ጆርጅ ዊሐ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን አሸንፈዋል | አፍሪቃ | DW | 30.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ጆርጅ ዊሐ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን አሸንፈዋል

በላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የ51 አመቱ ጆርጅ ዊሐ አሸንፈዋል። ፓሪሴን ዠርሜን፣ ኤሲ ሚላን እና ቼልሲን ለመሳሰሉ የእግር ኳስ ክለቦች የተጫወቱት ዊሐ በፊፋ ኮከብ ተብለው የተሸለሙ ብቸኛው አፍሪቃዊ የእግር ኳስ ተጫዋች ናቸው። የላይቤሪያ ወጣቶች እንደ ፕሬዝዳንት ለውጥ ያመጡልናል ብለው ተስፋ ቢጥሉባቸውም ልምድ የላቸውም እየተባሉ ይተቻሉ።

በደስታ በተዋጡት ደጋፊዎቻቸው ፊት አዲሱ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ሲያነቡ ታዩ። ጆርጅ ዊሐ ይኽቺን ቅፅበት ለረዥም ጊዜያት ሲጠብቁ ቆይተዋል። ከዚህ ቀደም በተወዳደሩበት ምርጫ የተሸነፉት ዊሐ አሁን ግን በሰፊ የድምፅ ልዩነት አሸናፊ ሆነዋል። ደጋፊዎቻቸው በደስታ ጭፈራቸው መካከል የሚያወሩላቸው ታሪክ አላቸው። 

"በርካታ ሥሞች ሰጥተውት ነበር። አልተማረም ብቁም አይደለም ሲሉትም ነበር። ነገር ግን እኔ ስጠብቀው የነበረው ሰው ይኸ ነው። ሕልሜ ተሳክቷል። እጅግ ተደስቻለሁ። ጆርጅ ዊሐ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ሆኗል።" ይላል አንድ ደጋፊያቸው። 

የላይቤሪያ ምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በድጋሚው ምርጫ ከተሰጠው 98.1 በመቶ ድምፅ 61.5 በመቶውን ዊሐ ማግኘታውን አስታውቋል። ዊሐ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ተክተው በሚቀጥለው ወር የፕሬዝዳንትነት መንበረ- ሥልጣኑን ይረከባሉ። ከጎርጎሮሳዊው 1994 ዓ.ም. ወዲህ በላይቤሪያ እንዲህ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሲደረግ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ሰርሊፍ በምርጫ ሥልጣን ይዘው መንግሥት የመሩ የመጀመሪያዋ አፍሪቃዊት እንስት ናቸው።  


ዊሐ ከምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦዓካይ ጋር ሲፎካከሩ የለውጥ ተስፋ ምልክት ተደርገው ተቆጥረዋል። በነገራችን ላይ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ይልቅ የአገራቸው ፍቅር እንደሚበልጥባቸው ገልጠው መሸነፋቸውን አሜን ብለው የተቀበሉት ወዲያው ነበር።
"ለአገሬ ያለኝ ፍቅር ለሥልጣን ካለኝ ፍላጎት የበለጠ እና የጠነከረ ነው። ለዚህም የፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን አሸናፊ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጥምረት ተወካይ ጆርጅ ማኔሕ ዊሐን በስልክ ደውዬ እንኳን ደስ ያለዎ ብያቸዋለሁ። በማንኛውም መንገድ ልረዳቸውም ራሴን አዘጋጅቻለሁ። የዚህች መርከብ ካፒቴን ባልሆን እንኳ የመንግሥታችን መርከብ በሰላም እንድትሰግር ጥልቅ ምኞቴ ነው።"

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎችም ከቃላቸው አልወጡም። ጆሴፍ ቦዓካይ ሽንፈታቸውን በጸጋ መቀበላቸውን ባረጋገጡበት የሞኖሮቪያ አደባባይ የተገኘው ወጣት እንደሚለው በውጤቱ ሐዘን ተሰምቶታል። ግን ደግሞ ከአብላጫው ምርጫ አያፈገፍግም።

"በግሌ የምርጫውን ውጤት ተቀብያለሁ። ምክንያቱም የአብላጫው ውሳኔ በመሆኑ ምንም ማድረግ አንችልም። ዴሞክራሲ ማለት ይኸ ነው። ምንም አይነት መጥፎ ስሜት ቢሰማን እንኳ ልንቀበለው ይገባል። ስለዚህ አምባሳደር ጆርጅ ዊሐን የሚቀጥለው ፕሬዝዳንታችን አድርገን ተቀብለናል።"

በላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ የድሖች መንደር ተወልደው ያደጉት ዊሐ እውቅና ያገኙት በእግር ኳስ ተጫዋችነታቸው ነበር። ለትልልቅ የአውሮጳ የእግር ኳስ ክለቦች ተጫውተው ሥመ-ጥሩ ሆነዋል። ጡረታ ከወጡ አሊያም ጫማቸውን ከሰቀሉ በኋላ ፖለቲከኛ ሆነ ከአስር አመት በላይ ተንቀሳቅሰዋል። ቢመረጡ ሙስናን ለመዋጋት እና የአገሪቱን መዋዕለ-ንዋይ ለማነቃቃት ቃል መግባታቸው በድምፅ ሰጪዎች ዘንድ ትኩረት እንዲያገኙ አግዟቸዋል። 

ጥሩ ጥሩ መንገዶች እንዲኖሩን ጥረት አደርጋለሁ። ለዜጎች ሥራ እንዲፈጠር አደርጋለሁ። ለላይቤሪያውያን ቃል የገባሁትን እሰራለሁ። ምክንያቱም ይህቺ አገር እድገት ያስፈልጋታል። ላይቤሪያ ከአፍሪቃ ጥንታዊ አገሮች አንዷ ናት። ይሁንና በቂ መንገድ እንኳ የላትም። አገሪቱን እርስ በርስ የሚያገናኙ መንገዶች መገንባታቸውን እከታተላለሁ።"

ዊሐ ለምክትል ፕሬዝዳንትነት የመረጧቸው ጄዌል ሐዋርድ ቴይለር የላይቤሪያ አምባገነን መሪ የነበሩት የቻርልስ ቴይለር የቀድሞ ባለቤት መሆናቸው ግን ጥርስ አስነክሶባቸው ጥርጣሬ ውስጥም ጥሏቸው ነበር። ቴይለር ፈፅመዋቸዋል በተባሉባቸው ወንጀሎች የ50 አመታት እስር ተበይኖባቸው በብሪታኒያ ማረሚያ ቤት ናቸው። በእርግጥ ጥርጣሬው ዛሬም ከተቃዋሚዎቻቸው እና ታዛቢዎች ምናብ ገሸሽ አላለም። እርሳቸው ግን ምርጫቸውን የሚከላከሉባቸው ምክንያቶች አሏቸው።

"ጥሩ ምርጫ ነው። በምክር ቤቱ ውስጥ የሥራ ባልደረባዬ ነች። ጠንካራ ሰራተኛ ሴት ናት። አሁን የቻርልስ ቴይለር የቀድሞ ባለቤት ናት። ብቁ እና አዋቂ ላይቤሪያዊት ናት። ላይቤሪያውያንም ይወዷታል። ከዚያ ባሻገር በፆታ እኩልነት አምናለሁ። እንደማስበው ከሆነ ምክትል ፕሬዝዳንቴ ሴት መሆኗ መልካም ነገር ነው።"

የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ (ECOWAS) እና በላይቤሪያ የአውሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑካን ቡድን የዕለተ ሐሙሱ የድምፅ አሰጣጥ ሰላማዊ እና አጥጋቢ ነበር ብለዋል። 250,000 ሰዎች የተገደሉባቸው ሁለት የርስ በርስ ጦርነቶች አሰቃቂ ትዝታ ላልራቃት ላይቤሪያ ይኸ መልካም ዜና ይመስላል።

ላይቤሪያ በጎርጎሮሳዊው 1847 ዓ.ም. ከዩናይትድ ስቴትስ እና የካሪቢያን ደሴቶች ነፃ በወጡ ባሪያዎች የተመሰረተች ጥንታዊት አገር ናት። ከየርስ በርስ ጦርነት ማግሥት በተካሔደ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ላይቤሪያን ከገባችበት ማጥ መንጭቀው ያወጡ የተከበረ ሥም ያላቸው ፖለቲከኛ ናቸው። የዛኑ ያክል ግን ወይዘሮዋ ሙስናን መግታት ተስኗቸዋል አገሪቱን ለሚፈትነው ድሕነትም መፍትሔ ማግኘት አልሆነላቸውም እየተባሉ ይተቻሉ። ድንገት ብቅ ብሎ ላይቤሪያ እና የምዕራብ አፍሪቃ አገራትን ያመሰው የኢቦላ ተኅዋሲ ወረርሽኝ ሰርሊፍን የፈተነ ሌላው ጉዳይ ነበር። የፖለቲካ ሥራው ለዊሐ እንደ ጎል ማስቆጠር ይቀላቸው እንደሁ ወደ ፊት ይታያል። 

እሸቴ በቀለ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ