ጀርመን፤ የኤኮኖሚ ለውጥና ማሕበራዊ ፍትህ 2 | ኤኮኖሚ | DW | 10.11.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ጀርመን፤ የኤኮኖሚ ለውጥና ማሕበራዊ ፍትህ 2

ምዕራባዊቱ የጀርመን ፌደራል ሬፑብሊክ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውድቀት በኋላ ሁለት አሠርተ-ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያሳየችው የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ቀደምት ከሚባሉት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት መካከል አንዷ እንድትሆን አብቅቷታል። የኤኮኖሚ ዕድገት “ተዓምር” የተሰኘው አስደናቂ የምጣኔ-ሐብት ምጥቀት ዕርምጃዋ ምናልባት ከጃፓን ባሻገር በሌላ ቦታ ተመሳሳይ ተፈልጎ የማይገኝለት ነው። በዚህ ጉዳይ በመጀመሪያው ክፍል ዝግጅታችን በሰፊው በማተኮራችን አሁን እንደገና በጥልቀት አንመለከተውም።

የተዋሃደች ጀርመን በወቅቱ ከሰባኛዎቹ ዓመታት መጨረሻ ገደማ ወዲህ ሥር-እየሰደደ በመጣ የኤኮኖሚ ዕድገት ቀስ በቀስ መመንመን ሂደትና ይሄው ባስከተለው የሕብረተሰብ ማሕበራዊ ዋስትና ሥርዓት ዝቤት ፈታኝ ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው። ምንም እንኳ የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ሁኔታ ተጽዕኖ በአገሪቱ የምጣኔ-ሐብት ይዞታ ላይ የራሱ ድርሻ እንዳለው ባይታበልም በብሄራዊ ደረጃ አስፈላጊው ለውጥ በጊዜው አለመደረጉ በአመዛኙ ለችግሩ ምክንያት ነው።

በሁለቱ ጀርመን ግዛቶች መልሶ መዋሃድ በምሥራቁ ወገን ከሞላ-ጎደል የአዲስ ጅማሮን ያህል ሆኖ የተገኘው የተሃድሶ ግንቢያ ብዙ ሚሊያርድ ገንዘብ ነው የጨረሰው፤ እየጨረሰም ነው ያለው። ውሕደቱ አጠያያቂ ሊሆን የማይገባው ተገቢና ታሪካዊ ዕድል ቢሆንም በአጠቃላይ ሂደቱ ለዛሬው የኤኮኖሚ ችግር ሊዘረዘሩ ከሚችሉት ምክንያቶች አንዱ ለመሆኑ ብዙም አያጠራጥርም።

በዘመነ-ሶቪየት ፍጻሜ ዋዜማ ተንኮታኩቶ የወደቀውን የጊዜይቱን ምሥራቅ ጀርመን ኤኮኖሚ መልሶ ለማቅናትና የሕዝቡም የኑሮ ሁኔታ ቀስ በቀስ ከምዕራቡ ደረጃ ለማጣጣም አስፈላጊውን ጥርጊያ ለማመቻቸት ብዙ ጥረት ነው የተደረገው። በዚህም ብዙ ዕርምጃ መደረጉ የተሰወረ አይደለም። የባቡር ሃዲዶችና ፈጣን አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ የመገናኛውን መዋቅር በምዕራቡ ደረጃ በማነጽ፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪና ንግድን ዘመናዊ በማድረግ የተካሄደው የተሃድሶ ተግባር አርኪ ውጤቶችን አስከትሏል። ዛሬ በርሊንን፣ ላይፕትሢግንና ድሬስደንን የመሳሰሉት የምሥራቁ ከተሞች ገጽታ ከምዕራቡ መዲናዎች አንድ ለመሆን የበቃ ነው።

ይሁንና ውሕደቱ በማዕከላዊ የኤኮኖሚ ዕቅድ ሥር በቆየው በምሥራቁ ክፍል ያስከተለው ሥር-ነቀል ተሃድሶ ብዙ ማሕበራዊ ችግሮችን ማስከተሉም አልቀረም። ዛሬ በአማካይ መጠን ሲታይ ጀርመንን ክፉኛ የተጠናወተው ሥራ-አጥነት ጠንክሮ የሚታየው በዚያው በምሥራቁ ክፍል ነው። ይህ ደግሞ በአጠቃላይ በጀርመን ተጎታች ከሆነው ካለፉት ዓመታት የኤኮኖሚ ዕድገት መጠንና የማሕበራዊ ሥርዓት ዝቤት ተጣምሮ ለወቅቱ ችግር ሰፊ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ጀርመን ዛሬ ለምትገኝበት የኤኮኖሚ ዕድገት የማቆልቆል ሁኔታ የሕብረተሰቡ ሰፊ ክፍል ማርጀትም አጣዳፊ ምላሽን የሚጠይቅ አሳሳቢ ምክንያት እየሆነ ነው። 82ሚሊዮን ገደማ ከሚጠጋው የአገሪቱ ሕዝብ መካከል በመጦር ላይ የሚገኘውና ለጡረታ የተቃረበው ነዋሪ ብዛት ከሰባ በመቶ በልጧል። ሥራ-አጡና ማሕበራዊ ድጎማ እየተሰጠው የሚተዳደረው ወገንም ተጣምሮ በሥምንት ሚሊዮን ይገመታል። እንግዲህ በትውልዶች መደጋገፍ ውል ላይ ለቆመውና ለአያሌ ዓመታት ፍቱን ሆኖ ለኖረው የማሕበራዊ ዋስትና ሥርዓት ሕልውና ዛሬ መሠረት ሆኖ የሚገኘው ሰርቶ-አደርና ግብር ከፋይ ወጣት-ጎልማሣ የሕብረተሰብ ክፍል ሃያ በመቶ ቢሆን ነው።

ችግሩ በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም። በዚህ በጀርመን በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ጭምር እንደሚታየው ሁሉ ብዙዎች ዜጎች በኤኮኖሚ ይዞታና ሌሎች ምክንያቶች የተነሣ ልጅ መውለድ ስለማይፈልጉ ሠርቶ የማሕበራዊውን ሥርዓት ሕልውና የሚያረጋግጥ ተተኪ ትውልድ እጦት እየጨመረ ሲሄድ ነው የሚታየው። ጠበብት ከዛሬው እንደሚያስጠነቅቁት የጀርመን ሕዝብ ቁጥር ሁኔታው ካልተለወጠ በሚቀጥሉት ሃያና ሰላሣ ዓመታት ዛሬ ከሚገኝበት 82 ወደ 60 ሚሊዮን ገደማ ማቆልቆሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ በአማካይና በረጅም ጊዜ ለኤኮኖሚው ዕድገት ጠንቅ እንደሚሆን ጨርሶ አያጠያይቅም።

ይህን ማሕበራዊ ችግርም ሆነ አጠቃላዩን የኤኮኖሚ ድቀት ሂደት ለመግታት በመሠረቱ ሃብቱ ጠፍቶ አይደለም። የሕብረተሰቡን ጥቅምም ሆነ አስፈላጊው ለውጥ የሚጠይቀውን ሸክም በማከፋፈሉ በኩል ፍትሃዊ ተሃድሶ ማድረግ አለመቻሉ ነው። የአገሪቱን የግብር ሥርዓት በመጠገን የመንግሥቱን የበጀት ኪሣራ ለማለዘብ እስካሁን በቀድሞው የቻንስለር ኮል ወግ አጥባቂ አስተዳደር ዘመንም ሆነ አሁን በመሰናበት ላይ በሚገኘው የሶሻል ዴሞክራቶችና የአረንጓዴዎች ጥምር መንግሥት የተደረጉት የለውጥ ሙከራዎች በገፍ ትርፍ ከሚያጋብሰው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ይልቅ ሰርቶ-አደሩን ይበልጥ የሚጫኑ ሆነው ነው የታዩት።

የጀርመን የውጭ ንግድ ገቢ በተከታታይ ለሶሥተኛ ዓመት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ክብረ-ወሰን ማስመዝገብ በያዘበት በዛሬው ጊዜ የአገሪቱ ታላላቅ ኩባንያዎች ተቋሞቻቸውን በከፊል ወይም በሙሉ እየዘጉ ርካሽ ጉልበት ወደሚገኝባቸው አገሮች ጨርሰው እንዳይኮበልሉ እሹሩሩ የሚባሉ ሆነዋል። እርግጥ በጀርመን የዳበረ ከሆነው የኑሮ ደረጃ አንጻር የሠራተኛው ደሞዝና የአመራረቱ ዋጋ ከሌሎች አገሮች ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑ ባይታበልም ትርፍ ብቻ የሽሽት ምክንያትም ሆነ የለውጥ ሸክም በአንድ ወገን ላይ እንዲጫን መገፋፊያ የተጽዕኖ መሣሪያ ሊሆን ባልተገባው ነበር።

በነገራችን ላይ ለጀርመን ብሄራዊ ኤኮኖሚ ዕድገት መጓተት ምናልባትም ዓቢይ ምክንያት የሆነው በማሕራዊው ሥርዓትና በሥራ ገበያው ላይ የተያዘው ለውጥ ሸክም ይበልጥ በሕዝብ ላይ ማጋደሉ የዜጎች የመገብየት የገንዘብ አቅም እንዲዳከም ወይም ከስጋት የተነሣ ቆጣቢነት እንዲጠነክር ማድረጉ ነው።

የወቅቱ የረባ የኤኮኖሚ ዕድገት እጦት፣ የሥራ-አጡ ቁጥር መናርና የወጣቱ ትውልድ የወደፊት ተሥፋ መደብዘዝ ሰሞኑን ፈረንሣይ ውስጥ እንደሚታየው ለማሕበራዊ ዓመጽ መቀጣጠል መንስዔ እንዳይሆን በጣሙን ያሰጋል። ፈረንሣይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ደምብ ለማወጅ መገደዷ ማሕበራዊና ፖለቲካዊው ሥርዓት ለረጅም ጊዜ ችላ ብሏቸው የኖሩት መጤዎች ልጆች ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሆኖ መታየቱ ስለበቃቸው ነው።

ይህን መሰሉ የሕብረተሰብ ክፍል ደግሞ በአውሮፓ ከብሪታኒያ እስከ ኔዘርላንድና እስከዚህ እስከ ጀርመንም ያለና ቁጣው ውስጥ ውስጡን የሚጋይ፤ የሥራ-አጡ ቁጥር እየጨመረና ማሕበራዊው ፍትህ እየተጓደለ በቀጠለ ቁጥር ድንገት ሊፈነዳ የሚችል በስውር እየተቀጣጠለ ያለ ነገር ነው። እርግጥ ድህነቱ አንጻራዊ ነው። ከታዳጊው ዓለም ሁኔታ የሚነጻጸር አይደለም። ሆኖም በሃብታሙና በውሱኑ የሕብረተሰብ ክፍል መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ለሕብረተሰብ ሰላም አደገኛ እየሆነ መሄድ መቻሉ ከሰሞኑ የፈረንሣይ ሃቅ ወዲህ የማይጠበቅ ነገር ሊሆን አይችልም።

ሥራ-አጥነትን በማለዘቡ በኩል መላው ሕብረተሰብ እንደያቅሙና እንደሁኔታው ድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል። ጊዜው የግሎባላይዜሺን፤ የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ትስስር ዘመን ነው በሚል አስባብ መሸሽ የሚቃጣው የኢንዱስትሪ ዘርፍም እዚህ ለዓመታት ላተረፈበትና ለካበተበት ሕብረተሰብ ዋጋ መላሽ መሆኑ ተገቢ ነው። ነጻ የኤኮኖሚ ሥርዓት በሰፈነበት አገር እርግጥ መንግሥት ተገቢውን ግብር ከመጠየቅ አልፎ ይህን አምራች ወገን የማስገደድ ሥልጣን የለውም። ቢሆንም የሞራል ግዴታ፤ የአገር ሃላፊነት ድርሻ የሠርቶ-አደር የዜጎች ብቻ አለመሆኑን ማስረገጡ ግድ ነው።

በጀርመን በተለይም የሥራ-አጡ ብዛት አለመቀነስ ባስከተለው ችግር የተነሣ ከመደበኛ ጊዜው የቀደመ ምርጫ ግድ ሆኖ ባለፈው መስከረም ወር መካሄዱ አይዘነጋም። ሕዝብ በድምጹ የለየለት አቅጣጫ ጠቋሚ ውሣኔ ባለማድረጉም የቀረው ምርጫ በሁለቱ የአገሪቱ ታላላቅ ፓርቲዎች በክርስቲያኑ ሕብረትና በሶሻል ዴሞክራቶች መካከል ጥምረትን ማስፈኑ ነው። ሁለቱ ወገኖች ከረጅም ውጣ-ውረድ በኋላ በፊታችን ቅዳሜ ድርድራቸውን አጠናቀው መንግሥት ለማቆም እንደሚበቁ ዕምነት አለ።

ጥያቄው እስካሁን በተካሄደው ድርድር የመንግሥቱን ዕዳ በከፊል ለማጣጣትና ኪሣራውን ለማለዘብ ማሕበራዊ ወጪን በሚቀንሱ አጠቃላይ የቁጠባ ዕርምጃዎች ከአንድነት ከመደረሱ ባሻገር የረጅም ጊዜ ራዕይ የጎላበት የተሃድሶ ዕቅድ ሲፈልቅ አለመታየቱ ላይ ነው። ያለፉት ዓመታት ችግርም ይህ እንጂ ሌላ አልነበረም። መጪው መንግሥት በሚከተለው የቁጠባ ፖሊሲ ምናልባትም የወደፊት ጡረታውን በተጨማሪ የግል ዋስትና ውል ማሟላት፤ ለጤና አገልግሎት ተጨማሪ ድርሻ መክፈልና ሌላም የሚኖርበት ሕዝብ የመገብየት አቅም ይባስ እንዳይዳከም አዝማሚያው ቢቀር ለስጋት መንስዔ የሚሆን ነው።
ጀርመን ዛሬ የአውሮፓ ሕብረት በማስትሪሽት ውሉ የደነገገውን ከየብሄራዊው ምርት ከሶሥት በመቶ መብለጥ የሌለበትን የበጀት ኪሣራ እንኳ ዘንድሮም ለተከታታይ ሶሥተኛ ጊዜ እንደማታሟላ ነው የሚጠበቀው። ራሷ ያንቀሳቀሰችው የመቀጮ ደምብ በራሷ ላይ እስከማንዣበብ መድረሱ ያስገርማል። የአገሪቱ ኤኮኖሚ ዕድገት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በመጪው ዓመትም ከአንድ በመቶ ያለፈ እንደማይሆን የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ሰሞኑን የተነበዩት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ከዓለምአቀፉ አማካይ የዕድገት መጠን ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ ሌላ ሥራ-አጥነትን በማለዘቡ በኩል የተሻለ ሁኔታን አይፈጥርም።

ችግሩ ቀጣይነት የሚኖረው፤ በቀላሉ የማይበገር ነው የሚመስለው። “ጀርመን ከተዓምራዊ የኤኮኖሚ ዕድገት ወደ ማሕበራዊ ድቀት? የአገሪቱ የምጣኔ-ሐብት ዕርምጃ መንታ መንገድ ላይ ነው የሚገኘው። መሥፍን መኮንን ነኝ፤ በሌላ ርዕስ ቸር ይግጠመን!