥት ላይ እምነት የለኝም፣ »
አሁንም በኃላፊነት ስልጣን ላይ ከሚገኙ የቀድሞ የጃሜህ ደጋፊዎች መካከል ስንቱ ፍርድ ፊት እንደሚቀርቡ እና ምን እንደሚባሉ ግልጽ አይደለም። በመሆኑም፣ እንደፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ንጄ አስተሳሰብ፣ ኮሚሽኑ ከ1994 ዓም ጀምሮ ለተፈጸሙት በደሎች ተጠያቂዎቹን ሁሉ ለፍርድ ማቅረብ ይችል ዘንድ  ምርመራውን በሁሉም አቅጣጫ ማካሄድ ይኖርበታል። የፍትህ ሚንስትሩ አቡበከር ታምባዱም ሁለት ሚልዮኑ ጋምቢያውያን፣ በተለይ የቀድሞው መንግሥት ጥሰት ሰለባዎች፣ በኮሚሽኑ እንደተወከሉ ሊሰማቸው እንደሚገባ ከማመልከታቸው ጎን፣ በወቅቱ ከሁሉም በላይ ለሕዝቡ ዓቢይ ትርጓሜ የያዘው ጉዳይ ከብዙ ዓመታት የመብት ጥሰት በኋላ ጋምቢያ እንደገና አንድ የምትሆንበት ርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች