ጀርመን አፍሪቃዊትዋ የምዕተ ዓመቱ የታሪክ መስካሪ | ባህል | DW | 09.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ጀርመን አፍሪቃዊትዋ የምዕተ ዓመቱ የታሪክ መስካሪ

የ 90 ዓመትዋ ደራሲ ሩት ቫይስ እትብታቸዉ የተቀበረበት ሀገረ ጀርመንን የሚያዉቁት እጅግ በጥቂቱ ነዉ። በደቡብ አፍሪቃ ግን አዛዉንቷ በሥነ-ጽሑፍ ስራቸዉ እጅግ ታዋቂና የተከበሩ ናቸዉ፤ ምናልባትም ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ሩት እጅግ ታዋቂዋና ብቸኛዋ የጀርመናዊት ጋዜጠኛ ናቸዉ ማለትም ይቻላል።

Schriftstellerin Ruth Weiss

የ 90 ዓመትዋ ጀርመናዊት የሥነ-ጽሑፍ ሰዉ ሩት ቫይስ

ደቡብ አፍሪቃ ኬፕታዉን የሚገኘዉ የአይሁዳዉያን ቤተ-መዘክር የ 90 ዓመቷን ጋዜጠኛ፤ ለማወደስ አንድ የህይወት ዘመን ታሪካቸዉን የሚያሳይ አዉደ- በማዘጋጀት ክብሩን ገልጾአል። የዶቼ ቬለዉ ክላዉስ ሽቴከር ጀርመን አፍሪቃዊትዋን የምዕተ ዓመት የታሪክ መስካሪ ሩት ቫይስን አነጋግሮዋቸዋል።

« ከሁሉ ነገር በቅድሚያ ልጠይቅ የምወደዉ,,,» ሲሉ ነዉ፤ ጋዜጠኛ ሩት ቫይስ አብዛኛዉን ግዜ ለዘገባ የሚያደርጉት ቃለ-ምልልሳቸዉን የሚጀምሩት። ሩት ቫይስ የአፍሪቃ የሙዚቃ ንግሥት ማርያ ማኬይባን፤ ደቡብ አፍሪቃዊትዋን የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚ ናዲን ጎርዲሜርን በቅርበት አግኝተዉ አነጋግረዋቸዋል። ቀድሞ ሄንሪ ኪሲንገር ይባሉ ከነበሩት ከታዋቂዉ የዩኤስ አሜሪካ የቀድሞ ፖለቲከኛ እና የቀድሞ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂንሪ ኪስድሼ ጋርም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል። የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላንም በግል መኖርያ ቤታቸዉ ገበታ ቤት ጠረቤዛ ላይ ፊት ለፊት ተቀምጠዉ አጫዉተዋቸዋል። ሩት ቫይስ የዚምባቤዉን ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን በመዝናኛ ፓርካቸዉ ዉስጥ ለዜና ዘገባቸዉ ቃለ-ምልልስ ሲያደርጉ የቀድሞዉ የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካዉንዳ መቅረፀ ድምፁን በመያዝ አግዘዋቸዋል።

Buchcover Ruth Weiss A Pass through Hard Grass. A Journalist's Memories of Exile and Apartheid

ሩት ቫይስ በጎርጎረሳዊዉ 1980 ከፕሪዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና ቆየት ብሎ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማት ካገኙት ናዲን ጎርድሜር« ይህ ሊሆን የቻለዉ ሁሉንም ስልጣን ሳይዙ ገና ትግል ላይ ሳሉ ስለማዉቃቸዉ ነዉ። ይህ እድል ነዉ ጠቅሞኝ ፤ በመካከላችን እምነት ሰፍኖ እንደ ጓደኛ የሆነዉ። ብቻ ለዚህ የበቃሁት እድለኛ ሆኜ ነዉ።»

ሩት ቫይስ ከዚህ ቀደም ሲል እድል ቀንቶአቸዉ ነዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሄድ የበቁት። በጎርጎረሳዊዉ 1933 ዓ,ም በጀርመን የናዚ አስተዳደር ስልጣን ሲይዝ የሩት አባት በጡረታ ተገለሉ። አባታቸዉ በጡረታ የተገለሉበት ምክንያት ደግሞ አይሁዳዊ ስለነሆኑና በጀርመን ዉስጥ የትኛዉም ቦታ ሥራ ማግኘት ባለመቻላቸዉ ነበር። በዚህም ምክንያት የሩት ቫይስ ቤተሰብ ጥሩ ተስፋን ሰንቆ በጎርጎሮሳዊዉ 1936 ዓ,ም ይኖሩበት ከነበረዉ ከደቡባዊ ጀርመንዋ ከባቫርያ ግዛት ፉርት ከተማ ወደ ደቡብ አፍሪቃዋ ኬፕታዉን ከተማ የተሰደዉ። ሩት ቫይስ የደቡብ አፍሪቃ ዜግነትን ሲይዙ የ12 ዓመት ታዳጊ ነበሩ። ሩት ቫይስ በደቡብ አፍሪቃ የአይሁዳዉያን ባህላዊ ሕብረት ዉስጥም የግራ እና የለዘብተኛ ፓለቲካ አራማጅ ምሁራን ጋም ይገናኙ ነበር። በዚህ ሕብረት ዉስጥም ቆየት ብሎ ጋዜጠኛ ባለቤታቸዉን ሃንስ ቫይስን እንዲሁም እዉቋን የደቡብ አፍሪቃ የሥነ-ጽሑፍ ሰዉ ናዲን ጎርድሚርን ተዋወቁ ። ናዲን ጎርድሚር በሕብረቱ ዉስጥ ስለ ፖለቲካ ዘረኝነትና ባህል ነክ ጉዳዮች ላይ ከወንዶች ጋር ሲወያዩና ሲከራከሩ የቆዩ ቢሆንም፤ ታዛዥዋን የጋዜጠኛ ሃንስ ቫይስ ባለቤትን ሩት ቫይስን ግን የተዋወቁት በጣም ዘግይቶ ነበር፤ « አንድ ጊዜ ስለ ሥነ-ጽሑፏ ወይስ ስለ መጽሐፍዋ መወያየታችንን ተጠይቄያለሁ። ግን አይደለም! ያ የሁለታችን ርዕስ አልነበረም። በመካከላችን የነበረዉ ለአስርተ ዓመታት የዘለቀ በሴቶች መካከል ያለ የጠነከረ፤ ወዳጅነት ብቻ ነበር»

ደቡብ አፍሪቃዊትዋ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚ ናዲን ጎርድ ሜር እጅግ አይናፋር ለሆኑት ባልንጀራቸዉ ለሩት ቫይስ የነበራቸዉ ግምት አነስተኛ እንደነበርም ተናግረዋል። ሩት ቫይስ በመጀመርያ አጫጭር ድርሰቶችን ፤ ቆየት ብለዉ ደግሞ ረጃጅም ልብ-ወለዶችን፤ ወንጀል ነክ እና ለሕጻናት የሚሆኑ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ለአንባብያን አቅርበዋል። ስለ ሕግ ጉዳይ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት ባለቤታቸዉ ሃንስ ቫይስ ስለሕግ ያስረድዋቸዋል፤ በጋዜጠኝነት ሥራቸዉ ላይም ያሳትፎአቸዉ ነበር። በዚህም ነዉ ሩት ቫይስ ለመጀመርያ የመስክ ሥራ ዘገባ ቀድሞ ታንጋኒካ በመባል ወደምትታወቀዉ ወደ ምሥራቅ አፍሪቃዊትዋ ሀገር ታንዛንያ ያቀኑት፤

«የዜና ዘገባ መሥራት መቻሌን በፍፁም አላዉቅም ነበር። እጅግ ፍርኃትና ሥጋት ይዞኝ ነበር። ደግሞ ለዘገባዉ ወደ ዚያች ሀገር ከማቅናቴ በፊት እጅግ ብዙ ማንበብም ነበረብኝ። በዚያ ላይ ታንዛንያ ለኔ የማላዉቀዉ አዲስ ነገር፤ አዲስ ሀገር ነበር»
በርግጥም የሄዱበትን ሥራቸዉን ድንቅ በሆነ ሁኔታ አጠናቀቁ፤ ከዚያም በኋላ ይላሉ ሩት፤ የበላይነት ያሳየኝ ከነበረዉ ባለቤቴ ጋር ተለያየሁ። ሩት ቫይስ በደቡብ አፍሪቃ የነበረዉን የአፓርታይድ ስርዓት በመቃወም በወቅቱ የነበረዉን የነጭ አገዛዝ ሥርዓት በጥቁር መዝገብ ዉስጥ አስፍረዋል። ሩት ቫይስ ፋይናንሻል ታይምስ በተሰኘዉ ጋዜጣና በሌሎች እዉቅ ጋዜጦች ላይም አገልግለዋል። በዛምቢያ መዲና ሉሳካ እና ሃራሬ ዚምባቤ ላይ የኖሩት ትዉልደ ጀርመናዊት ጋዜጠኛ ሩት ቫይስ፤ አንድዬ ልጃቸዉን «ሳሻን» ያሳደጉት ብቻቸዉን ነዉ። በጋዜጠኝነት ሞያቸዉ ለዘገባ ወደ አንድ ቦታ መሄድ ሲኖርባቸዉ፤ ልጃቸዉ ሳሻን ይዘዉት ነበር የሚጓዙት። አንድ ግዜ ሉሳካ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ጣብያ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካዉንዳ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣንን ሲቀበሉ በሚታየዉ ወታደራዊ ሰልፍና አቀባበል ላይ ሩት ቫይስ ልጃቸዉ ሳሻን ይዘዉት ሄደዉ፤ ልጃቸዉ ሳሻ እንግዶች በተቀመጡበት የመጀመርያ ረድፍ ላይ ይታይ እንደነበር እንዲህ ያስታዉሳሉ፤

Buchcover Ruth Weiss A Pass through Hard Grass. A Journalist's Memories of Exile and Apartheid

በጎርጎረሳዊዉ 2014 ዓ,ም ለአንባብያን የቀረበዉ የሩት ቫይስ የህይወት ታሪክን የሚያስነብበዉ መፅሐፍ«የዛን እለት ምን እንደነካዉ አላዉቅም። ዝግጅቱ በነበረበት አዉሮፕላን ጣብያዉ ሜዳ ላይ እንደልቡ እየቦረቀ ይሮጥ ነበር በመጨረሻ መድፉ ወደተደረደረበት ሄዶ አንዱ መድፋ ላይ ጫፍ ድረስ ወጣ። ታድያ ይህን ሁኔታ የተከታተሉት ፕሬዚዳንት ካዉንዳ ወደ ህጻኑ አንድ የጸጥታ አስከባሪ ላኩ። ይህ የጸጥታ አስከባሪ ሳሻን ያዘና ትከሻዉ ላይ አስቀምጦ ካዉንዳ ጋር ይዞ ቀረበ። ታድያ ይህ ሁኔታ በሌሎች አዉሮጳ ሃገራት ቢታይ ኖሮ ትልቅ አወዛጋቢ ርዕስ ሆኖ ይከርም ነበር»
ሩት ቫይስ ፤ ከዘጠና ዓመቱ የቀድሞ የዛንብያ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካዉንዳ ጋር አሁንም ወዳጅ ናቸዉ።

በ1970 ዎቹ ሩት ቫይስ ባደረጉት አንድ ቃለ-ምልልስ ላይ የጤና ችግር እንዳለባቸዉ ከድምፃቸዉ መረዳት ይቻላል። ይህን የተረዱት ፕሬዚዳንት ካዉንዳ ሩት ቫይስ ተናግረዉ እስኪጨርሱ በትዕግስት ጠብቀዉ፤ መቅረፀ ድምፁን ተቀብለዋቸዉ እራሳቸዉ ይዘዉ መቅዳት ጀመሩ፤ ሩት ቫይስ የዘጠናኛ ዓመት የልደት በዓላቸዉን ሲያከብሩ በቀድሞዉ የዛንቢያ ፕሬዚዳንት ብቻ አይደለም ያስታወሱዋቸዉ፤ በልጅነት ግዚያቸዉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በቫባርያዋ ግዛት ፉርት ከተማ ሲከታተሉ አብረዋቸዉ የተማሩት የቀድሞዉ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ኪሲንገር እና ደቡብ አፍሪቃዊትዋ ከሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚ ናዲን ጎርዲሜም የእንኳን አደረሶ መልክት በማኅበረሰብ መገናኛ መረብ «በፊስ ቡክ» አድርሰዋቸዋል። « እኔ የፊስ ቡክ አፍቃሪና ተጠቃሚ አይደለሁም፤ ግን ከቀናቶች በፊት በዚህ የማኅበረሰብ መገናኛ መረብ ከተመዘገብኩ በኋላ ነዉ ከኪሲንጀር የእንኳን አደረሰሽ መልክት የደረሰኝ። ከሌላኛዉ ጫፍ ወደ እዚህኛዉ ጫፍ የደረሰ መልክት ነዉ። በጣም ደስ የሚል ነገር ሆኖ ነዉ ያገኘሁት።»

በሌላ በኩል 90 ኛ ዓመታቸዉን ስላከበሩት ስለ ሮበርት ሙጋቤ ሩት ቫይስ የሚናገሩት ብዙም ጥሩ የሆነ አስደሳች ነገር የላቸዉም። ትዉልደ ጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ ሩት ቫይስ ከሮበርት ሙጋቤ የመጀመርያ ሚስት ወ/ሮ ሳሊ ጋር ባልንጀራ ነበሩ። በጎርጎሮሳዊዉ 1980 ዓ,ም ሙጋቤ የደቡብ አፍሪቃዊትዋ ጎረቤት ሀገር የዚምባቤ የመጀመርያዉ ጥቁር ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዉ ሲመረጡ፤ ሩት ቫይስ ሙጋቤን እንኳን ደስ ያሎት ለማለት በመኖርያ ቤታቸዉ በሚገኘዉ ፓርክ ሙጋቤንና ቤተሰቦቻቸዉን እንዲሁም ጥቂት ጓደኞቻቸዉን ጠርተዉ ለክብራቸዉ ደግሰዉላቸዉ ነበር።
«ሙጋቤ ተጋብዘዉ ወደኛ መምጣታቸዉን በደስታ እየተጠባበቅን ነበር። ባለቤታቸዉ ሴሊም ብትሆን ሁኔታዉ ጥሩ እንዲሁን ሁሉን ነገር አዘጋጅታ ነበር፤ እጅግ ጥሩ ስሜትና ደስታ ላይ ሆነን የሙጋቤን መምጣት እየተጠባበቅን ነበር። ቆየት ብለዉ ሙጋቤ መጡ ፤ ታድያ አለቃዉ ወደቤት ሲገቡ ለሰላምታ እጃቸዉን ለመስጠት እንኳ አልዳዳቸዉም ፤ አንድ ሁለት ሰዎችን ጨበጡና ፤ አንድ ክፍል ዉስጥ ሄደዉ ብቻቸዉን ተቀመጡ።»

ሩት ቫይስ ሙጋቤ በዚያች ዕለት ያሳዩት ባህሪ፤ ቀደም ሲል የሚታወቁበትን ባህሪ ትተዉ የጨቋን እና የገዥ ባህሪ ምዕራፋቸዉን የከፈቱበት ዕለት ነበር ሲሉ ነዉ እስከ ዛሬ የሚያያስቡት። ለጀርመናዊትዋ አንጋፋ ጋዜጠኛ ለሩት ቫይስ ሙጋቤ ብቻቸዉን አሳቢና አቅለቢስ ናቸዉ። በጎርጎረሳዊዉ 1980 ዓ,ም ዚምባቡዌ ከቅኝ ግዛት ነጻ እንደወጣች ስልጣን ላይ የመጡት ሙጋቤ፤ የአገዛዝ ክርናቸዉን አጠንክረዉ በሀገሪቱ ፍርሃትን አነገሱ። በዚንባቡዌ የስልጠና ትምህታቸዉን ይከታተሉ የነበሩት የዚያን ግዜዋ ወጣት ጋዜጠኛ ሩት ቫይስም እዉነት ያዘሉ ዘገባዎችን ለአንባቢን ለማቅረብ ድፍረቱን አጡ። በዚህም ምክንያት ስልጠናዉን አቋርጠዉ ዚንባቡዌን ለቀዉ ለመዉጣት እንደወሰኑ፤ በጎርጎረሳዊዉ 1990 ዓ,ም አንድ ፍፁም ሌላ ገጽታ ያላቸዉና በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በዚንባቡዌዋ መዲና ሃራሬ ላይ ተከሰቱ። በስደት ያለዉ የ« ANC» ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የመሪ አካል ሃራሬ አዉሮፕላን ማረፍያ የመጀመርያ ስልጠናን ለመካፈል ለሚገቡት አባላት አቀባበል ለማድረግ መፈለጉን ሩት ቫይስ ያስታዉሳሉ። ለስልጠና ይመጣሉ ተብሎ የተጠበቀዉ ጥቁር የፓርቲ ካድሪዎች ነበሩ ። በዚያ ምትክ ግን ከአዉሮፕላን ጣብያዉ የወጡት ሁለት የምዕራባዉያን ገጽታ ያላቸዉ ነጫጭ ዉብ ሴቶች ነበሩ፤ ሩት ቫይስ በመቀጠል እንዲህ ይተርካሉ

« በመጀመርያ እጅግ ድንጋጤ የተሞላበት ፀጥታ ሰፈነ። በጣም የሚገርም ሁኔታ ነበር። ከዚያ እንደገና በሩ ተከፈተና ማንዴላ ገቡ፤ ቀጠሉና ወደ ጎን ወደ ኋላ ተመለከቱና ከሁለቱ ሴቶች መካከል ተቀመጡ። ማንዴላ በግራም በቀኝም የተቀመጡትን ሴቶች ዞር እያሉ ተመከቱና እንኳን ደህና መጣችሁ፤ ወደ ዚምባቡዌ እንኳን ደህና መጣችሁ አሉ በአፍሪካንስ ቋንቋ። በዚህም ፀጥታዉን ሰበሩት። እንዲህ ናቸዉ፤ ማንዴላ። » አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ሩት ቫይስ ይህን የመሳሰሉ አጓጊ ትዉስታና ታሪኮች አልዋቸዉ። ምንም እንኳ የ90 ዓመት አዛዉንት ቢሆኑም የማስታወስ ችሎታቸዉ አሁንም ጠንካራና ብሩህ በመሆኑ በርካታ አፍሪቃ ነክ ታሪኮችን እና ተሞክሮዎቻቸዉን መናገር ይችላሉ። ደቡብ አፍሪቃ ኬፕታዉን ከተማ ላይ የአይሁዳዉያን ቤተ- መዘክርና ባዝለር የተሰኘዉ የአፍሪቃዉያን ታሪክ ማተምያ ቤት ሩት ቫይስን ለማወደስ በጋዜጠኝነት ሞያ ባገለገሉባቸዉ ዘመናት ያበረከትዋቸዉን ሥራዎች በአዉደ ርዕይነት አቅርቦላቸዋል።


አይሁዳዊትዋ ሩት ቫይስ ከጀርመን ጋር እርቅን የፈጠሩት ዘግየት ብሎ ነዉ። በጎርጎረሳዊዉ 1970 ዎቹ አጋማሽ ለዶቼ ቬለ በጋዜጠኝነት ሞያቸዉ ማገልገል የጀመሩት ሩት ቫይስ፤ የጀርመን ህዝብ ስለናዚ የግፍ አገዛዝ ታሪክ ማስታወስ አለመፈለጉን ሲያዩ ከሕሊናቸዉ ጋር ትልቅ ሙግት ጀምረዉ ከባድ ግዜን አሳልፈዋል። ሩት በደቡብ አፍሪቃ፤ በዛምቢያ፤ በዚምባብዌ እና በብሪታንያ ለዘመናት ከኖሩ በኋላ ዛሬ ቀሪ ኑሮአቸዉን በጀርመን ሉዲንግ ሃዉዘን ከተማ ላይ አድርገዋል። ጀርመን ዉስጥ አንድ ትምህርት ቤት በስማቸዉ ተሰይሞላቸዋልም፤ መጻሕፍቶቻቸዉም ለሥነ-ጽሑፍ ማስተማርያነት በጀርመን ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ላይ ዉለዋል። ሩት ቫይስ በጀርመን የሚታያቸዉ አዲስ ትዉልድ ነዉ። አሁን መኖርያቸዉ ባደረጉባት በምዕራባዊ ጀርመን በምትገኘዉ ሉዲንግሃዉዘን አነስተኛ ከተማ ለሚገኙ ሕፃናት እና ወጣቶችም ስለዘር፤ ስለአፓርታይድ የዘረኛ አገዛዝ እንዲሁም ስለብሔራዊ ሶሻሊዝም ሳይደክሙ ገለፃን ያደርጋሉ።

«ለአንድ ወጣት የቀድሞ ታሪክን ጠንቅቆ የሚያዉቅ ግለሰብን አግኝቶ በቀጥታ መጠየቅ መቻሉ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነዉ። በዚህ ምክንያት እኔ በህይወቴ እስካለሁና እስከቻልኩ ድረስ ሰዉን አቅርቤ ለጥያቄዎች ሁሉ መልስን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ።»
የ 90 ዓመትዋ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሩት ቫይስ ሙሉ ህይወታቸዉን ትክክለኛ ነገር ለማድረግ ጥረት እንዳደረጉት ሁሉ፤ በቀጣይም ትክክል ነገር ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።


ክላዉስ ሽቴከር / አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic