ጆሮ ቆራጩና ሌሎች የህፃናት ማስፈራሪያዎች | ባህል | DW | 09.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ጆሮ ቆራጩና ሌሎች የህፃናት ማስፈራሪያዎች

ተረቶቻችንና ለህፃናት የምንነግራቸው ታሪኮቻችን መልካም ስብዕናን የሚቀርፁ የመሆናቸውን ያህል አደገኞች የሆኑም ይበዛቸዋል። ጆሮ ቆራጩ፣ አያ ጅቦ፣ እና ጭራቅ እንዲሁም ሌሎች ተረቶች በአብዛኞቻችን የህፃንነት ዘመን በአዕምሮዋችን ተቀርፀው ለዘመናት አብረውን የዘለቁ የህፃንነት ጊዜ አስፈሪ ታሪኮች ናቸው። እንደ ስነልቦና ጠበብት ከሆነ

እነዚህ በልጅነት ዘመን የሚነገሩ አስፈሪ ታሪኮች ቢያንስ ሁለት አበይት አሉታዊ ነገሮችን በህፃናት የወደፊት ስብዕና ላይ እስከወዲያኛው ማስረፃቸው አይቀርም ብዙዎቻችን ምድጃ ዳር ሆነን ስንሰማቸው ኋላም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲነገሩን የነበሩ ተረቶች በአብዛኛው ከማማለል ይልቅ አስፈሪነታቸው የጎሉ ነበሩ ይለናል ደራሲና አንጋፋው ጋዜጠኛ አበራ ለማ። በእርግጥም አሁንም ድረስ እነዚያ ተረቶች ቅርጽና መልዕክታቸው ሳይቀየር መነገራቸው እንደቀጠለ ነው።

ተረት አለያም ሌሎች ለህፃናት የሚነገሩ ታሪኮች በጊዜና በአድማስ የሚገደቡ አይደሉም። ለህፃናት የሚነገሩ ተረቶችም ሆኑ የስነቃል ትሩፋቶች ህፃናት ጠልቀው ሩቅ በሚሄዱበት የምናብ ዓለም ውስጥ ትተው የሚያልፉት አሻራ ለዘመናት የማይደበዝዝ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በእርግጥ ድፍረትን፣ ቆራጥነትን፣ ልግስናን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልን፣ አስተዋይነትን፣ ብልሀትን የመሳሰሉትን አዎንታዊ ስብዕናዎችን የሚያጎሉ ታሪኮች ሊበረታቱ ይገባል።

Strohmänner auf dem Schweizer Karneval

ህፃናትን በተለያዩ ምስሎች፣ ተረቶች አለያም አነጋገር ይሁን በማንኛውም መልኩ ማስፈራራት በህፃናት ስብዕና ላይ ሁለት አበይት አሉታዊ ነገሮችን ይፈጥራል የሚሉን ደግሞ ዶ/ር አበባው ምናዬ ናቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለይ የማኅበረሰብ ሳይኮሎጂን የሚያስተምሩ የስነ-ልቦና መምህር ናቸው።

በምዕራቡ ዓለም ተረቶችና ታሪኮች መሰል አስፈሪ ታሪኮች ቢኖሩም ብዙውን ጊዜ ግን ኃይለኛ አውሬዎች ከሰው ልጆች ጋር ተላምደው በፍቅር ስምም ሆነው ሲኖሩ ይቀረፃል። ህፃናት ወደፊት ሲያድጉ አውሬዎቹን አጥፍተው በጆሮዋቸው ሎቲ እንዲያንጠለጥሉ ሳይሆን መንከባከብ እንደሚገባቸው ገና ከለጋነታቸው አንስቶ እንዲያስቡበት የማስተማሪያም ዘዴ ነው።

ለህፃናት በሚነገሩ ተረቶቻችንና ታሪካችን ውስጥ ግን አብዛኛዎቹ የዱር አውሬዎች እጅግ ክፉ እና በተገኘው መንገድ ሊወገዱ የሚገቡ ተደርገው ሲሳሉ ይስተዋላል። «እባብን ግደል በትሩን ወደ ገደል» እንዲሉ ማለት ነው።

ህፃናትን ከሚያስፈራሩ ተረትና ታሪኮቻችን ባሻገር ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችንም ቢሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የህፃናትን አንገት ከማቅናት ይልቅ የሚያስደፉት ይበዛሉ። በዕለት ተዕለት ንግግራችን መሀል እንደዘበት ሻጥ አድርገን የምናልፋቸው አባባሎች ህፃናቱን ሲያኮስሱና ሲያሳንሱ የሚስተዋልበትም ጊዜ አለ።

König der Löwen

ህፃናትን ፈሪ እና የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ከሚያደርጉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች መካከል በአማርኛ የተፃፉ የተወሰኑትን ሰማን እንጂ በመላ ሀገራችን በተለያየ ቋንቋ የሚነገሩ አባባሎች ውስጥም ይኸው ችግር በስፋት ይስተዋላል። ለአብነት ያህል በኦሮሚኛ ቋንቋና ባህል ውስጥም መሰል ችግር በብዛት ይስተዋላል ይለናል ባልደረባችን ጃፈር አሊ።

የህፃናት ማስፈራሪያ ውጤቱ በረዥም ጊዜ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ስለእዚህም ቤተሰብ፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመገናኛ አውታር ሰራተኞች፣ መንግሥት እና ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ሀላፊነት አለባቸው። «ጆሮ ቆራጩና ሌሎች የህፃናት ማስፈራሪያዎች» በሚል ያቀረብንላችሁን ሙሉ ጥንቅር ለማድመጥ ከታች የሚታየውን የድምፅ ማጫወቻ ይጫኑ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic