ጀርመን፤ በስደተኞች ላይ የተነሳው ተቃውሞ ተወገዘ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 23.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመን፤ በስደተኞች ላይ የተነሳው ተቃውሞ ተወገዘ

ድሬስደን አቅራቢያ ባሳለፍነው ዓርብ ምሽት ስደተኞች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ከመምጣታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ በቀኝ አክራሪዎች የደረሰውን ብጥብጥብ የጀርመን መንግሥት አወገዘ። የቀኝ አክራሪዎች ያደረሱት ነውጥ ቅዳሜ ዕለትም ተከስቷል።

የጀርመን የፍትህ ሚንስትር ሐይኮ ማስ «የውጭ ሃገር ነዋሪዎች ጥላቻ እና ዘረኝነትን አንታገስም» ሲሉ ትናንት ባስተላለፉት መግለጫ አስታውቀዋል። የጀርመን መንግስት በስደተኞች ላይ የደረሰውን ተቃውሞ ቢያወግዝም ብጥብጡ በሁለት ተከታታይ ምሽቶች ተከስቷል። በብጥብጡ ከቀኝ አክራሪ ነውጠኞች በተወረወሩ ጠርሙሶችና ተቃጣጣይ ቁሶች ሁለት የመንግስት ሠራተኞች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል። 250 የሚጠጉት የቀኝ አክራሪ ሰልፈኞች ድርጊትን በመቃወም ቀደም ብሎ በርካታ ሠልፈኞች አደባባይ ወጥተው ነበር። ትናንት ምሽት በነበረው ተቃውሞ 31 ፖሊሶች መቁሰላቸው ተዘግቧል።

ድሬስደን አቅራቢያ በምትገኘው ሃይደናው በተባለች ከተማ 90 ስደተኞችን የጫኑ ኹለት አውቶቡስች ትናንት መድረሳቸው ተዘግቧል። ስደተኞቹ ወደ ከተማዋ የተወሰዱት መጠለያ እንዲያገኙ በሚል መሆኑም ተገልጧል።
በያዝንው የጎርጎሪዮስ አመት ወደ ጀርመን የሚደርሱ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ከ800 ሺህ ሊልቅ እንደሚችል ይጠበቃል። የጀርመን ምክትል መራሄ መንግስት ሲግማር ጋብሬል አሁን የተከሰተው የስደተኞች ቀውስ ከሁለቱ ጀርመኖች ውህደት በኋላ ትልቁ ፈተና መሆኑን ዛሬ ተናግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ