«ጊዜው ተባብረን የምንሰራበት ነው» ፋርማሲስት ሩት | ወጣቶች | DW | 15.05.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

«ጊዜው ተባብረን የምንሰራበት ነው» ፋርማሲስት ሩት

ፋርማሲስት ሩት ድረስልኝ ደነቀ በአሁኑ ሰዓት ዓለም አቀፋዊ ስጋት የሆነው የኮቪድ 19 ተህዋሲን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል አንድ የበጎ ፍቃደኞች ቡድን ውስጥ ትገኛለች። ሌሎች ወጣቶችም እንዴት የዚህ አካል መሆን እንደሚችሉ የመፍትሄ ሀሳብ አላት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:33

ወጣቶች፦«ጊዜው ተባብረን የምንሰራበት ነው» ፋርማሲስት ሩት

 ሩት ድረስልኝ ደነቀ ኢትዮጵያም ይሁን አሁን በምትኖርበት ጀርመን ሀገር ለተለያዩ የውጭ ድርጅቶች በሙያዋ በማገልገል ላይ ትገኛለች። የ 33 ዓመቷ ወጣት ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ሲሆን ከ 10 ዓመት ገደማ በፊት ከአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ በፋርማሲስት ሙያ ተመርቃለች። « የመጀመሪያ ስራዬ መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ፋይዘር የተባለ ድርጅት ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ኔስትሌ የተባለ ድርጅት ነው የሰራሁት» የምትለው ሩት በእነዚህ ድርጅቶች በብዛት የእናት እና የሕጻናት ጤና ላይ በማተኮር ሰርታለች። ቀጥላ በሰራችበት የገልፍ ፋርማቲካል ድርጅት ደግሞ የበለጠ ትኩረት ሰጥታ ትሰራ የነበረው ለስኳር እና ኩላሊት በሽተኞች የመድኃኒት አቅርቦት እና ጨረታ ላይ ነበር።« ብዙውን ጊዜ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ጋር ነው የምሰራ የነበረው። ጨረታውን ከአሸነፍኩ በኋላ ደግሞ ከሀኪሞች እና ከሆስፒታሎች ጋር የመድኃኒት አቅርቦቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ አብረን እንሰራ ነበር።» ሩት እንደምትለው ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር በሽተኞቹ መድኋኒቱን የመግዛት አቅማቸው ትንሽ ስለሆነ እነሱ ሊከፍሉት በሚችሉት ወይም በተመጣጣኝ ዋጋ መጫረት መቻሉ  ነበር። እንደዛም ሆኖ ወጣቷ ብዙ ጨረታዎችን እንዳሸነፈች ነግራናለች። ሩት በአሁኑ ሰዓት ሜርክ በተባለ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ውስጥ እዚህ ጀርመን ሀገር እየሰራች ትገኛለች። በዚህም ኩባንያ ውስጥ የተለያዩ የስራ ድርሻዎች አላት። 

ከዚህም ሌላ ሩት በአሁኑ ሰዓት የዓለም ስጋት የሆነው የኮሮና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ስለሚደረገው ጥረት ትኩረት ሰጥታ በመከታተል ላይ ትገኛለች። ይህ ብቻ ሳይሆን የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት በተለያዩ የበጎ አድራጎት ቡድኖች ውስጥ ተሳታፊ ናት። ከነዚህ ቡድን አንዱ አለም አቀፍ በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት (Ethiopia COVID-19 Response Team) ነው። ቡድኑ ጠቃሚ መረጃዎችን ማሰናዳት እና መለዋወጥ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም በተግባር እየተሰሩ ያሉ ነገሮች አሉ ትላለች ሩት። 
ሩት በውጭ ሀገር በስራ ላይም ይሁን በትምህርት ላይ የሚገኙ ወጣቶች በርካታ ሀገራቸውን ሊረዱ የሚችሉበት መንገድ አለ ትላለች። « ውጪ ነኝ እና አያገባኝም ማለት አይቻልም።» ለወጣቶች ሁላችንም ተባብረን መስራት አለብን የሚል መልዕክት ነው ያላት። በገንዘብም ይሁን በእውቀት እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ግራ ለገባቸው ወጣቶች ለምሳሌ በአካባቢያቸው የሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ደውለው በመጠየቅ ወይም ኢንተርኔት ላይ የበጎ አድራጊ ቡድንኖችን በመፈለግ መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ ትጠቁማለች። 
ከፋርማሲስት ሩት ድረስልኝ ደነቀ ጋር የነበረንን ቃለ መጠይቅ እዚህ ገፅ ላይ በድምፅ ያገኛሉ። 


ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic