ጅምላ እስር ያሰጋቸዉ ወጣቶች | ባህል | DW | 21.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ጅምላ እስር ያሰጋቸዉ ወጣቶች

ለከተሜ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች የሰሞኑ ሁኔታ መረጋጋትን አልፈጠረላቸዉም። በየቦታዉ የሚሰማዉ የእስር ዜና ጭንቀትን እና ጥርጣሬን ፈጥሮባቸዋል። የተወሰኑት በየአካባቢያቸዉ መደበቅን የመረጡ ሲሆን ጥቂቶቹ ደግሞ ቀያቸዉን ለቀዉ ከዘመድ አዝማድ ተጠግተዉ እስርን ለማምለጥ ሞክረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:53 ደቂቃ

ጅምላ እስር ያሰጋቸዉ ወጣቶች

በከተሞች የሚኖሩ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያን ፍርሃት ሰቅዞ ይዟቸዋል፡፡ በሰፈር- በመንደራቸው፣ በቤተሰብ- ጎረቤታቸው የሚያዩት እና የሚሰሙት እስራት ነገም የእነርሱን ቤት ላለማንኳኳቱ እርግጠኞች አይደሉም፡፡ የሸሹት የመሰላቸው የእስር ወሬ ቴሌቪዥን እና ሬድዮናቸውን ሲከፍቱ ተከትሏቸው ይመጣል፡፡ “በዚህን አካባቢ ይህን ያህል በዚያ ደግሞ ያን ያህል በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው” የሚል አስጨናቂ ዜና ጋር ይፋጠጣሉ፡፡ እንደመቀጣጫ በማስረጃነት የሚቀርቡ የዕድሜ እኩዮቻቸውን በቴሌቪዥን መስኮት እያዩ ይሸበራሉ፡፡ ፍርሃት፣ ስጋት፣ ጥርጣሬ፤ መጪውን ካለማወቅ ጋር ተዳምሮ አየሩን አክብዶባቸዋል፡፡

መንግስትን ተቃውመው ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ በወጡት ላይ ጭንቀቱ ይበረታል፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገመንግስታዊ መብታቸውን እየተጠቀሙ እንደሆነ የሚያስቡት እነዚህ ወጣት ሰልፈኞች በየማህበራዊ ድረ ገጹ ፎቶዎቻቸው ሲወጡ እና ቪዲዮዎቻቸውን ሲያጋሩ በልበ ሙሉነት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ጣጣው ያስፈራቸዋል፡፡ በመላው ሀገሪቱ የታወጀው እና ለትርጉም ክፍት የሆኑ አሻሚ አንቀጾች ያዘለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጭራሹኑ ከህግ አወጣጥ መንፈስ በተቃራኒ ወደኋላ ሄዶ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተደረጉ የሁከትና የብጥብጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሳተፉትን እንደሚቀጣ ማወጁ ክፉኛ አስደንግጧቸዋል፡፡

ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ የተጋቡ ወጣቶች መሸሸግ ግዴታቸው ሆኗል፡፡ በመስከረም መጨረሻ ከፍ ያለ አመጽ እና ተቃውሞ ካስተናገዱ የኦሮሚያ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ምስራቅ ሸዋ ዞንም የሆነው ይሄው ነው፡፡ አስር ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር የሚገኝበት ይህ ዞን “ከአንድ ወረዳ በስተቀር በሁሉም ላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ወድመት” መድረሱን የዞን ፖሊስ በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡ ፖሊስ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች ሆቴሎችን፣ የአስተዳደር ጽህፈት ቤቶችን እና ተሸከርካሪዎችን አጥቅተዋልም ብሏል፡፡ 

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዞኑ ነዋሪ ወጣቶቹ እና ሌሎች ለተቃውሞ የወጡ ግለሰቦች በኢሬቻ በዓል ወቅት የደረሰውን እልቂት እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ማንሳታቸውን ያወሳሉ፡፡ በወቅቱ በነበረው ተቃውሞ ንብረት መቃጠሉን ያንን ተከትሎም እርሳቸው በሚኖሩበት ወረዳ በርካቶች መታሰራቸውን ይናገራሉ፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች እንደሆኑ እና ሸሽተው የተደበቁ እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ሽሸጋው በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚታይ እንደሆነ ጭምር ያስረዳሉ፡፡


የተደበቁ ወጣቶች

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የወጣው መመሪያ በሁከት እና ብጥብጥ ውስጥ በቡድን ወይም በግል ተሳትፈዋል ያላቸውን ግለሰቦች በ10 ቀናት ውስጥ በፍቃደኝነት እጃቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡ እጁን በገዛ ፍቃዱ ለፖሊስ የሰጠ ሰው “እንደ ወንጀል ተሳትፎው ቀላልና ከባድነት አሊያም ዋና ፈጻሚና አባሪ ተባባሪ መሆኑ ታይቶ” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመተግበር በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አማካኝነት “የተሃድሶ ትምህርት” ተሰጥቶት እንደሚለቀቅ ቃል ገብቷል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ 1‚ 600

 ገደማ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በፍቃደኝነት እጃቸውን መስጠታቸውን አስታውቆ ነበር፡፡ 

ይህን መሰሉ የጅምላ እስራት ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመደንገጉም በፊት በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ለወራት ሲደረግ መቆየቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ያሉ ተሟጋቾች አንድ ዓመት በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በሺህዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውን በየመግለጫዎቻቸው ጠቅሰዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከታሰሩባቸው ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ባህር ዳር ነዋሪ የነበረው ወጣት ድንገተኛ እስርን ፍራቻ ወደ አዲስ አበባ ለመሸሽ መገደዱን ይናገራል፡፡ ነገሮች እስኪረጋጉ በሚል ከሶስት ጓደኞቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ ያቀናው የባህር ዳር ወጣት በመዲናይቱ ለሁለት ወራት መቆየቱን ይገልጻል፡፡ 


ሽሽት ወደ አዲስ አበባ

ዘንድሮ ዩኒቨርስቲ ለመግባት እየተሰናዳ የነበረው ይህ ወጣት አዲስ አበባ ከሰው ተጠግቶ እንዲቆይ በመገደዱ መቸገሩን ይናገራል፡፡ ለአካባቢው ባዳ በመሆኑ አብዛኛው ጊዜ ያሳልፍ የቤት ተቀምጦ እንደነበር ያስረዳል፡፡ ለመሸሸጊያነት የመረጣት አዲስ አበባም ብትሆን ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በፍርሃት ቆፈን አላመለጠችም፡፡ ወጣቶቿ ውጭ ውጭ ማለትን ትተው ከቤት መከተት አዘውትረዋል፡፡ በፖለቲካ እና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳባቸውን ከመተፈንስ ተቆጥበዋል፡፡ ለስራ እንኳ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደልብ ማግኘት ቸግሯቸው የሆቴል “ዋይ ፋይ” አገልግሎት ጠኚ ሆነዋል፡፡   

በመዲናይቱ ያረበበውን ፍርሃት ይዞ በዚህ ሳምንት አባይን የተሻገረው የባህር ዳሩ ወጣት ወደ ቀዬው ቢመለስም አሁንም እታሰራለሁ የሚለው ስጋቱ ግን ከውስጡ አልወጣም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቋፍ የነበረውን ስጋቱን የበለጠ እንዳባባሰው ይገልጻል፡፡ በአካባቢያቸው እስራት መቀጠሉን፤ ቀደም ሲል በብርሸለቆ ታስረው የነበሩ እንደተያዙ መስማቱን ነገር ግን ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቅ ያብራራል፡፡ አብዛኞቹ ታሳሪዎች ግን ወጣቶች መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡

 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ ቀደም ብሎ አንድ ሺህ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውላ የነበረችው ሰበታም እንደ ምስራቅ ሸዋ ዞን እና ባህርዳር ሁሉ ወጣቶች ዋነኛ ኢላማ የሆኑባት ነች፡፡ ይህንኑ የሚያረጋግጡት የከተማዋ ከንቲባ አቶ አራርሳ መርዳሳ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች አንግበዋቸው የነበሩ ጥያቄዎች በመልካም አስተዳደር እና ሥራ አጥነት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እንደሆነ ይናገራሉ። 


እስር እና የወጣቶች ጥያቄ

የተወሰኑ ወጣቶች “ከጠላት እና አጥፊ ኃይል ጋር አብረው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚያነሱትን ለራሳቸው አላማ መጠቀሚያ” አድርገዋቸዋል ይላሉ ከንቲባው፡፡ ነገር ግን ተቃውሞቹ ላይ በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ እና የፋብሪካ ተቀጣሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን አይክዱም፡፡ በየቦታው የሚንተከተኩት የወጣቶቹ ጥያቄዎች በአገር ሽማግሌዎች ዘንድ ሳይቀር ቦታ አግኝተዋል፡፡ መንግስት ለጥያቄዎቹ  ምላሽ እንዲሰጥ እየጠየቁ የሚገኙት የምስራቅ ሸዋ የአገር ሽማግሌዎች ጎን ለጎን እየተፈለጉ ለሚገኙ ወጣቶች አማላጅ ሆነው ምህረት ፍለጋ ባለስልጣናት ደጅ ቆመዋል፡፡ 

መንግስት ተጠርጣሪዎች እጃቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንዲሰጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ቀናቶች ቀርተውታል፡፡ ከዚያ በኋላ በሁከት እና ብጥብጥ የጠረጠራቸውን “በጅምላ ማሰር ይቀጥላል ወይንስ ሌላ መፍትሄ ይፈልጋል?” የሚለው ጉዳዩን በአትኩሮት የሚከታተሉ ወገኖች ጥያቄ ነው፡፡ እስከዚያው ግን “ድብብቆሹ” ይቀጥላል፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች