ጀርመን በዘር ማጥፋት ተከሰሰች | አፍሪቃ | DW | 06.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ጀርመን በዘር ማጥፋት ተከሰሰች

ሁለት የናሚቢያ ጎሳዎች የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች የሚሏት ጀርመን ላይ በኒው ዮርክ ክስ መስርተዋል። የሔሬሮ እና የናማ ጎሳዎች በቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ላይ ባመጹበት ወቅት የጀርመን ወታደሮች ተቃውሞውን ለማብረድ በወሰዱት እርምጃ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:15
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:15 ደቂቃ

ጀርመን በዘር ማጥፋት ተከሰሰች

የታሪክ ታዛቢዎች የ20ኛው ክ.ዘ. የመጀመሪያው የዘር ማጥፋት ወንጀል ይሉታል። ወደ 100,000 የሔሬሮ እና ናማ ጎሳ አባላት በዛሬዋ ናሚቢያ ከጎርጎሮሳዊው 1904 እስከ 1905 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት በጀርመን ቅኝ ገዢዎች እጅ ማለቃቸው ይታመናል። በጊዜው የዛሬዋ ናሚቢያ የጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ተብላ የምትጠራ ቅኝ ግዛት ነበረች። በ1904 ዓ.ም. በቅኝ ገዚዎቻቸው ላይ ለተቃውሞ የወጡት የሔሬሮ እና የናማ ጎሳዎች በጀርመን ወታደሮች ወደ በረሐ ተባረሩ። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት በረሐብ አለቁ። በርካቶችም ጠፉ። በቅኝ ገዢዎቹ እርምጃ 80 በመቶ የሔሬሮ ጎሳ አባላት እንዲሁም ከናማ ጎሳ ግማሽ ያክሉ አለቁ። ይኸ ሁሉ ግን ለበርካታ አመታት ለአውሮጳም ሆነ ለአፍሪቃ ተዘንግቶ የቆየ የሰቆቃ ታሪክ ነው። 

ወንጀሉ የተፈፀመባቸዉ የሁለቱ የናሚቢያ ጎሳዎች ተወካዮች  ካሳ ሊከፈለን ይገባል በማለት ሲሟገቱ አመታት አስቆጥረዋል።አሁን ክስ የመሰረቱት የፖለቲካዉ ሙግት ዉጤት አላመጣ ስላለ ይመስላል። የድርድሩን ሒደት አጥብቀው ከሚተቹት መካከል አንዷ የሆኑት የሔሬሮ ጎሳ ተወካይ ኤስተር ሙይንጃንጉዌ «ለእኛ ሒደቱ በሕፀጽ የተሞላ ነው። ጉዳዩን የሚመለከቱበት መንገድም ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው። በጉዳዩ ላይ የሚደራደሩት ወገኖች ሁለቱ ልዩ ልዑኮች እንዲሆኑ የወሰነው ማን ነው? እኛን ሳያማክሩ  የወሰኑት ሁለቱ መንግሥታት ናቸው። በሒደቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን ተገፍተናል።» ሲሉ ይተቻሉ። ከጎርጎሮሳዊው 1904-05 ዓ.ም. የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ጀርመን ዘር ማጥፋት ተብሎ መጠራቱን ባትክድም ካሳ ለመክፈል ግን ስታንገራግር ቆይታለች። 

በኒው ዮርክ የማንሐታን ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ መሰረት ያለ ምንም የካሳ ክፍያ በያኔዋ ቅኝ ገዥ ጀርመን ባለስልጣናት ውሳኔ ከፍተኛ ሥፋት ያለውን መሬታቸውን ለጀርመን ሰፋሪዎሪዎች እንዲለቁ ተገደዋል።ፍርድ ቤቱ፤ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለል የቆየውን ጉዳይ ለመዳኘት ሥልጣኑ እንዳለው  ገና አልታወቀም።ጀርመንን ወክለው ከናሚቢያ ጋር ለዓመታት በጉዳዩ ላይ የተደራደሩ ፖለቲከኛ ሩፕሬሽት ፖለንዝ  «ይኼ ጉዳይ ጫናው እየጎለበት ይሔድ እንደሁ የሚታወቀው ፍርድ ቤቱ ክሱን ለውሳኔ የተቀበለ እንደሁ ነው። ማንኛውም ፍርድ ቤት የቀረበለትን ክስ የመዳኘት ሥልጣን እንዳለው ይመረምራል። መመርመር ብቻም ሳይሆን ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ሕጋዊ መሰረት መኖሩንም ያጤናል።» ሲሉ ተናግረዋል።  
አንድ የጀርመን ፖለቲከኞች በበኩላቸው አገራቸው ጉዳዩን የያዘችበት መንገድ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።የግራዎቹን ፓርቲ ወክለው የአገሪቱ ምክር ቤት አባል የሆኑት ኒማ ሞቫሳት
« የዘር ማጥፋት ነበር አልነበረም የሚለውን ለመወሰን ጀርመን ለረጅም ጊዜ ስታንገራግር ቆይታለች። ይኸ በእነሱ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል። ይፋዊ በሆነ መልኩ ዘር ማጥፋት ነው ብሎ መቀበሉ በርግጥም አንዳች እርምጃ ነው።  ሆኖም ግን ሁልጊዜም ከሔሬሮ እና ከናማዎች ጋር የቀጥታ ድርድር ማድረግ እንደሚገባቸው ሲናገሩ አይደመጥም። ስለ አንድ ማሕበረሰብ ዘር ማጥፋት  እያወራን ያን ማሕበረሰብ የማናናግር ከሆነ በውነቱ ያ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው እናም ሰዎቹም ከምር እንደተወሰዱ አይሰማቸውም።» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች