ጀነራል ሞተርስና የኦፔል ዕጣ | ኤኮኖሚ | DW | 04.11.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ጀነራል ሞተርስና የኦፔል ዕጣ

የአሜሪካው ታላቅ አውቶሞቢል አምራች ጀነራል-ሞተርስ በይዞታው የሚገኘውን የጀርመን ኦፔል ኩባንያ ለመሸጥ የነበረውን ዕቅድ መልሶ መሳቡ ለብዙዎች ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ሆኗል።

default

ጀነራል-ሞተርስ ኦፔልን እንደታቀደው ለአውስትሮ-ካናዳው የልዋጭ ዕቃ ኩባንያ ለማግና ለመሸጥ የነበረውን ዕቅድ መተዉን ያስታወቀው ትናንት ማምሻውን ነበር። የዴትሮይቱ ኩባንያ አስተዳደር በኦፔል ዙሪያ ያለ የአውሮፓ ንግዱን ራሱ ለመጠገን ሲወስን ለጀርመን መንግሥትና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ወገኖች ዕቅዱን እንደሚያቀርብ አስታውቋል። የኩባንያው ውሣኔ በተለይ ኦፔልን ከውድቀት ለማትረፍ በያመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የደሞዝ ጭማሪን ለመተው የተስማሙትን ሠራተኞች ሲበዛ ግራ የሚያጋባ ነው።

ጀነራል-ሞተርስ ኦፔልን ለማግና ለመሸጥ ማቀዱ በዚህ በአውሮፓና በተለይም በጀርመን የኩባንያው ቅርንጫፎች እንዳይዘጉ ሰግቶ ለነበረው ሠራተኛ ጥቂትም ቢሆን የተሥፋ ምንጭ ሆኖ ነው የቆየው። የኦፔል ሠራተኞች ኩባንያው በማግና ስር በአዲስ መልክ ከተቋቋመ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 265 ሚሊዮን ኤውሮ የደሞዝ ጭማር ለመተው ተስማምተው ነበር። ታዲያ ይህ ባለፉት ሣምንታት ጥቂት ሲጠረጠር፤ ሆኖም ግን ድንገተኛ የሆነው የጀነራል-ሞተርስ አስተዳደር ውሣኔ እጅግ አስከፊ ነው የሆነው። የጀርመን መንግሥት በውሣኔው የተሰማውን ቅሬታ ሲገልጽ የኦፔል ሠራተኞችም አዲሱን ዕቅድ አጥብቀው በመተቸት ላይ ናቸው።

የጀነራል-ሞተርስ ውሣኔ በአስተዳደር አካሉ ውስጥ የሚገኙት የማግና ዋነኛ ተቃዋሚዎች የሃይል ሚዛን ማየሉን የሚያመለክት ነው። በተለይም የማግናን ከሁለት የሩሢያ ሸሪኮች ጋር መጣመር የኩባንያውን የቴክኖሎጂ ዕውቀት ወደ ሩሢያ ሊያሾልክ ይችላል በሚል ጥርጣሬ ሲመለከቱ ለቆዩት የአስተዳደሩ አካል መሪ ለቴክሣሱ ኤድ-ዋይቴክር ትልቅ ድል ሆኖ መታየቱ አልቀረም። በመሆኑም በውሣኔው መርካታቸውን በከፍተኛ ስሜት ነው የገለጹት።

“ዕለቱ ታላቅ ነው”

ምክትላቸው ጆን ስሚዝም ቢሆን ባለፉት ሣምንታት ጀነራል-ሞተርስ ለምን በቴክኖሎጂ ቀደምት የሆነ አካሉን ይሸጣል? ሲሉ በማግና ላይ ከማተኮር ሲያስጠነቅቁ ነበር የቆዩት። ታላቁን የዲትሮይት ኩባንያ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ካስከተለው መዘዝ ለማላቀቅ በኦባማ መንግሥት የተቋቋመው የአስተዳደር አካል ዓባላት ኤክስፐርቱን ጀስቲን ሃይድን ጨምሮ ተመሳሳይ አቋም ነው ያንጸባረቁት።

“ኦፔል የጀነራል-ሞተርስ ማዕከላዊ አካል ነው። ይህ ደግሞ በሽያጭ ረገድ ብቻ ሣይሆን በምርምርና በቴክኖሎጂ ዕርምጃ ጭምር ነው። ይህ አመለካከት በአዲሱ የጀነራል-ሞተርስ አስተዳደር አካል ውስጥ ከወር ወደ ወር እየጠነከረ ነው የመጣው። ፕሬዚደንት ኦባማ በግብር ከፋዩ ሕዝብ ሰባ ሚሊያርድ ዶላር ከውድቀት በተረፈው ኩባንያ ላይ የስኬት ግዴታ ጥለዋል። ታዲያ ኦፔል በአውሮፓ ማዕከላዊ የአውቶሞቢል ገበያ ላይ የጀነራል-ሞተርስ አካል ሆኖ ካልቆየ የስኬት ዕድል ሊኖር አይችልም”

እንግዲህ ሃይድ አያይዘው እንደሚሉት ኦፔልን ለማግና አሳልፎ መሸጡ ለዴትሮይቱ ኩባንያ ትልቅ የፉክክር አቅምም የሚያሳጣ ነው። ጀነራል-ሞተርስ እንደ ጥቂት ዓለምአቀፍ ቀደምት አምራቾች በአውሮፓ የንግድ ዘርፉ ላይ ቁጥጥሩን ያጣ ነበር ማለት ነው።

“ሁሉም የዓለም ታላላቅ አውቶሞቢል አምራቾች በአውሮፓ ንግዳቸው ላይ ጥገኞች ናቸው። ምክንያቱም ለወደፊቱ የዓለም ገበያ ሞዴሎች ሁሉ የሚፈጠሩት በአውሮፓ ነው”

የጀነራል-መተርስ ፍላጎት ኦፔልን ይዞ መቆየት ከሆነ ኩባንያውን ከኪሣራ ለማዳን በፍጥነት በሚሊያርድ ኤውሮ የሚቆጠር ገንዘብ ማሰባሰብ ይኖርበታል። በተለይ ጀርመን የሰጠችውን የ 1,5 ሚሊያርድ ኤውሮ መሸጋገሪያ ብድር እስከያዝነው ወር መጨረሻ መመለሱ ግድ ነው የሚሆነው። እርግጥ ኩባንያው ቀደም ብሎ አስፈላጊውን ገንዘብ የማግኘት ስሌት ሳያደርግ አልቀረም። የጀርመን መንግሥት በአገሪ የሚገኙትን ፋብሪካዎች ሕያው አድርጎ ለማቆየት ሲል ኦፔልን ለማትረፍ ሶሥት ሚሊያርድ ኤውሮ ያወጣል ብሎ ይገምታል። ከዚሁ ሌላ ብሪታኒያ፣ ስፓኝና ፖላንድም ኦፔል ሙሉ በሙሉ በጀነራል ሞተርስ ሥር ከቆየና በአገሮቻቸው የሚገኙት የኦፔል ኩባንያዎች ካልተዘጉ ተጨማሪ ሚሊያርድ እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል። በዴትሮይቱ ውሣኔ ግልጽ ያልሆነው የኦፔል ትውልድ አገር በሆነችው በጀርመን በተለያዩ ከተሞች የሚገኙት ፋብሪካዎች ዕጣ ነው። በነዚህ ቦሁምና ካይዘርስላውተርንን በመሳሰሉት ከተሞች የሚገኙት ፋብሪካዎች ሠራተኛው እንደገና በስጋት ተወጥሯል። በጣሙን አሳዛኝ ሂደት ነው።

MM/DW

ነጋሽ መሐመድ