ጀርመን-ምርጫ 2002/ የፖለቲካ ሥርዓት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 27.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመን-ምርጫ 2002/ የፖለቲካ ሥርዓት

የጀርመን የፖለቲካ ሥርአት፥ፓርቲዎችና የዛሬ ዋና ዋና ተፎካካሪዎች

default

በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ማግሥት የያኔዋ ምዕራብ ጀርመን መከተል የጀመረችዉ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት የመላዉ ጀርመን መርሕ ከሆነ ዘንድሮ አስራ-ዘጠነኛ አመቱ። የመጀመሪያዉ ፌደራላዊ መንግሥት ሲመሰረት ከሰወስት የማይበልጡት የፖለቲካ ማሕበራት ዛሬ ሥድስት ደርሰዋል።በዛሬዉ ምርጫ የሚወዳደሩት እነዚሕ የፖለቲካ ማሕበራት እንደየዘመኑ ሒደት፥ እንደ ፖለቲካዊዉ ጥያቄና የሕዝብ ፍላጎት ከጦርነቱ በፊት፥ በጦርነቱ መሐልና ከጦርነቱ በሕዋላ የተመሠረቱ ወይም የተጠናከሩ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ የጀርመንን የፖለቲካ ሥርዓት፥ የዛሬ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ማበራትን መርሕ፥ የዋና ዋና ፖለቲከኞችን አቋም ባጭሩ የሚቃኝ ዘገባ አለዉ።

ዋናዉ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ እንደሆነ በሚያምነዉ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በምትመራዉ ጀርመን ሕግ የሚያረቅና የሚወስነዉ፥መራሔ-መንግሥቱን የሚመርጠዉ፥ የመንግስቱን ሥራዎች የሚቆጣጠረዉ፥ አመታዊ በጀት የሚያፀደቀዉ የሐገሪቱ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት ነዉ።Bundestag-እንደ ጀርመንኛዉ።ምክር ቤቱ የተለየ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ዛሬ እንደሆነዉ ሁሉ በየአራት አመቱ አንዴ በሚደረገዉ ምርጫ በቀጥታ በሕዝብ የተመረጡ ስድስት መቶ እንደራሴዎች አሉት።

ለዚሕ ምክር ቤት አባልነት እስከ ዛሬ የተደረገዉ የምረጡኝ ዘመቻ ብዙዎች እንዳሉት በርግጥ አሰልቺ ነበር።የየፖለቲካ ማሕበራቱ መሪዎች፥ እጩ እንደራሴዎችና ደጋፊዎች ያደረጉት ክርክር፥ብዙ የሚስብ አልነበረም።በትላልቆቹ የፖለቲካ ማሕበራት መርሐ-ግብር መካካል ብዙ ልዩነት አይታይም።

ያም ሆኖ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት እስካሁን በስልጣን ላይ ያለዉን ተጣማሪ መንግሥት የሚመሩት መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከዛሬዉ ምርጫ በሕዋላም የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ መቀጠላቸዉ አይቀርም።ሜርክል የሚመሩት ክርስቲያናዊ-ዲሞክራሲያዊ ሕብረት (CDU)-በጀርመንኛ ምሕፃሩ ከሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ካልተጣመረ ግን ብቻዉን መንግሥት ሊመሰርት አይችልም።

Logo CDU/CSU

በዚሕም ምክንያት አስተያየቱ ከያዘ-ሜርክል የመራሔ-መንግሥትነቱን ሥልጣን እንደያዙ የሚቀጥሉት ፓርቲያቸዉ ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ ቢያንስ ካንዱ ተጣማሪ መንግሥት ሲመሰርት ነዉ።ከማን ጋር? ይሕ ጥያቄ የምርጫ ዘመቻዉን አሰልቺነት-እያዋዛ የመራጭ-ተመራጭ፥ ያስተንታኙን ልብ አንጠልጥሎ-ሲያነጋግር፥ ሲያከራክር፥ መላ ሲያስመታ ቆይቷል።ከዛሬ በሕዋላ ይለያል።

አሁን ሜርክል የሚወክሉት የክርስቲያናዊ-ዲሞክራሲያዊ ሕብረት (CDU) እሕቱ ከምትባለዉና ባየር (ወይም ባቬሪያ በእንግሊዝኛዉ) ክፍለ-ግዛት ከምትንቀሳቀሰዉ ከክርስቲያናዊ-ሶሻል ሕብረት (CSU) ጋር በመሆን ለፌደላራዊ ጀርመን አብዛኞቹን መራሕያነ-መንግሥት ያፈራ ፓርቲ ነዉ።ከኮንራድ አደናወር ጀምሮ በሔልሙት ኩል አቋርጦ አንጌላ ሜርክልን ያፈራዉ CDU ሥሙእንደሚያመለክተዉ ከካቶሊክ ክርሲያቲያኖች የመነጨ ነዉ።

ሑለተኛዉ የአለም ጦርነት እንዳበቃ አብዛኞቹ የካቶሊክ ክርስቲያን መራጮች ወደ መሐል የተጠጋ አቋም ያለዉ የፖለቲካ ፓርቲ አገኙ።ሕብረቱ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅበት የጥቁር ቀለም አርማዉ ምንጭም ከኒያ ወደ መሐል ከሚያዳሉት ወገኖች የወጣ ነዉ።ለዚሕ መለያ እንዲሆንም ጥቁር የለበሱ የካቶሊክ ቀሳዉስት ምክር ቤት ይቀመጡ ነበር።እንደ እሕትማማች የሚታዩት ሁለቱ ፓርቲዎች ግን ክርስቲያናዊ የሚለዉን ከስም ባለፍ ብዙ አይጠቀሙበትም።ፓርቲዉና አባላቱ በፖለቲካዉ አለምም «ወግአጥባቂ» በሚለዉ ቅፅል-ነዉ የሚታወቁት።

የሁለቱ ፓርቲዎች አመሠራረት፥ ልማዳዊ ዳራም ሐይማኖታዊ ቢሆንም እንደ ሕዝባዊ የፖለቲካ ማሕበራት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸዉ በሚችሉት ሁሉ አግባቢ መርሆችን ይከተላሉ።ብዙ ጊዜ ተጣማሪ መንግሥት የሚመሰርቱት በአቋም ከሚቀራረቡት ከነፃ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (FDP) በጀርመንኛ ምሕፃሩ ጋር ነዉ።አልፎ አልፎ ግን ላለፉት አራት አመታት በስልጣን ላይ እንዳለዉ መንግሥት የጀርመን ሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ (SPD) ጋር ታላቁ ጥምረት የተሰኘዉን መንግሥት እየመሰረቱ ይሰራሉ።

ዛሬ በሚሰጠዉ ድምፅ የሚጠናቀቀዉ የዘንድሮዉ ምርጫ ግንባር ቀደም ተፎካካሪዎችም ሁለቱ ፓርቲዎች፥ ለመራሔ መንግሥትነት የሚፎካከሩት ደግሞ የተጣማሪዉ መንግሥት መራሒተ-መንግሥት እና የምክትል መራሔ መንግሥትነቱን ሥልጣን ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱ ጋር ደርበዉ የያዙት ቫልተር ሽታይን ማየር ናቸዉ።

የምርጫ ዘመቻቸዉ በሕዝብ አስተያየት የተደገፈላቸዉ ሜርክል ተጣማሪዉ መንግሥት ባለፉት አራት አመታት በጎ ምግባር ያከናወነዉ እኔ ሥለመራሁት ነዉ-ባይ ናቸዉ።

«ከሁሉ በፊት ሊነገር የሚገባዉ ነገር፥ ይሕ የታላቁ ጥምረት መንግሥት ጥሩ ሥራዎች ያከናወነዉ በእኔ መሪነት መሆኑ ነዉ።»

ክርስቲያናዊ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት (CDU) እና የክርስቲያናዊ ሶሻል ሕብረት (CSU) አደናወር፥ ኮል ሜርክል እንዳፈሩ ሁሉ የጀርመን ሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ-SPD በጀርመንኛ ምሕፃሩ ቪሊ ብራንት፥ ሔልሙት ሽሚት እና በቅርቡ ደግሞ ጌርሐርት ሽሩደርን የመሳሰሉ ጠንካራ፥ በሳል፥ አርቆ አስተዋይ መሪዎች ለጀርመን ምናልባትም ለአለም አበርክቷል።

Logo SPD

ቀይ አርማዉን በ19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ደምቆ ከነበረዉ ከወዝአደሩ ንቅናቄ መለያ ነዉ-የወረሰዉ።ከቫይናመር ሪፐብሊኮች ዘመን ጀምሮ-በዚሕ ስም የሚጠራዉ ይሕ ፓርቲ አሁን ካሉት የጀርመን የፖለቲካ ማሕበራት ሁሉ አንጋፋዉ ነዉ።ይሁንና በ1930ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በሒትለር መሪነት ሥልጣን የያዘዉ ብሔራዊ ሶሻሊስቶች ፓርቲ እንደብዙዎቹ ሌሎች የፖለቲካ ማሕበራት ሁሉ SPDንም አግዶት ነበር።

ብዙ አባላቱም በየማጎሪያ ጣቢያዉ ታስረዉ ነበር።ጦርነቱ ካበቃ በሕዋላ አባል መሪዎቹ ለብዙ ጊዚያት በርዕዮተ-አለም ልዩነት ሰበብ ሲወዛገቡ ነበር።ፓርቲዉ በ1959 የጠራዉ ጉባኤ የአባላቱን ልዩነት ማርገብ ችላል።ጉባኤዉ «የጎደስበርግ-ፕሮግራም» ባለዉ መርሁ ፓርቲዉ በርዕዮተ-አለለምም ሆነ በአቋም ከሲሻሊስታዊ ወዛደራዊ ፓርቲነት ወደ ሶሻልዲሞክራሲያዊ ፓርቲ መለወጡን አስታወቀ።ለዉጡ ከሁሉም የማሕበረሰብ ክፍል ደጋፊዎችና መራጮች እንዲኖሩት ያለመ ነበር።

እስካሁን ጀርመንን የሚመራዉ ተጣማሪ መንግሥት ካከናወናቸዉ ምግባራት ዋነኛዉ እንደ ብዙዎቹ የበለፀጉት ሐገራት ሁሉ ጀርመንን የመታዉን የገንዘብና የምጣኔ ሐብት ቀዉስ መከላከል ነበር።ተጣማሪዊ መንግሥት በዚሕ ረገድ በርግጥ ተሳክቶላታል።መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በእኔ አመራር የተገኘ ድል-የሚሉት ይሕን ዉጤት-SPD ወክለዉ ለመራሔ መንግሥትነት የሚፎካከሩት ምክትል መራሔ መንግሥትና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫልተር ሽታይን ማየር የፓርቲዬ በሳል ሰዎች ዉጤት ነዉ-ባይ ናቸዉ።

«ቀዉስ ዉስጥ የነበርንባቸዉን ያለፉትን ሰባትና ስምንት ወራት መለስ ብዬ ሳስብ ብዙዎቹ ችግሮች በሶሻልዲሞክራቲኩ (ፓርቲ) የመፍትሔዎችና ፅንሰ-ሐሳቦች መቃለላቸዉ ይታወሰኛል።ከገንዘብ ሚንስትር ሽታይንቡሩክ እስከ የሥራና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚንስትር፥ እስከ ምክትል መራሔ መንግሥት (እራሳቸዉ ናቸዉ) ያሉ ሚንስትሮች የከሰሩ የገንዘብ ተቋማት የሚሰጠዉን ድጎማ፥ ለአጭር ጊዜ ሥራ ያቀድነዉ የመወረት መርሐ-ግብር፥ ሁሉም፥ እንዳዴ ከተጣማሪዎቻችን ጋር አጥብቀን እየተሟገትን ገቢር ያደረግ ነዉ በሙሉ ሶሻል ዲሞክራቶቹ የወጠኑት እቅድ ነዉ።»

የሕዝብ አስተያየቱ ይዞ ዛሬ በተሰጠዉ ድምፅ የክርስቲያናዊ እትማማቾች ፓርቲዎች አብላጫ ድምፅ ቢያገኙ እንኳን ሶሻል ዲሞክራቱ ወደፊት የሚመሠረተዉ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሆኑ አያጠያይቅም።CDU/CSU የሚያገኙት ድምፅ የታላቁ ተቀናቃኛቸዉን የSPDን ጥምረት የማያስፈልጋቸዉ አይነት ከሆነ ተጣማሪ መንግሥት የሚመሠርቱት ከFDP ጋር እንደሚሆን የእስካሁኑ ታሪክ፥ የሰሞኑ የምርጫ ዘመቻ፥ የፓርቲዎቹ ዝንባሌም መስካሪ ነዉ።

Flash-Galerie Wochenrückblick KW 3 2010 Logo FDP Parteispenden

እንደ ጀርመንኛዉ FDP ተብሎ የሚጠራዉ የነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲ በክርስቲያናዊዎቹ እትማማች ፓርቲዎችና በሶሻል ዲሞክራቶቹ መካካል ያለዉን የግኝ-ግራ ክፍተት ለመሙላት ያለመ ይመስላል።ለዘብተኛ።እስከ 1990ዎቹ ካንዴ በስተቀር ሁል ጊዜ ከሁለቱ ትላልቅ ፓርቲዎች ከሚያሸንፈዉ ጋር እየተጣማሩ ከጀርመንን መንግሥትነት ስልጣን ርቆ አያዉቁም።በዚሕም ምክንያት መገናኛ ዘዴዎች አንጋሽ የሚል ቅፅል ደርበዉለታል።

የፓርቲዉ አለማ ከዝቅተኛና ከከፍተኛዉ ይልቅ በትምሕርቱ ጠለቅ፥ በገቢዉ ደልደል ላለዉ ለመካከለኛዉ መደብና ለመለስተኛዉ ከበርቴ-የሚያዳላ በሆኑ-የንዑስ ከበርቴዎች ማዕከል ተደርጎ ይታያል።በ19 መቶ ክፍለ-ዘመን ከነበረዉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የተወለደዉ ፓርቲ አርማዉ ቢጫ ነዉ።ፓርቲያቸዉን ከዘጠኝ አመት ተቃዋሚነት አዉጥተዉ የመንግሥት ከመንግሥት ተቋዳሽነት ለማብቃት የሚጓጉት ፖለሚከር ቬስተርቬለ የእስካሁን ተጣማሪ መንግሥት በሰሉ ቃላቶች ነዉ-የሚወርፉት።

«ከዚሕ መንግሥት ምናልባት ያተርፍነዉ ነገር ካለ (ሐብት) መሟጠጥ ብቻ ነዉ።ከዚሕ ዉጪ ሌላ የታየ ዉጤት የለም።»

በፌደራላዊ ጀርመን ገና ከጅምሩ ባየር ላይ CSUን እንደ እሕት ፓርቲዉ የሚያየዉ CDU አብላጫ ድምፅ ባገኘ ቁጥር እስካሁን ባለዉ የጀርመን ታሪክ ከሁለቴ በስተቀር ተጣማሪ መንግሥት የሚመሰርተዉ ከFDP ጋር ነበር።FDP ሥልጠን ለመጋራት ግድ ካልሆነበት በስተቀር ከSPD ጋር መጣመሩን አይፈቅደዉም።

በ1980ዎቹ አረጋንዴዎቹ በሚል ሥም የተጣማሩት የተለያዩ ማሕበራት እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሲደራጁ ግን FDP በSPD ላይ የነበረዉ ኩራት፥ የSPDም ብቸኝነት አበቃ።ሥሙም አርማዉም በአረንጓዴ ቀለም የተሰየመዉ የፖለቲካ ማሕበር መሠረቱ በ1960ዎቹ ማብቂያና በሰባዎቹ የነበረዉ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ፥ የሴቶች እኩልነት፥ የባሕል ተሐድሶ፥ የፀረ-ጦርነት ንቅናቄ ነዉ።ባብዛኛዉ በከፍተኛ ትምሕር ተቋማት የነበረዉን ይመሩ የነበሩት የተፈጥሮ ሐብት ተቆርቋቂዎች፥ የፀረ-ኑክሌርና የሴቶች እኩልነት ተሟጋቾች በ1980ቹ አጋማሽ ዛሬ ከማሕበራዊ ተፎጥሯዊ ንቅናቄ ወጥተዉ የፖለቲካ ማሕበር ሆኑ።

Logo Bündnis 90/Die Grünen

የአረንጓዴዎቹ ጥምረት 90 በሚል ሥም የተደራጀዉ የፖለቲካ ፓርቲ በ1990 አጋማሽ ከሶሻል ዲሞክራቶቹ ጋር ተጣምሮ የመንግሥት ሥልጣን ለመጋራት በቅቷል።የፓርቲዉ የበላይ ወይዘሮ ኩንሳት ላለፉት አራት አመታት ሥልጣን ያለዉ የታላቁ ጥምረት መንግሥት ከዛሬ በሕዋላ ማብቃት አለበት ባይ ናቸዉ።

«ታላቁ ጥምረት ለጥያቄያችን እስካሁን የሰጠዉ መልስ ታላቅ ችግሮችን ብቻ ነዉ።አሁን ሁሉም ሊያዉቀዉ የሚገባዉ ጉዳይ ብዙ እድሎች ማምለጣቸዉን ነዉ።ትላልቆቹ ችግሮች አልተፈቱም።ከዚሕ ይልቅ የታየዉ ትናንሽ አልማዞችና ባለበት መርገጥ ብቻ ነዉ።»

በ1990ዎቹ የጀርመን ዳግም ሁደት፥ የስፔዴ ከበርካታ አመታት በሕዋላ ለሥልጣን መብቃቱን ሲያስመሰክር ከዉሕደቱ በሕዋላ ባሉት የፖለቲካ ማሕበራት ቅር የተሰኙትን፥ የSPD የመሐል አዝማሚያ የሚቃወሙትን ፖለቲከኞችን አፍርቶ ነዉ-ያለፈዉ።ከምሥራቅ ጀርመኑ Partei des Demokratischen Sozialismus PDS እና ከሶሻል ዲሞክራቶቹ በጣም ወደ ግራ ፈንጠር የሚሉት ፖለቲከኞች በ2005 የግራ-ግራ መርሕ የሚከተለዉን የፖለቲካ ማሕበር መሠረቱ።

Flash-Galerie Gregor Gysi der Fraktionsvorsitzende der Partei Die Linke und Oskar Lafontaine Parteivorsitzende Bundestagswahl

ሥም-ግራዎች፥ አርማ ቀይ-ቀይ፥ የቀዮች ቀይ እንደማለትም ነዉ።ልብ የሚመታዉ በስተ-ግራ ነዉ ይላሉ እነሱ።ፓርቲዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድጋፉን እያሰፋ-በቅርቡ በተደረጉ የክፍለ-ሐገራት ምርጫ አስገራሚ በርካታ ድጋፍ አግኝቱ ሌሎቹን ፓርቲዎች አስደንግጧል።እንደ ግራ-ግራዎቹ ሁሉ ዘረኞችን፥ አፍቃሬ ናዚዎችን የሚያስተናብር የፖለቲካ ፓርቲም አለ።NPD በምሕፃሩ።-በፌደራል ደረጃ ብዙ ድጋፍ ግን የለዉም።

በዛሬዉ ምርጫ ማን-የትኛዉን ቦታ ይይዛል።ማታ ይለያል።

ነጋሽ መሐመድ