ጀርመን የኢራቅ ኩርዶችን ለማስታጠቅ መወሰኗ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመን የኢራቅ ኩርዶችን ለማስታጠቅ መወሰኗ

የጀርመን መንግሥት የኢራቅ ኩርዶችን ለማስታጠቅ መወሰኑ የሰሞኑ የጀርመናውያን አብይ የመነጋገሪያ ርዕስ ነው ። የጀርመን መንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ዛሬ ሳምንት ሐሙስ ድረስ የሚሰጧቸው መግለጫዎች ጀርመን ጦርነት ወደ ተባባሰባት ኢራቅ የጦር መሣሪያዎችን አትልክም የሚል ነበር ።

ፈረንሳይን የመሳሰሉ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በምህፃሩ IS በመባል የሚጠሩትን አክራሪ ሙስሊም ተዋጊዎችን ለሚፋለሙት የኩርድ ኃይሎች የጦር መሣሪያ እንሰጣለን ሲሉ ጀርመን ይህን መሰሉን ድጋፍ እንደማትሰጥ ነበር በተደጋጋሚ ስታሳውቅ የቆየችው ። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርም ሆኑ መከላከያ ሚኒስትሯ ኡርዙላ ፎን ዴር ላይን ጀርመን የጦርመሣሪያ ከመስጠት ይልቅ ትክረቷ ወታደራዊ ቁሳቁሶችንና ሰብዓዊ እርዳታዎችን መስጠት ላይ ብቻ እንደሚሆን ነበር የተናገሩት ። በወቅቱ መከላከያ ሚኒስትር ፎን ዴር ላየን መንግሥታቸው አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ያቀርባል ነበር ያሉት ።

«በአሁኑ ጊዜ በአሁኑ ቅፅበት ማድረግ የሚቻለንን ለማከናወን በጥድፊያ ላይ ነን ። ብርድ ልብስ ድንኳኖች የጥይት መከላከያ ሰደርያ የብረት ቆብ የመሳሰሉትን ማቅረብ ይቻላል ። ሁለተኛ እንዴት አድርገን ይህን እርዳታ እንደርሳለን የሚለው ጥያቄ ነው ። ይህ ሁሉ በአጣዳፊ እየተመከረበትና መላ እንዲገኝለትም ጥረት እየተደረገ ነው ። እርዳታውን በፍጥነት ለማድረስ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ።»

«ምንም እንኳን የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህን አቋማቸውን ሲያንፀባርቁ ቢቆዩም ባለፈው ሳምንት ግን ራሳቸውን ISIL ብለው የሚጠሩትን አክራሪ ሙስሊም ኃይሎችን የሚወጉትን የኢራቅ ኩርድ ፔሽሜርጋ ተዋጊዎችን ጀርመን በልዩ አስተያየት ለማስታጠቅ መወሰኗን አስታውቃለች ። የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ARD ከተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ መንግሥታቸው የቀደመውን አቋሙን ለመቀየር ያበቃውን ምክንያት ተናግረዋል።

«የጦር መሣሪያ እርዳታን በተመለከተ አሁን ከዚህ ቀደም አጋጥሞን ከሚያውቅ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ቀርቧል ። የእስላማዊ መንግስት ሚሊሽያ ጦር በተሰኙ ታጣቂዎች ዓለም በመላ እየተመለከተ የሽብር ተግባር በመፈፀም ላይ ነው ። ይህን የሽብርና ጥካኔ ተግባር የሚፈፅሙትም የራሳቸውን ሥልታዊ አቋም ይዘው በማንኛውም የተለዬ አመለካከትና ባለው ሙስሊም ሆነ ክርስቲያን ወይም ሌላ እምነት ተከታይ በሆነ ላይ ነው ። ስለዚህም እኛ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተስማምተን ርዳታው በመንገድ ላይ ነው ። የትጥቅ ርዳታ ያስፈልጋል። እናም ይህ ተማፅኖ ሲቀርብልን በተወሰነ ደረጃ የጦር መሣሪያ ጥይት በፍፁም ከኛ አታገኙም ማለት አይቻለንም ። የኩርድ አካባቢያዊ መስተዳድር ከአሜሪካውያንና ከሌሎች ጋር ሆነው ነው ጥቃቱን የመከቱት ። እኛም ድርሻችንን ከመወጣት የምናፈገፍግበት ሁኔታ የለም »

የISIL ደፈጣ ተዋጊዎች አሁን የኢራቅን መንግስት ኃይሎች የሚወጉት በአሜሪካን የጦር መሣሪያዎች መሆኑ ነው የሚነገረው ። ከዚህ ቀደም በነበሩት ተደጋጋሚ ልምዶች በተለያዩ ምክንያቶች ከምዕራባውያን የሚለገሱ የጦር መሣሪያዎች በአማጽያን እጅ ይገባሉ ። በበቦን ዩኒቨርስቲ የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ቶማስ ሽፔክማን ይህ ችግር በአንዳንድ ሃገራት መከሰቱን ያስታውሳሉ ። በተለይ ተደጋግሞ የሚወሳውን በአፍጋኒስታን ያጋጠመውን ሁኔታ ሽፔክማን በአብነት ያቀርባሉ ።

«የጦር መሣሪያ መሰጠትን የሚቃወሙ ወገኖች ምሳሌ አድርገው የሚያነሱት አፍጋኒስታንን ነው ። የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አፍጋኒስታንን እጎአ በ1979 ከወረረች በኋላ አንዳንድ ምዕራባውያን ሃገራት የሶቭየትን ኃይሎች ለሚወጉት ለሙጅሃዲኖች የጦር መሳሪያ ለማቅረብ ወሰኑ ። እነዚህ የጦር መሣሪያዎችም ታሊባኖች እጅ ገብተው በኋላም ምዕራባውያንን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ዋሉ ። እኔ ግን በተለየ መንገድ ነው የምመለከተው ። ታሊባኖችና አልቃይዳ የምዕራባውያኑ ጠላት በሆኑበት ወቅት በትከሻ የሚነገቱት ፀረ አውሮፕላን ሮኬቶችን የመሳሰሉት የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎች ከስራ ውጭ ነበሩ ። በአካባቢውም ስለ እነዚህ የተወሳሰቡ የጦር መሣሪያዎች የሚያውቅ ባለሞያ መኖሩ ያጠራጥራል ። ሆኖም ረዥም እድሜ ያላቸው ጠመንጃዎችና አቶማቲክ ጠመንጃዎችን የመሳሰሉ መሳሪያዎችም አሉ ። »

እናም ይህን ከመሳሰለው ልምድ በመነሳት ጀርመን ለኩርዶች የምትሰጠው የጦር መሳሪያ በአማጽያን እጅ ላለመግባቱ ምን ዋስትና አለ ተብለው መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ተጠይቀው ነበር ። ሜርክል ለዚህ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ተናግረው ሆኖም ይህን ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ነበር ያስረዱት ።

« በጉዳዩ ላይ በሰፊው መክረናል መቶ በመቶ አስተማማኝ ሁኔታ የለም ግን ሁለት አማራጮች አሉን ። የሆነ ነገር ለማቅረብ የዚህ አሸባሪ ቡድን ዘመቻ ከነአካቴው እንዲቆም ማድረግና የህዝብ ጭፍጨፋን ና ተከታታይ ጭፍጨፋዎችን ማስቆም ፤ አለበለዚያም የሚገጥመው ፈተና እጅግ ከባድ ነው ብሎ ዝም ማለት ይሆናል ።ይሁን እንጂ በምክክራችን የሆነ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ነው የተገነዘብን »

በእርዳታ የሚሰጡ የጦር መሣሪያዎች ከታሰበላቸው ቦታና ዓላማ ውጭ መዋል አለመዋላቸው አስጊው ጉዳይ ነው ። ሽፔክማን እንደሚሉት በተወሰነ ደረጃ ይህን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ አለ ።

ይህ እንደ ጦር መሣሪያው ዓይነት ይለያያል ። ካላሽንኮቭን የመሣሠሉ ቀላል መሣሪያዎችን እንዲሁም የተወሳሰቡ አሰራር ያላቸውን የጦር መሣሪያዎችንም መቆጣጠሪያ መንገዶች አሉ ። ለነዚህ መሣሪያዎች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ለየት ያሉ ክፍሎች አሏቸው ።እነዚህን ክፍሎች ደግሞ ከዓለም ዓቀፍ ገበያ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም ። እናም አነዚህን አስፈላጊ የሆኑ የጦር መሣሪያውን ክፍሎች በቀላላሉ እንዳይገኙ በመከላከል በጦር መሣሪያዎቹ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይቻላል ። በተራቀቁና በተወሳሰቡ መሣሪያዎች ውስጥም የሚገጠሙ ከሌላ ቦታ ሆኖ የጦር መሣሪያውን መቆጣጠር የሚያስችሉ ስልቶች አሉ ።ይህ መሣሪያው ላይ የተገጠመ የደህንነት መቆጣጠሪያ መሆኑ ነው ።»

ምዕራባውያን ውጊያ በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች የሚያቀርቡት የጦር መሣሪያ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አለማምጣታቸው ሁሌም የሚያነጋግር ጉዳይ ነው ። ሽፔክማን በዚህ ረገድ የተፈለገው ዓላማ የተሳካባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ የመኖራቸውን ያህል ችግሮች የተከሱቱባቸው ወቅቶች እንደነበሩም ያስታውሳሉ ።

በ1980 ዎቹ ፈረንሳይና ዩናይትድ ስቴትስ የሊቢያውን የሞአመር ጋዳፊን ጦር ቻድ ውስጥ ገጥመው ነበር ።ምዕራባውያኑ በጋዳፊ የሚደገፈውን የቻድ መንግሥት ጦር የሚወጉትን የቻድን አማፅያን በወታደራዊ አማካሪዎችና በጦር መሣሪያዎች ያግዙ ነበር ። አማፅያኑ ከፈረንሳይ የአየር ኃይል የጦር አውሮፕላኖችም ይታገዙ ነበር ። ግጭቱ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ የቻዱ ፕሬዝዳንት ከስልጣን ተወግደዋል ።ጋዳፊም በዚህ ግጭት ክፉና ተመተዋል ምክንያቱም ጀርመንና ፈረንሳይ ሰራሹ MILAN የሚባሉት ፀረ ታንክ ሚሳይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የሊቢያ ጦር ታንኮችን አውድመዋል ። እነዚህን መሰል ፀረ ታንክ ሚሳይሎች ኢራቅ ለሚገኑት ኩርዶች ሳይሰጥ አይቀርም ።

«ይህ የታሰበለትን ዓላማ አሳክቷል ከሚባል የጦር መሣሪያ ድጋፍ አንዱ መሆኑን የተናገሩት ሽፔክማን በአንፃሩ የምዕራባውያን ሃገራት የመሣሪያ አቅርቦት በተዘዋዋሪም መንገድ ቢሆን የራሳቸውን አጋር የጎዳበት አጋጣሚ እንደነበርም ያስታውሳሉ

«እዚህ ላይ ሌላ ችግር የተፈጠረበትን አሉታዊ ምሳሌ ማንሳት እፈልጋለሁ ። እጎአ በበ1982 የፎክላንድ ጦርነት የአርጀንቲና ወታደራዊ አገዛዝ ከዩናይትድ ስቴትስና ከፈረንሳይ አያሌ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቆ ነበር ። አርጀንቲና በነዚህ መሳሪያዎች ተጠቅማ በብሪታኒያ ጦር ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሳለች ። ዋሽንግተንና ፓሪስ ይህን አስቀድመው መገመት ቢችሉ ኖሮ ለአርጀንቲና ይህን መሰሉን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ባልፈቀዱ ነበር ።»

ሽፔክማን እንደሚሉት በመሠረቱ እነዚህ የጦር መሪያዎች ከተሰጡ በኋላ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም ።የጀርመን መንግስት ለኩርዶች የጦር መሳሪያ አቀርባለሁ ማለቱ የጀርመን ፖለቲከኞች እያከራከረ ነው ። ሃሳቡን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የለም በዚህ መሰሉ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት የለብንም የሚሉም አሉ ። በጉዳዩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመወሰን መብት ይሰጠው የሚሉም አሉ ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል መንግሥታቸው የኢራቅ ኩርዶችን ለማስታጠቅ ስለደረሰበት ውሳኔ በሚቀጥለው ሳምንት ለፓርላምው ማብራሪያ ይሰጣሉ ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic