1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጉባኤ ያካሔደው የህወሓት አመራር ቀጣይ እርምጃ ምን ሊሆን ይችላል?

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2016

በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት ባካሔደው ጉባኤ ያልተሳተፉ የፓርቲውን አመራሮች እና ቁጥጥር ኮሚሽን አግዷል። ይህ ውሳኔ ህወሓትን ወክለው የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርን እየመሩ ያሉ አካላትንም የሚመለከት ነው ሲሉ ተንታኞች ይገልፃሉ። ይህ ሁኔታ ወዴት ሊያመራ ይችላል ? የሕግ ምሁር አነጋግረናል።

https://p.dw.com/p/4jhk9
ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የህወሓት ሊቀመንበር፤ አቶ አማኑኤል አሰፋ ምክትል ሊቀመንበር
ለሰባት ቀናት የተካሔደው ጉባኤ ሲጠናቀቅ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የህወሓት ሊቀመንበር፤ አቶ አማኑኤል አሰፋ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።ምስል Million Haileslasse/DW

ጉባኤ ያካሔደው የህወሓት አመራር ቀጣይ እርምጃ ምን ሊሆን ይችላል?

ትላንት ጉባኤውን ያጠናቀቀው ህወሓት በጉባኤው መዝግያ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል አንዱ ከዚህ ቀደም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የነበሩ እና በጉባኤው ያልተሳተፉ አባላቱ ማገዱ የገለፀበት ነው። ህወሓት እንዳለው አፈንጋጭ ብሎ የገለፀው ቡድን ራሱ ከጉባኤ በማግለሉ፥ ከፓርቲው እንደወጣ አድርጎ በመውሰድ ከህወሓት ጋር እንደማይቀጥሉ አስታውቋል።

ይህ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እየመሩ ያሉ አካላት እና የህወሓት የቁጥጥር ኮምሽን የሚመለከት ሲሆን፥ በቀጣይ ሊፈጠሩ ይችላሉ ተብለው ለሚገመቱ 'የቢሆን ትንተናዎች' መነሻ ተደርጎ የተወሰደም ሆንዋል።

ከህወሓት መከፋፈል እና አንዱ ሐይል ወደ ጉባኤ መግባት በኃላ፣ የጉባኤው ውጤት ተከትሎ የሚፈጠር አዲስ ሁኔታ እንዲሁም ቀጣይ እርምጃ ምን ይሆናል በሚል የሕግ ምሁሩ አቶ ተኽሊት ገብረመስቀልን አነጋግረናል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና በነፈገው ጉባኤ ደብረፅዮን የህወሓት ሊቀ-መንበር ሆነው ተመረጡ

የሕግ ምሁሩ እንደሚሉት ስለቀጣይ ሁኔታ በርካታ የቢሆን ትንተናዎች ማስቀመጥ የሚቻል ቢሆንም፥ በዋነኝነት ግን ጉባኤ ያደረገው ህወሓት በፓርቲው የስልጣን ድርሻ ወደ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የገቡ ወይም የግዚያዊ አስተዳደሩ እየመሩ ያሉ የስራ ሐላፊዎች እንዲነሱ መስራት ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

ጌታቸው ረዳ እና ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
ህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት በተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ በፕሬዝደንትነት ሲመሩ ቆይተዋል። ምስል Million Hailesilassie/DW

ተኽሊት ገብረመስቀል "ይህ ጉባኤ አካሂጃለሁ የሚለው ሐይል፥ በግዚያዊ አስተዳደሩም ውክልና ያለኝ ስለሆነ አልያም እዛ ያሉ ሰዎች በእኔ ስም የተወከሉ ስለሆኑ፥ አሁን ደግሞ ከፓርቲው ስለወጡ ወይም ሐላፊነታቸው ስላጡ፥ የመንግስት ስልጣናቸውም እንዲሁ አብቅቷል ሊል ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል።  

ምክንያቱ ደግሞ የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነትን የተፈራረሙት "ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት ስለሆኑ በህወሓት ስም ወደ ግዚያዊ አስተዳደሩ የገቡ ሰዎች ላይ ውክልናዬ አንስቻለሁ ሊል ይችላል። ይህ በቀጣይ ሊከሰት የሚችል አንድ ግምት ነው" በማለት አስረድተዋል። 

የህወሓት አመራሮች ክፍፍል እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈጠረ ውዝግብ ሥጋት ፈጥሯል

ከዚህ ውጪ ሌሎች የቢሆን ትንተና የሚያስቀምጡት የሕግ ምሁሩ አቶ ተኽሊት ገብረመስቀል፥ ዝቅተኛ ዕድል ቢኖረውም እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ ግዚያዊ አስተዳደሩ ባለበት እንዲቀጥል መግባባት አልያም ያለው ድርሻ መከፋፈል፦ ሌሎች በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ለውጦች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስቀምጣሉ።

14ኛው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ
14ኛው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ሥራ አስፈፃሚ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽን መርጧል። ምስል Million Haileslasse/DW

ይህ ሁኔታ ጨምሮ በአጠቃላይ በትግራይ ያለው የፓለቲካ እንቅስቃሴ አሳሳቢ አድርገው የሚያስቀምጡት እኚሁ የሕግ ምሁር፥ የአስተዳደር መዋቅር እንዳይጠናከር ዕንቅፋት የሚፈጥር፣ በቀንተቀን የዜጎች ኑሮ ላይም ስጋት የሚፈጥር ፓለቲካዊ ሁኔታ ትግራይ ውስጥ እየታየ መሆኑ አቶ ተኽሊት ይናገራሉ።

የሕግ ምሁሩ ተኽሊት "ይህ ሁኔታ የአስተዳደር መዋቅሩ እንዳይሰራ፣ የቀን ተቀን ስራዎ እንዳይከውን ዕንቅፋት የሚፈጥር፣ ሁለት ሶስት መንግስታት እንዳሉ ዓይነት የሚያስመስል በተጨማሪም አሰላለፉ ለመገመት የሚያስቸግር፣ በሁሉ መልኩ እርግጠኛነት እንዲጠፈ የሚያደርግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። "የትግራይ ህዝብም፥ በእንቅስቃሴው እርግጠኛ ሆኖ ስለቀጣይ የሚያቅድበት ዕድል የሚያጠብበት ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው" ሲሉ አክለዋል። 

ትላንት በተጠናቀቀው የህወሓት ጉባኤ ዘርያ በጉባኤ ካልተሳተፉ አካላት ማብራርያ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች ብንደውልም ለግዜው አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር