ጀርመን፣ የውጭ ንግዷና ጎረቤቶቿ | ኤኮኖሚ | DW | 15.02.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ጀርመን፣ የውጭ ንግዷና ጎረቤቶቿ

የጀርመን ኤኮኖሚ እጅጉን በውጭ ንግዷ ላይ ጥገኛ ነው። ስለዚህም ማደጉ ወይም ማቆልቆሉ በአገሪቱ ዕርምጃ ላይ በጣሙን ወሣንነት አለው። ለነገሩ የአገሪቱ የውጭ ንግድ ባለፉት ዓመታት ያለማቋረጥ እያደገና እየሰፋ ነው የመጣው።

ጀርመን የውጭ ንግድ የዓለም ሻምፒዮን ስትባል መኖሯም እንግዲህ ያለ ምክንያት አይደለም። የአገሪቱ ኤኮኖሚ ዋነኛ መንኮራኩር የሆነው የውጭ ንግድ በቅርቡ በተገባደደው በጎርጎሮሳውያኑ 2011 ዓመት-ምሕረት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ኤውሮ በላይ መዝለቁን ሰሞኑን የቀረበ ያፋ መረጃ አመልክቷል።

እርግጥ አገሪቱ የምታስገባው ምርትም በመጨመር አዲስ ወሰን ላይ መድረሱ ነው ተያይዞ የተነገረው። አውሮፓ በስፊው በበጀት ቀውስና በኤኮኖሚ ችግር በተወጠረበት በአሁኑ ወቅት ታዲያ የጀርመን ጥንካሬ በጎረቤቶቿ ዘንድ አድናቆትን ብቻ ሣይሆን እንበል ቅናትን ወይም በኛ ትከሻ የሚል ስሜትን ማጠንከሩም አልቀረም። የጀርመን ኢንዱስሪዎች ከዓለምአቀፉ የፊናንስና ኤኮኖሚ ቀውስ በፍጥነት ሲያገግሙ ፌደራላዊው የሰንጠረዥ ቢሮ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ከቪስባደን ቢሮው እንዳስታወቀው ባለፈው ዓመት በውጭ ንግድ ያገኙት ገቢ 1060 ሚሊያርድ ኤውሮ ተጠግቷል።

ይህም ቀደም ካለው ዓመት የ 902 ሚሊያርድ ኤውሮ ገቢ ሲነጻጸር እጅግ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። የውጭ ንግዱ መዳበር ጀርመን ከሌሎቹ የአውሮፓ ሃገራት የተሻል የኤኮኖሚ ዕድገት እንድታደርግም አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ የተሰወረ ነገር አይደለም። ይሁንና በሌላ በኩል የጀርመኑ የሄሰን-ቱሪንገን ክፍለ-ሐገራዊ ባንክ የፊናንስ ባለሙያ ሽቴፋን ሙትሰ እንደሚሉት በተከታዩ ጊዜ ከባድ አይሁን እንጂ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የኤኮኖሚ ዕድገት ግምት ማቆልቆል ሊታይ የማይችልበት ምክንያት የለም።

«በዓመቱ አራተኛ ሩብ ውስጥ ፌደራላዊው የሰንጠረዥ ቢሮ ያቀረበው የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ጽናት የሚኖረው አይመስለኝም። 0,2 ከመቶ እንደሚሆን ነበር ቀደም ብሎ የተገመተው። በቅርብ መረጃዎች መሠረት ምናልባት ይሄው አሃዝ እንዲያውም 0,3 ወይም 0,4 በመቶ ያነሰ ሣይሆን አይቀርም»

ለማንኛውም የጀርመን የውጭ ንግድ በዚህ በያዝነው ዓመት በ 2012-ም ምንም እንኳ የኤኮኖሚ ማቆልቆል ፍርሃቻ ባይጠፋም ምናልባት አይጋነን እንጂ ወደ አዲስ ክብረ-ወሰን መዝለቁ እንደማይቀር ነው የፌደራሉ የንግድና አገልግሎት ሰጭ ዘርፍ ማሕበር ፕሬዚደንት አንቶን በርነር በበኩላቸው የሚናገሩት። ወደ አገር ከሚገባው ጋር ተደምሮ የውጩ ንግድ በጠቅላላው ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለት ቢሊዮን ኤውሮ መስመርን ሊያልፍ እንደሚችል ተንብየዋል።

የዓለም ኤኮኖሚ ከሚገኝበት ከባድ ሁኔታ አንጻር እርግጥ የአገሪቱን ወቅታዊ ጥንካሬ ጠብቆ ማራመዱ ቀላል ነገር አይሆንም። ነገር ግን የጀርመን ኤኮኖሚ የፉክክር ብቃቱን ጠብቆ መቀጠል መቻሉን የሚጠራጠር ብዙ የለም። የፊናንሱ ባለሙያ ሽቴፋን ሙትሰም ቢሆን ችግር ይኑር እንጂ ሁኔታው በተጋነነ መልክ የባሰ ይሆናል የሚል ዕምነት የላቸውም።

«ከሶሥት ወራት በኋላ ሁኔታው ብዙም የከፋ እንደማይሆን አስተማማኝነት ያለው በጀርመን የምጣኔ-ሃብት ምርምር ተቋም ኢፎ ኢንስቲቲዩት የቀረበ መረጃ ያመለክታል። ሌሎች መረጃዎችም በተለይም ከአሜሪካ በቅርብ የሚመጡት ጠበብት ከጠበቋቸው የተሻሉ ናቸው። እጅግ ጠቃሚ ገበያ በሆነችው በቻያናም የኤኮኖሚው ድክመት በጣም ለዘብ ያለ ነው»

በጀርመኑ የውጭ ንግድ ላይ እናተኩርና ይሄው ባለፈው 2011 ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር በ 11,4 ከመቶ ነው ያደገው። በዚሁ ጊዜ ወደ አገር የሚገባው ምርት ድግሞ እንዲያውም በተፋጠነ ሁኔታ በ 13,2 ከመቶ ጨምሯል። በቪስባደን የሰንጠረዥ ቢሮ ጊዜያዊ መረጃ መሠረት ጀርመን ባለፈው 2011 በውጭ ንግዷ 158 ሚሊያርድ ኤውሮ ትርፍ አግኝታለች። አንድ ዓመት ቀደም ሲል በ 2010 ትርፉ 155 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋ ነበር።

ነገር ግን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የጀርመን ኢንዱስትሪዎች በዓመቱ መጨረሻ ላይ እስትንፋስ ማጣታቸው አልቀረም። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በታሕሣስ ከበፊቱ ሕዳር ወር ሲነጻጸር የውጭ ንግዱ ድርሻ በጣም ነበር ያቆለቆለው። ይህም በሁለቱ ወራት ንጽጽር የ 4,3 ከመቶ ማቆልቆል ሲሆን ከጥር 2009 ወዲህ ጠንካራው መሆኑ ነበር። በጊዜው በሌህማን ብራዘርስ ባንክ ክስረትና በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ የጀርመን የውጭ ንግድ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት በ 6,7 በመቶ መውደቁ ይታወሣል። ጠበብት በታሕሣስ የተነበዩት የአንድ ከመቶ ማቆልቆል ነበር። ጀርመን ከሞላ ጎደል ከባዱን ችግር ስትወጣ ከወቅቱ የአውሮፓ የበጀት ቀውስ አንጻርም መሰናክሉን ማለፉ እንደማይከብዳት ነው የሚታመነው።

«አጠቃላዩን ሁኔታ ግምት ውስጥ በመክተት በበኩላችን የምንጠብቀው የዕዳው ቀውስ በፖለቲካ ዕርምጃዎች በቁጥጥር ስር ሊውል እንደሚችልና በ 2008 እንዳየነው የመዋዕለ-ነዋይን ፍሰት ወደሚገታ አስቸጋሪ ደረጃ እንደማይሸጋገር ነው። ግን ይህን መሰሉ አደጋ ጨርሶ አይከሰትም ለማለት አይቻልም»

ጀርመን በዓለምአቀፍ ደረጃ በስፊው ብትነግድም ዋነኞቹና የአብዛኛው ምርቶቿ ተቀባዮች አሁንም መሰል የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት ናቸው። እነዚሁ ሃገራት ባለፈው 2011 627 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያወጣ ምርት ከጀርመን ገዝተዋል። በአንጻሩ ከሕብረቱ ሃገራት ለጀርመን የተሸጠው 573 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚጠጋ ነው። ጀርመን ወደ ሕብረቱ ሃገራት የምታስገባው ምርት በዚሁ አሥር በመቶ ሲጨምር እርግጥ አገር የገባውም 14 በመቶ ከፍ ብሏል። ሆኖም ሚዛኑ ወደርሷ ያጋደለ ነው።

በውጭ ንግዱ ጊዜያዊ የሰንጠረዥ መረጃ አማካይነት ጀርመን ክውጭው ዓለም ጋር ያላትን የንግድ ሚዛን ሰፋ ባለ መልክ ለማስላትም ያቻላል። ለምሳሌ የጀርመን አገር ጎብኚዎች ወይም ቱሪስቶች በዘልማድ አገራቸው ከምታስገባው የበለጠ ገንዘብ በውጭ እንደሚያወጡ ያታወቃል። እናም በአገልግሎቱ ዘርፍ የገቢ-ውጪ ሚዛን ባለፈው ዓመት 7,8 ሚሊያርድ ኤውሮ ወደታች ያጋደለ ነበር። በዚህ በጀርመን የሚኖሩ የውጭ ሠራተኞችም በ 2011 ወደየትውልድ ሃገራቸው የላኩት ገንዘብ 35,6 ሚሊያርድ ኤውሮ ይጠጋል።

በአንጻሩ ጀርመናውያን በንግድና በሃብታቸው በውጭ ሃገራት የሚያካብቱት ገቢ በ 40,9 ሚሊያርድ ኤውሮ ነው የጨመረው። በአጠቃላይ የጀርመን የገቢ-ወጪ ሚዛን በአገሪቱ ፌደራል ባንክ ጊዜያዊ ስሌት መሠረት ባለፈው ዓመት የ 136 ሚሊያርድ ኤውሮ ትርፍ ታይቶበታል። አንድ ዓመት ቀደም ሲል ይሄው አሃዝ 141 ሚሊያርድ ይጠጋ ነበር።

የጀርመን ኩባንያዎች ከአውሮፓ ባሻግር በእሢያና በላቲን አሜሪካም በስፊው የሚነግዱ ሲሆን ከነዚሁ ሲሶው በውጭ የራሳቸው ውክልና ወይም ቅርንጫፍ ድርጅት አላቸው። የአገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት ባልደረባ ኢልያ ኖትናግል የሚናገሩት ይሄውም ባለበት እንደሚቀጥል ነው።

«ይሄ ጀርመንን የሚጎዳ አይደለም። ይልቁንም የጀርመን ኩባንያዎች በዚህ በአገርም ንግዳቸውን እንዲያስፋፉና ብዙ ሠራተኞችን እንዲቀጥሩ ያደርጋል። ትርጉሙ የሚናቅ አይደለም። እና ስለዚህም የዓለምአቀፋዊነቱ ጉዞ ያቀጥላል ማለት ነው»

የጀርመን ኩባንያዎች በውጭ በመስፋፋቱ ረገድ በተለይም የሚያተኩሩት በኤኮኖሚ እመርታ ላይ በምትገኘው በእሢያ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በቻያና ላይ ነው። አካባቢው ከአውሮፓ ቀጥሎ ሁለተኛው የምርት ማራገፊያቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

«እርግጥ ነው አውሮፓ እንደ እናት ገበያ መቆሚያችን ናት። ሆኖም ግን ለዕድገት የሚበጀው አዲስ አቅጣጫ በወቅቱ የሚያመራው ወደ ምሥራት፤ ማለትም ወደ እሢያ ነው። በዚያ ከቻይና ጎን አስተማማኝ ዕድገት የሚታይባቸውና ለንግድ የሚመቹ ሌሎች ገበዮችም አሉ። የጀርመን ኩባንያዎች እንግዲህ በአካባቢው ስር እንዲሰዱ አመቺው ሁኔታ አለ»

የደቡብ ምሥራቅ እሢያው አካባቢ ለጀርመን ኩባንያዎች ይበልጥ ማራኪ መሆኑን አሁንም ቀጥሏል። በያዝነው ዓመት ምንም እንኳ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ዝግ እንደሚል ቢጠበቅም በአንጻሩ ኢንዶኔዚያ፣ ማሌዚያ፣ ፊሊፒን፣ ታይላንድ፣ ሲንጋፑር ወይም ቪየትናም በተፋጠነ ዕርምጃቸው እንደሚቀጥሉ ነው የሚጠበቀው። እና የጀርመን ኢንዱስትሪ ምርቶችም ይበልጥ ተፈላጊ ይሆናሉ።

በወቅቱ ከአካባቢው ሃገራት ጋር የነጻ ንግድ ውል ለማስፈን የሚካሄደው ንግግር ማሰሪያ እንዳገኘም ቀረጥን ለመቀነስና ተጨማሪ መዋዕለ-ነዋይ ለማድረግ እንደሚጠቅም አንድና ሁለት የለውም። በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት የነዚህ ሃገራት ኤኮኖሚ በተለይም ዘመናዊ ተሃድሶን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ከጀርመንም ጭምር የኢንዱስትሪ መኪናዎችንና ሌሎች ምርቶችን ይፈልጋሉ። ከዚህ አንጻር የጀርመን ኢንዱስትሪዎች የወደፊት ተሥፋ ብሩህ የሚሆን ነው የሚመስለው።

በሌላ በኩል ጀርመን ዓለምአቀፉን የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ከተቀሩት የአውሮፓ ሕብረት ሃገራት ቀድማ በተሻል ሁኔታ መቋቋሟና የውጭ ንግዷም እያበበ መቀጠሉ በጎረቤቶቿ ዘንድ በክፉም ይሁን በደግ አስቀኚ ሳያደርጋት አልቀረም። ዛሬ ግማሽ አውሮፓ በበጀት ቀውስ ተወጥሮ ባለበት ሰዓት ግሪክን መሰል መንግሥታትን ከክስረት ለማዳን በተያዘው ጥረት በተለይ ጀርመን ሰፊውን የገንዘብ ድርሽ እንድትሸከም በመጠየቅ ላይ ነው። ለዚህም ብዙዎቹ የሕብረቱ ሃገራት እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት ጀርመን በገበያቸው መካበቷን ነው።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 15.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/143GG
 • ቀን 15.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/143GG