ጄኔራሎቹና የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት | አፍሪቃ | DW | 28.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ጄኔራሎቹና የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት

የተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል በደቡብ ሱዳን የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ሶስት አባላት ያሉት ቡድን እንደሚያቋቁም አስታውቋል። ደቡብ ሱዳንም ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከሚመረምረው ቡድን ጋር እንደምትተባበር አስታውቃለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:15
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:15 ደቂቃ

የደቡብ ሱዳን ሰላም

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር በበኩላቸው ወደ ጁባ ለመመለስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ደቡብ ሱዳንን «መልሶ ለመገንባት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመቀበል» ወደ ጁባ ከማቅናታቸው በፊት ግን የጦር መኮንኖቻቸውን አስቀድመው ልከዋል።

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር ወደ ደቡብ ሱዳን ለመመለስ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። ዓርብ መጋቢት 26/2008 ዓ.ም. ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር የተገናኙት ሪየክ ማቻር «አገራችንን ለማሳደግ እና መልሶ ለመገንባት የተጣለብኝን ኃላፊነት ለመቀበል» ተመልሼ ለመሄድ ተሰናድቻለሁ ሲሉ ተናግረዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወደ ጁባ ከመጓዛቸው በፊት አስቀድመው 25 የጦር ጄኔራሎችን ልከው ነበር። የጦር ጄኔራሎቹ ከዋና ከተማዋ ጁባ መድረሳቸውን የደቡብ ሱዳን መንግስት ቃል-አቀባይ ሚካዔል ማኩይ አረጋግጠው እርምጃው ለሰባት ወራት ለተገተረው የሰላም ስምምነት ትግበራ ላቅ ያለ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ሪየክ ማቻር ወደ ጁባ ለመጓዝ ካስቀመጧቸው ቅድመ-ሁኔታዎች መካከል ወደ 3,000የሚጠጉ ወታደሮቻቸው እና ፖሊስ በዋና ከተማዋ ሲሰማራ እንዲሁም ተጨማሪ 1,200ፖሊሶች በቦር፤ማላካል እና ቤንቱ ሲዘምቱ ብቻ መሆኑን አስታውቀው ነበር። ደቡብ ሱዳናውያኑ የአገራቸውንና የህዝባቸውን ምስቅልቅል ለመፍታትም ይሁን ለይስሙላ በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስት አደራዳሪነት በተረቀቀው የሰላም ስምምነት ትግበራ ሂደትን እየተከተሉ ነው። በደቡብ ሱዳን ከስምንት መቶ በላይ የጦር ጄኔራሎች ሳይኖራት አይቀርም የሚሉት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ስልታዊ ጥናት ማዕከል የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ የስልጣን ፉክክሩ በወታደራዊ አስተሳሰብ የተቃኘ መሆኑ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት እንቅፋት መፍጠሩን ይተቻሉ።

ነጻ በወጣችበት ዓመት 745 የጦር ጄኔራሎች የነበሯት ደቡብ ሱዳን ከነዳጅ የምታገኘውን ገቢ የአገሪቱን የጦር ሰራዊት አባላት እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ታማኝነት ለመግዛት እንደምትጠቀምበት የፖለቲካ ሳይንቲስቱ አሌክስ ደ ዋል ጠቁመዋል። አሌክስ ደ ዋል አገሪቱ በደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ጦር (የአገሪቱ ብሔራዊ ጦር) እና ሌሎች ታጣቂዎች ስር ለሚገኙ ወደ 350,000 የሚጠጉ ነፍጠኞች በወር ከ75-150 ዶላር እንደምትከፍል በአዲሱ መጽሃፋቸው አትተዋል።

ከሪየክ ማቻር ጎን የተሰለፉት የጦር መኮንኖች እና ወታደሮች በሰላም ስምምነቱ መሰረት ወደ ጁባ ሲያቀኑ የታጠቁትን ከባድ የጦር መሳሪያዎች ይዘው ለመጓዝ መወሰናቸው በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል ከቁልፍ ልዩነቶቻቸው መካከል የሚጠቀስ ነው። ደቡብ ሱዳን ጦር ሰራዊትም ይሁን የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር በንዌር እና ዲንቃ ጎሳዎች ብቻ የበላይነት መያዙን የሚተቹት አቶ አበበ አይነቴ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ግለሰቦች አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ የመታደግ ፍላጎት አጠራጣሪ እንደሆነ ይናገራሉ።

የምስራቅ አፍሪቃን ለሚከታተሉ በርካታ የጸጥታ እና ደህንነት ተንታኞች በአንድ ወቅት በአፍሪቃ ህብረት፤የተ.መ.ድ. እና ምዕራባውያን ከፍተኛ ትኩረት ተሰጠቶት የነበረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት በተጠበቀው ፍጥነት መተግበር አቅቶት ተገትሯል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic