ጅቡቲ ፤ የአፍሪካ ቀንድ በር | አፍሪቃ | DW | 26.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ጅቡቲ ፤ የአፍሪካ ቀንድ በር

የዩናይትድ ስቴትስ እና የፈረንሳይ ጦር ጅቡቲ ከሰፈረ አመታት ተቆጠሩ። አሁን ቻይናም በአፍሪቃ ቀንድ ጅቡቲ፤ የጦር ሰፈር የምትከፍት ከሆነ ይህ ለምስራቅ አፍሪቃዊቷ ትንሽ ሀገር የገንዘብ ምንጭ ቢሆንም፤ የራሱን ፈተና እና ችግር ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው።

ጅቡቲ ውስጥ 800 000 የሚጠጋ ህዝብ ይኖራል። የቀድሞው የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ጅቡቲ ፤ የዓለም ስልታዊ ጠቀሜታ ካላቸው የዓለም ሃገራት አንዷ ናት። ቦን የሚገኘው «ዓለም ዓቀፍ የልውውጥ ማዕከል» የተሰኘው ድርጅት ባልደረባ ሚሻኤል አሽኬናዚ « ጅቡቲን የተቆጣጠረ በቀይ ባህር ላይ ብቻ ሳይሆን በአለም ገበያ ላይም ጭምር ግንባር ቀደም ሚና ይኖረዋል ይላሉ፤
« ጅቡቲ ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ከምትጠቀምባቸው ዋነኛ ወደቦች አንዷ ናት ። ለአንድ ትልቅ ሀገር በዋነኛ ወደብነት የምታገለግል እንደመሆንዋ ከዚህ የምትገኛቸው ጥቅሞች በሙሉ እያጣጣመች ነው »
80 ከመቶ የሚሆነው ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው እቃ መድረሻና ማመላለሻ ማዕከል የዶራሌህ ወደብ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጅቡቲ የቀውስ ረመጥ ውስጥ ላሉ የአፍሪቃ ፣ የእስያ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የምትቀርብ ስልታዊ ቦታ ናት። « ለዓለም አቀፍ የንግድ መንገድ እንዲሁም « አሸባሪነትን» ለመዋጋት ጅቡቲ ምናልባትም በአፍሪቃ ቀንድ ካሉ ሀገራት በአሁኑ ሰዓት ዋንኛዋ ሀገር ናት።»


ይላሉ፣ በርሊን የሚገኘው የሳይንስ እና የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ አኔተ ቬበር ። የጅቡቲን አስፈላጊነት ቻይናም ተረድታለች። ስለሆነም ቻይና በሀገሪቱ የጦር ሰፈሯን ማቋቋም የምትችልበትን መንገድ እያመቻቸች እንደሆነ ተሰምቷል። የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ በግንቦት ወር ለዜና ምንጭ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደገለፁት፤ ፔኪንግን በደስታ ሊቀበሉ ዝግጁ ናቸው። የቻይና መንግሥት ግን በጅቡቲ ጦሩን ስለማስፈሩ በይፋ አላረጋገጠም ወይም አላስተባባለም። ባለስልጣናቷም የ ቻይና ለአካባቢው መረጋጋት የበኩሏን ሚና እንደምትጫወት ከመናገር ውጭ ሌላ ያሉት ነገር የለም ።
እኢአ በ2008 ዓም ቻይና የባህር ላይ ወንበዴዎችን ለመዋጋት መርከቦች ወደ ሶማሊያ የባህር ዳርቻ አሰማርታለች። ከ 2010 ዓም አንስቶ ደግሞ ቻይና በየመን አቅራቢያ በአደን ባህር ሰላጤ አለም አቀፋዊ ሚና መጫወት ትሻለች ይላሉ ሚሻኤል አሽኬናዚ።


« ቻይና ላለፉት 10 ዓመታት፤ ምናልባትም ከዚያም በላይ አፍሪቃ ውስጥ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ አፍስሳለች። ይህ በርግጥ ትርፋ ለማግኘት ነው፤ ከዚህ የበለጠ ግን ዋናው ነገር የአፍሪቃን ጥሬ ሀብት ለመቆጣጠር ነው። እናም የጦር ሰፈር አፍሪቃ ውስጥ መክፈት፤ ከቻይና ባህርያት አንዱ የሆነው የረዥም ጊዜ እቅድ የመጀመሪያው ርምጃ ነው እለዋለሁ ። »
የቻይና እቅድ ፤ የበለፀጉት ሀገራት ጅቡቲ ውስጥ ለአመታት ሲያደርጉት የነበረ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ እኢአ ከ 2002 ዓም ጀምሮ ጅቡቲ ውስጥ የጦር ሰፈር አላት። ከዚህ በተጨማሪ ፈረንሳይ፣ ጃፓን እና የአውሮፓ ህብረት የጦር ሰፈር አላቸው። ከዚያም ሆነው በሶማሊያ የባህር ዳርቻ ሲፈፀሙ የነበሩ የባህር ላይ ውንብድናን ሲዋጉ እንደነበር ይታወሳል። ዩናይትድ ስቴትስ ከጅቡቲ ሆና በሰው አልባ አይሮፕላን በየመን እና በሶማሊያ በሚገኙ አክራሪ የሙስሊም ቡድናት ላይ ጥቃት ታካሂዳለች። በቅርቡ ደግሞ የቻይና ጦር በዚያ ከሰፈረ አኔተ ቬበር ስጋት አላቸው ።
« ይህ ከሆነ ምናልባት ቀድመው ቦታው ላይ ከሚገኙት ጋር ከፍተኛ ግጭት ሊነሳ ይችላል።»
ለጅቡቲ መንግሥት የውጭ የጦር ሰፈሮቹ ዋንኛ የገንዘብ ምንጭ ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሰፈር ብቻ በዓመት 60 ሚሊዮን ዶላር ያስገኛል። ይሁንና ብዙሃኑ የጅቡቲ ህዝብ የገንዘቡ ተጠቃሚ አይደለም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህዝብ ኑሮ መመዘኛ ጅቡቲ ከ187 ሀገራት 170ኛው ደረጃ ላይ ናት ። በተመድ መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት ከ 21 000 የሚበልጡ የሶማሊያ ስደተኞች ጅቡቲ ይገኛሉ። 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ውጊያ ከሚካሄድባት ከየመንም ስደተኞች በየዕለቱ ጅቡቲ ይገባሉ።
ዩሊያ ሀን
ልደት አበበ

ተዛማጅ ዘገባዎች