ጊኒ ከግድያው በኋላ | ኢትዮጵያ | DW | 03.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ጊኒ ከግድያው በኋላ

የምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ጊኒ ጸጥታ አስከባሪዎች ብዙ ሰዎች ከገደሉ ከአራት ቀናት በኋላ የሀገሪቱ ወታደራዊ መሪ ሻምበል ሙሳ ዳዲስ ካማራ ከተለያዩት የተቃዋሚ ወገኖች ጋር ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ አቀረቡ።

default

ሻምበል ሙሳ ዳዲስ ካማራ

ጊኔ መዲና ኮናክሪ ውስጥ የጸጥታ አስከባሪዎች ባለፈው ሰኞ በመንግስቱ አንጻር በእግር ኳስ ሜዳ-በስቴድየም ተሰብበው በነበሩት የተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ ከፍተው ፡ አንድ መቶ ሀምሳ ሰባት ሰዎችን ከገደሉና በሺዎች የሚቆጠሩ ካቆሰሉ በኋላ በሻምበል ሙሳ ዳዲስ ካማራ በሚመራው ወታደራዊ መንግስት ላይ ዓለም አቀፍ ውግዘት ተፈራርቆዋል። በሀገሪቱ ተቃውሞ እንዳይደረግ መንግስት ቢከለክልም፡ ሀምሳ ሺህ የተቃዋሚ ቡድኖች ደጋፊዎች፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሲድያ ቱሬ ጭምር ነበሩ ባለፈው ታህሳስ ወር በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን በያዙት በሻምበል ካማራ አንጻር ተቃውሞ ለማሰማት በእግር ኳሱ ሜዳ የተሰበሰቡት።
ከግድያው በኋላ ካማራ በፈረንሳይ ቴሌቪዥን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ወታደሮቹ የወሰዱት የኃይል ርምጃ እንዳሳዘናቸው በመግለጽ በሀገሪቱ የሁለት ቀን ብሄራዊ ሀዘንም አውጀው ነበር።
« በጣም ያሳዝናል፤ ያስደነግጣል። እንዴት እዚህ ሊደረስ መቻሉን ለማወቅ ተጨማሪ መረጃዎችን እየጠበቅሁ ነው። ግን፡ በውነቱ፡ በጣም በጣም አዝናለሁ። »
በዚሁ አነጋገራቸው ግድያውን በፍጹም እንዳልጠበቁት እና በድርጊቱ መፈጸምም መገረማቸውን ለመግለጽ ሞክረዋል። ከዘጠኝ ወራት በፊት የቀድሞው ፕሬዚደንት ላንዛና ኮንቴ ሲሞቱ ካላንዳች ደም መፋሰስ ስልጣኑን በያዙበት ጊዜ ህዝቡ ደግፎዋቸው ነበር። ይኸው ካማራ ያኔ ያካሄዱት መፈንቅለ መንግስት ለርሳቸው ታማኝ ከሆኑ እና እንደርሳቸው የጀርመንኛ ቋንቋ ከሚናገሩ ጥቂት የጦር ኃይሉ መኮንኖች ጋር ያሴሩት ስለነበር የጀርመኑ መፈንቅለ መንግስት እየተባለ ይጠራል። ካማራ የጀርመንኛውን ቋንቋ የተማሩት በጀርመን ብሄራዊ ጦር የጦር መኮንን አካዳሚ ውስጥ ትምህርት በተከታተሉበት ጊዜ እንደነበር በአንድ የቴሌቪዥን ውይይት ላይ ገልጸው ነበር።
« በጀርመን ነበር መሰረታዊውን ስልጠና፡ ማለትም፡ የቡድን መሪነትና የአየር ወለድ ትምህርትን የተከታተልኩት። ወደ ጀርመን የምመለሰው በፕሬዚደንትነት ስልጣን ይሆናል። መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም ሊቀበሉኝ ይገባል፡ ቢያንስ ይህን አክብሮት ከርሳቸው እጠብቃለሁ። »
ካማራ በጊኔ የሲቭሉ መንግስት መመስረት ይችል ዘንድ የፊታችን ጥር ወር በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በዕጩነት ላለመቅረብ ለህዝቡ የገቡትን ቃል ይጠብቁ እንደሆን በኮናክሪ የሚገኙት የጀርመን አምባሳደር ከጥቂት ጊዜ በፊት ጥያቄ ባቀረቡላቸው ጊዜ እጅግ ነበር የተቆጡት። ካማራ ጥያቄውን እንደስድብ ነበር የተመለከቱት።
« አሁን ያለሁት እኮ ቤቴ ውስጥ ነው፡ ይህ ሀገሬ ነው። ፕሬዚደንት ነኛ፤ ስልጣኔን ያክብሩ። ለጀርመንና ለስልጣንዋ ትልቅ አመለካከት አለኝ። እና እንደ አንድ ህጻን ልጅ ሊመለከቱኝ አይገባም። እኔ የጊኔ ፕሬዚደንት ነኝ። »
ቀደም ባሉት ጊዚያት ብዙ ተሞግሰው የነበሩት ካማራ በወቅቱ ስጋት አድሮባቸው ጭንቀት ይታይባቸዋል። እንደሚታወቀው፡ ከቀድሞው የጦር ኃይሉ አመራር ቡድን ጋር ግንኙነት ያልነበራቸው ካማራ በድህነትና በሙስና አንጻር ትግል ለማካሄድ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው፤ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚልዮን ህዝብ ያላት በቦክሲትና በሌሎች ማዕድናት የታደለችው ጊኔ በሀገርዋ ተስፋፍቶ በነበረው ሙስና እና የተሳሳተ አስተዳደር ሰበብ ይህንኑ ሀብትዋን እስካሁን ጥቅም ላይ ልታውለው ባለመቻልዋ ከዓለም ድሆች ሀገሮች መካከል ትቆጠራለች። በዚህም የተነሳ ነበር የብዙዎቹን የጊኔ ዜጎችን ድጋፍ አግኝተው የነበሩት። ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተቀያይረው ያ ሁሉ ድጋፍም ጠፍቶዋል። በኮናክሪ እግር ኳስ ሜዳ በአንጻራቸው የተሰበሰበው ሀምሳ ሺህ ህዝብ በስቴድየሙ ከሚፈቀደው በእጥፍ ይበልጥ ነበር። ይህም በአንጻራቸው የተፈጠረው ተቃውሞ ምን ያህል እንደተጠናከረ የሚያሳይ ነው። እርግጥ፡ ካማራ ከፕሬዚደንት ላንዛና ኮንቴ ሞት በኋላ በጦር ኃይሉ መኮንኖች መካከል የስልጣኑ ሽኩቻ እንዳይነሳ ማድረጉ ተሳክቶላቸው ነበር፤ ሀገሪቱም ወደ ምስቅልቅሉ ሁኔታ እንዳትወድቅ አድርገው ነበር። ፕሬዚደንታዊው ምርጫ የፊታችን ጥር ወር እስኪደረግ ድረስ ይህን ሁኔታ ጠብቀው ማቆየት መቻላቸውን ግን ብዙዎች ተጠራጥረውታል። ምክንያቱም፡ የተቃውሞው ቡድን አባልና የቀድሞው ከፍተኛ ባለስልጣን ሴሎ ዳለይን ዲያሎ እንዳሉት፡ የተቃዋሚዎች ትግላቸውን አያቋርጡም።
« የምንፈልገው ነጻነትና ዴሞክራሲን ነው። ተቃውሞአችንም ዴሞክራሲያዊ ትግል ጅምር ነው፤ እናም ትግላችንን እንቀጥላለለን። »
ይህንን ነው የጦር ኃይሉ ለማከላከል በመጣር ላይ ያለው። ከሰኞው ግድያ በኋላ የተቃውሞውው ቡድንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሴሎ ዳለይን ዲያሎ እና ሌሎች የመንግስቱ ተቃዋሚዎች የመታሰር ዕጣ ገጥሞአቸዋል።
የአፍሪቃ ህብረት የአዉሮጳ ህብረት ኮሚስዮንና የተመድ በጊኔ በርካታ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች መፈፅማቸዉን አጥብቆ አውግዞዋል። ፈረንሳይም ትብብርዋን አቋርጣለች። የአፍሪቃ ህብረትም ማዕቀብ እንደሚጥል አስጠንቅቋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የታሰሩ ፖለቲከኖች ባስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል። ተጠያቂዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ፡ በመጨረሻም የጊኒ ወታደራዊ መንግሥት በገባዉ ቃል መመሰረት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓትን እንዲያከብር አሳስበዋል። ሻምበል ካማራ ነጻ ምርጫ ይደረጋል፤ የጦር ኃይሉም ወደ ሰፈሩ ይመለሳል በሚል የገቡትን ቃል ባለመጠበቃቸው ወቀሳ ከተፈራረቀ በኋላ መንግስታቸው ምንም እንኳን አሁንም የሰኞው ትዕይንተ ህዝብ ህገ ወጥ እንደነበረ ቢያመለክትም፡ አንድ በተመድ የሚመራ ኮሚሽን ጭፍጨፋውንና ወታደሮቻቸው በተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ላይ ተኩስ እንዲከፍቱ ማን ትዕዛዝ እንደሰጣቸው እንደሚያጣራ አስታውቀዋል። ከተለያዩት የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጋር እስከ ጥር ምርጫ የሚቆይ የብሄራዊ አንድነት የሽግግር መንግስት የብሄራዊ አንድነት መንግስት ለመመስረት ዝግጁነቱንም አሳይቶዋል።

Audios and videos on the topic