ጂዳ ሆስፒታል ዓመታትን ያስቆጠረዉ ኢትዮጵያዊ | ኢትዮጵያ | DW | 24.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ጂዳ ሆስፒታል ዓመታትን ያስቆጠረዉ ኢትዮጵያዊ

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሳዑዲ አረቢያ በሃኪም ቤት ዉስጥ ከሰመመን ሳይነቃ የተኛዉ ኢትዮጵያዊ እናት ለተፈጠረዉ የሕክምና ስህተት እንዲከፈላቸዉ የታዘዘዉን ካሳ እንደማይቀበሉ አስታወቁ። 2.4 ሚሊዮን ሪያል ወይም 13 ሚሊዮን በላይ ብር የካሳ ክፍያ የተወሰነላቸው እናት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:25

ጂዳ ሆስፒታል ዓመታትን ያስቆጠረዉ ኢትዮጵያዊ

ወ/ሮ ሐሊማ ሙዘሚል ሁሴን ከአመታት በፊት የአራት አመት ልጃቸውን በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ ወደሚገኘው የሱሌይማን ፋኬህ ሆስፒታል ሲወስዱ ለአነስተኛ ቀዶ ህክምና ነበር። መሐመድ አብዱል አዚዝ የመተንፈስ ችግር ስለነበረበት ለአነስተኛ ቀዶ ህክምና በእግሩ ሆስፒታል የገባው መሐመድ አብዱል አዚዝ ያህያ የገጠመው ግን ለእናቱ ዱብ እዳ ነበር። መሐመድ ለአስር ደቂቃ ከገባበበት የቀዶ ህክምና ክፍል ሲወጣ ራሱን አያውቅም ነበር። እናቱ «ተኝቷል ብዬ ነበር።» ሲሉ በጊዜው ሁኔታውን ቀለል አድርገው መረዳታቸው ያስታውሳሉ። የህክምና ባለሙያ ጠርተው ልጃቸው ያለበትን ሁኔታ ሲጠይቁ ግን ነገሩ ከባድ ሆነና የአስቸኳይ የህክምና ባለሙያዎች ክትትል አስፈለገው። ለሶስት ወራት ጥብቅ የህክምና ባለሙያዎች ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ እንዲተኛ የተደረገው የወ/ሮ ሐሊማ ሁለተኛ ልጅ የሆነው መሐመድ ላለፉት ዘጠኝ አመታት አልነቃም። «እስከ ዛሬ ድረስ አልነቃም፤አይንቀሳቀስም፤አይሰማም፤አያይም።» የሚሉት እናት ስለልጃቸው ሲናገሩ እንባ ይቀድማቸዋል።

ሐዘን የገባቸው እናት በመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ የቆየውን ልጃቸውን ህይወት ለመመለስ ይመለከታቸዋል ያሏቸውን ሁሉ ደጅ ሲጠኑ አመታት አልፈዋል። ከመካ ከተማ እየተመላለሱ ልጃቸውን ሲያስታምሙ የቆዩት ወ/ሮ ሐሊማ በጅዳ ቤት ለመከራየት ተገደዋል። ልፋታቸው ጠብ ያደረገው ነገር ግን የለም። የመሐመድ አብዱል አዚዝን የህክምና ሂደት በቅርብ የሚከታተለው ጂዳ የሚገኘዉ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ «ይህ ጉዳይ በሳዑዲ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል የዶክተሮች ኮሚቴ ተቋቁሞ ተጣርቶ በመጨረሻ የተገኘው ውጤት የሐኪሞች ስህተት መሐመድ ለዚህ እንደደረሰና ያለበት ሁኔታ ተስፋ እንደሌለው።» መገለጹን ተናግሯል።

Äthiopische Flüchtlinge in Saudi

ወ/ሮ ሐሊማ በሐኪሞች ስህተት ለዘጠኝ አመታት መንቃት ላልቻለው ልጃቸው ፍትህ ፍለጋ በሳዑዲ አረቢያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሱሌይማን ፋኬህ ሆስፒታል ደጃፍ ሲንከራተቱ ሪያድ ከተማ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ይሁን በጅዳ ከሚገኘው ቆንስላ ተገቢ ድጋፍ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ። «እኔ ካሳ ምን ያደርግልኛል? ልጄ አልጋ ላይ እያደገ ነው።» የሚሉት ወ/ሮ ሐሊማ የሳዑዲ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመሐመድን የህክምና ሂደት መርምሮ እንዲከፈላቸው የወሰነው 2.4 ሚሊዮን ሪያል ወይም 13 ሚሊዮን በላይ ብር የካሳ ክፍያ ትርጉም አጥቶባቸዋል። ለመቀበልም ዝግጁ አይደሉም።

የሳዑዲ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የካሳ ክፍያ ከፈረደ በኋላ መሐመድን ከተኛበት ክፍል በወታደሮች ለማስወጣት መሞከሩን ወ/ሮ ሐሊማ ተናግረዋል። የሱሌይማን ፋኬይ ሆስፒታልም ወ/ሮ ሐሊማ ልጃቸውን ሲያስታምሙ ለማረፊያነት የፈቀደላቸውን አንድ ክፍል የመኖሪያ ቤት እንደቀማቸውም ተናግረዋል። መሐመድ አብዱል አዚዝን በተኛበት አልጋ ላይ የተመለከተው ነብዩ ሲራክ «በመሳሪያ ነው የሚተነፍሰው፤ምግብ አይበላም፤ህይወቱ የተበላሸ ሆኗል።» በማለት ሲናገር ድምጹ የውስጡን ሐዘን ያሳብቃል። «እንደ ህጻን ልጅ አይቦርቅም፤ እንደ ህጻን ልጅ የሚያስፈልገውን አይናገርም፤ቤተሰቦቹንም አያቅም።» የሚለው ነብዩ የመሐመድ አብዱል አዚዝ ጉዳይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መድረሱን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

ያለ ህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መተንፈስም ሆነ መመገብ የማይችለው መሐመድ አብዱል አዚዝ ከተኛበት ክፍል እንዲወጣ የሱሌይማን ፋኬህ ሆስፒታል እንዲወጣ ግፊት እያደረገ ነው። ወ/ሮ ሐሊማ ለልጃቸው እና ለመንገላታታቸው «ፍትህ እፈልጋለሁ» ሲሉ ሳግ እየተናነቃቸው ይናገራሉ።

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዘግይቶም ቢሆን እገዛ ማድረግ መጀመሩን ወ/ሮ ሐሊማ ተናግረዋል። በዚህ ዘገባ ላይ የኤምባሲውን አስተያየት ለማካተት ያደረግንው ጥረት ግን የስልክ ጥሪዎቻችን ምላሽ በማጣታቸው አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic