ጀርመን ዋንጫዉን ወሰደች | ስፖርት | DW | 14.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ጀርመን ዋንጫዉን ወሰደች

20ኛዉ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ዉድድር በጀርመን ድል ትናንት ተጠናቀቀ። ጀርመን ከምድቧ ማለትም ከምድብ G በአንደኝነት ነበር ወደቀጣዮቹ የግጥሚያ ዉድድሮች የተሻገረችዉ።

በወጣቶች የተገነባዉ ቡድን አያያዝ ይበልጥ የእግር ኳስ አፍቃሪዉን ሕዝብ ይበልጥ በማነሳሳቱም ዘንድሮስ ዋንጫዉን ይዘዉልን ይመጣሉ የሚለዉ የብዙዎች ግምት ነበር። ግምት ብቻ ሆኖ አልቀረም አርጀንቲናን አንድ ለባዶ በ113ኛዉ ደቂቃ ወሳኝ በሆነችዉ ግብ እዉን ሆነ። ማርዮ ገትሰ ያስቆጠራት ግብ ቡድኑንም ሆነ ደጋፊዎቹን ከፍፁም ቅጣት ምት ልብ ሰቀላና ጭንቅ ገላግሎ የጀርመን የእግር ኳስ ቡድን ከወር በላይ ላቡን ያፈሰሰባትን ዋንጫ ለመሳም በቃ። ሀገሩንም ባለድል አደረገ።

በላቲን አሜሪካ የዓለም ዋንጫ ተዘጋጅቶ አዉሮጳዊ የኳስ ቡድን ድል ቀንቶት አያዉቅም ቢባልም የዘንድሮዉ የብራዚል የዓለም ዋንጫ ግን በጀርመን ድል ታሪክ አስቀይሯል። ጀርመን መጀመሪያ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1954፣ በድጋሚ በ1974፣ ለሶስተኛ ጊዜም በ1990 በዚሁ የዘመን ቀመር የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ዉድድር አሸናፊ ሆናለች። የዘንድሮዉ ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ። ለዋንጫ የቀረበችዉ ላቲን አሜሪካዊት ሀገር አርጀንቲና ለሶስተኛ ጊዜ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ሻምፒዮን የመሆን ተስፋዋ መደበኛዉ የጨዋታ ሰዓት አልቆ ከተራዘመ በኋላ ባለቀ ደቂቃ በተቆጠረችዉ ግብ በሰቀቀንና ሃዘን ተለዉጧል። በዘንድሮዉ የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ ከፍተኛ ሥራ ከበዛባቸዉና ቡድኖቻቸዉን የግብ ጎተራ ከማድረግ ካዳኑ መካከል የሜክሲኮዉ እና የጀርመን ቡድን ግብ ጠባቂዎች የበርካታ ተመልካቾችንና የእግር ኳስ ጨዋታ ተንታኞችን ትኩረት የሳቡ ነበሩ።

በፍፃሜዉ ዕለትም የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር የወርቅ የእጅ ጓንት ተሸልሞ የዘንድሮዉ ድንቅ በረኛ ተሰኝቷል። የአርጀንቲናዉ ኮከብ ተጫዋች ሌዮኔል ሜሲ ምንም እንኳን ዋንጫዋን ለመጨበጥ የሰነቀዉ ምኞት እዉን ሳይሆንለት ቢቀርም በኮከብ ተጫዋችነት የወርቅ ኳሱን ተሸልሟል።

በአራት አመት አንድ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ትናንት ምሽት ሲጠናቀቅ ፊፋ ከአሸናፊዋ ጀርመን በተጨማሪ ኮሎምቢያን የጸባይ ዋንጫ ሸልሟል። የፈረንሳዩ ፖል ፖግባ የውድድሩ ወጣት ተጫዋች ሆነው ተመርጠዋል። ትናንት የተጠናቀቀውን ውድድር አስመልክቶ ለአጭር ጊዜ በጆቼ ቬለ የአማርኛ ዝግጅት ክፍል በተባባሪ ዘጋቢነት የሚገኘዉ እሸቴ በቀለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪዎችን አነጋግሯል።

ዝርዝሩን ከድምፅ መረጃዉ ያድምጡ፤

ሃይማኖት ጥሩነህ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic