ጀርመን ለፀረ ኤቦላ ትግሉ የምትሰጠው ርዳታ መዘግየቱ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመን ለፀረ ኤቦላ ትግሉ የምትሰጠው ርዳታ መዘግየቱ

የጀርመን ፌደራል መንግሥት የኤቦላ ጉዳይ ተጠሪ ቫልተር ሊንድነር የጀርመንን ተሳትፎ ሲያወድሱ ሌሎች የርዳታ ድርጅቶች የጀርመን ድጋፍ የተጓተተ ነው በማለት ይተቻሉ። በዛሬው የአውሮፓ እና ጀርመን ዝግጅት የምናነሳው ርዕስ ነው ።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤቦላ ወረርሽኝ እስካሁን 5000 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። ሴራ ሊዮን ፣ ላይቤሪያ እና ጊኒ በተለይ በዚህ በሽታ ከተጠቁ የአፍሪቃ ሀገራት ዋንኞቹ ናቸው። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እነዚህን ሀገራት በገንዘብ፣ በመድሃኒት እና በሽታውን ለመቀነስ በሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ለመደገፍ ቃል ገብቷል። በመደገፍ ላይም ይገኛል። ይሁንና የጀርመን ድጋፍ እስከምን ድረስ ይሆን?

በኤቦላ ለተጠጉ ሀገራት ጀርመን ሙሉ በሙሉ ርዳታዋን መለገስ የጀመረችው፤ ወረርሽኙ ከተስፋፋ ከግማሽ ዓመት በኋላ ነው። እንደ የጀርመን ፌደራል መንግሥት የኤቦላ ጉዳይ ተጠሪ- ቫልተር ሊንድነር ፤ ጀርመን የዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶችን በተለያየ ረገድ እየተባበረች ትገኛለች።« ገና ቀደም ብለን የበረራ መስመር ዘርግተናል። ከዳካር - ሴኔጋል እስከ አክራ ጋና የሚዘልቅ እና ሶስቱን ዋና ከተሞች የሚያገናኝ። ከዓለም አቀፉ እና ከጀርመን የቀይ መስቀል ድርጅች ጋር በመተባበር ደግሞ አንድ ማዕከል በሴራ ሊዮን ኬኔማ ውስጥ እናዘጋጃለን። አልጋዎች እና መታከሚያ ጣቢያዎች ያሉት ማለት ነው። ከዚህም ሌላ ከጀርመን የጦር ሰራተኞች እና ከጀርመን ቀይ መስቀል ጋር ሞንሮቪያ ውስጥ መቶ አልጋዎች ያሉት የመታከሚያ ማዕከል እናዘጋጃለን። ይህም ዘገየ ቢባል በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል። ከዛም የመጀመሪያዎቹ በጎ ፍቃደኞች ሊመጡ ይችላሉ። እነሱም በድጋሚ ስልጠና ካገኙ በኋላ 100 አልጋ የያዙ ታካሚዎችን ሊከታተሉ ይችላሉ። »

World Health Summit in Berlin - Walter Lindner 20.10.2014

የጀርመን ፌደራል መንግሥት የኤቦላ ጉዳይ ተጠሪ ቫልተር ሊንድነር

የጀርመን የኤቦላ ጉዳይ ተጠሪ ሊንድነር ገና የጀርመን ተልኮዎች ስለሚፈፅሙት እንጂ በተግባር ስለፈፀሙት በዝርዝር አልተናገሩም። በጀርመን ላይ በየአቅጣጫው ትችቱ ተጠናክሯል። « አዎ! ይህንን እኛም ራሳችንን እንወቅሳለን። ሁላችንም መዘግየታችን እውነት ነው። ከድንበር የለሽ የሀኪሞች ድርጅት በቀር ሁሉም ስላረፈደ ሁላችንም ዕርስ በርስ ልንወቃቀስ እንችላለን። ግን ምን እናተርፋለን?»

ትችቱ ይህ ብቻ አይደለም። የጀርመንመከላከያሚኒስትርኦዙላፎንዴርላይን ከሰባት ሳምንታት በፊት የኤቦላ በሽታ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች መዝመት የሚሹ የጀርመን ጦር ባልደረባዎች በፍቃደኝነትመመዝገብእንደሚችሉ ሲያስታውቁ፤ ወታደር በፍቃደኝነት የሚዘምትበት ተግባር ግራ ያጋባቸውም በርካታ ነበሩ ።የበጎ ፍቃደኛው ቁጥርም በቂ ባለመሆኑ ሊንድነር ከ 2 ሳምንት ገደማ በፊት ህዝባቸውን ለማነሳሳት ጥሪ አድርገው ነበር። እንደ ጀርመን ያሉ ያደጉ እና ሀብታም ሀገራት ቶሎ ለተጎጂ ሀገራት በፍጥነት ስላልደረሱም መፍትሄ ያሹት የላይቤሪያን ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሌፍ ለጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የርዳታ ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ እስከመላክ መድረሳቸው ይታወሳል። ከዛም በከፊልም ቢሆን ለውጥ ታይቷል። በቅርቡ ከምዕራብ አፍሪቃ የተመለሱት ሊንድነር ፤« የላይቤሪያዋን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ከሶስቱም ፕሬዚዳንቶች ጋር ተነጋግሬያለሁ። ሁሉም ጊዜያቸውን ወስደው « ብቻችንን አልተዋችሁንም» የሚል ምስጋናቸውን ለመግለፅ ፍቃደኞች ነበሩ።»

የኤቦላ ተህዋሲው ከተገኘ ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ በሽታው በአስከፊ መጠን እንደዚህ ሲሰራጭ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። በላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን እና ጊኒ በኤቦላ ተሕዋሲ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ 13,300 በላይ ሆኗል። በእነዚህ አካባቢዎች ያለው ሌላው ህክምናም በአግባቡ ስለማይከናወን፤ እንደ ወባ በመሣሰሉ ሌሎች በሽታዎች የሚጠቃው ሰውም ቁጥር ከፍ ማለቱን ነው በስፍራው የሚገኙ የርዳታ ድርጅቶች የሚያሳስቡት። የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኤቦላ ስርጭት ከቁጥጥር ውጪ በመሆኑ አስጊ ሁኔታ ላይ መኮኑን የገለፀው ገና ባለፈው ዓመት ነሀሴ ወር ነበር ። መስከረም 21, 2007 ዓምም የጀርመን ሚኒስቴሮች እና መስሪያ ቤቶችን የኤቦላ ትብብር እንዲያደራጁ ባለስልጣን ሊንድነር የጀርመን ልዩ ልኡክ ሆነው ተሾሙ ።

በአጠቃላይ እስካሁን ጀርመን ኤቦላን ለማሸነፍ 1 ሚሊዮን የሚያወጣ ርዳታ እንደምትለግስ አስታውቃለች። ልገሳውም በቀጥታ ለተጠቁት ሀገራት እና ለዓለም የጤና ድርጅት እንደሚውል ተገልጿል። ይሁንና የጀርመን የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይሁኑ የግል ረጂዎች የጀርመን መንግሥትን ርዳታ አጥጋቢ አይደለም ባይ ናቸው። የጀርመን የአረንጓዴ ፖርቲ የህዝን ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ኮርዱላ ሹልስ አሸ፤ ። ርዳታው እጅግ ዘግይቶ እና ያለ ምንም ስልት እየተካሄደው ነው ይላሉ « በጀርመን መንግሥት በኩል ለተጎጂ ሀገራት የተወሰዱ ርምጃዎችን ስንመለከት ፤ እስካሁን አንድም ህመምተኛ የታከመበት ሁኔታ እንደሌለ ነው የምንገነዘበው።»

Infografik humanitäre Hilfe Ebola

ለምዕራብ አፍሪቃ ድጋፍ የሰጡ ሀገራት እና ተቋማት

ሹልስ አሸ ፤ የሊንድነር የጀርመን የኤቦላ ጉዳይ ተጠሪ ሆኖ መመረጥን ባይቃወቁም እስካሁን ድረስ የጀርመን ርዳታ ማቀናበሩን በተመለከተ ምንም የተደረገ ለውጥ የለም ይላሉ። ተመሳሳይ ወቀሳ የሚያቀርቡት አነ ዩንግ ናቸው። ዩንግ ለዓለም አቀፉ የርዳታ ድርጅት ሜዲኮ የኤቦላ ርዳታ ተጠሪ ናቸው። ለዶይቸ ቬለ ተከታዩን ገልፀዋል።«የሚያሳዝነው የጀርመን መንግሥት እስካሁን የሰጠው ርዳታ አጥጋቢ አለመሆኑ ነው። ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ጋ ሲነፃጸር ይኼው ወረርሽኝ ፈጣን ርምጃ ይጠይቃል።በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ኃላፊነቱ ማን ጋ ነው የሚለው ጥያቄ በርካታ ክርክር አስነስቷል። ይህ አሳዛኝ ክስተት ሆኖ አግኝተንዋል።»ይላሉ ዩንግ። ወቀሳውን በጀርመን መንግሥት ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የአውሮፓ ሀገራት ላይ እየሰነዘሩ።

ዩንግ ሴራሊዮን የሚገኙ ባልደረባዎቻቸው እንደገለፁላቸው ፤ በአንድ በኩል የዓለም አቀፉን ድጋፍ እጅግ ያመሰግናሉ በሌላ በኩል ይህንን በሽታ ለማሸነፍ ትንሽ የተባለው መሣሪያ እንኳን እንደጎደላቸው ይናገራሉ። « በዚህም የተነሳ የተለያየ አስተያየት ነው የሚሰጡት። « ኔትዎርክ ሙቭመንት ፎር ጀስቲስ ኤንድ ዲቨሎፕመንት» የተባለው አጋራችን ባልደረቦች በሽታው ከተስፋፉባቸው ሶስት ሀገራት መካከል በሁለቱ ተሳትፈዋል። በአንድ በኩል ርዳታው በተሻለ መንገድ እንዲደርስ የተቻለው ነገር ሁሉ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ። እንደ ሜዲኮ ያለ የርዳታ ድርጅት የርዳታውን መጠን ከፍ ማድረግ በመቻሉም ደስተኞች ናቸው። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ሁሉ ነገር በዝግመት እንደሚከናወን፤ ይህ ዝግመት ደግሞ በየዕለቱ የሰዎችን ህይወት እያጠፋ መሆኑን ይናገራሉ። »

Symbolbild Ebola Schutzanzüge Ärzte

ጀርመን አሁን ድረስ በጎ ፍቃደኞችን እያፈላለገች ትገኛለች።

የአረንጓዴ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ሹልስ አሸ የጀርመንን ርዳታ በተመለከተ ከሁሉም ትልቁ ችግር ነው ብለው የሚጠሩት ጀርመን በጎ ፍቃደኞችን የምታሰባስብበትን መንገድ ነው። ሊንድነር ከባድ የሆኑ ሁኔታዎች በሚስተዋልበት የኤቦላ አካባቢዎች ከጀርመን የሚጓዙትን « ሀቀኛ ጀግና» ቢሏቸውም ጀርመን በምታቆመው ማዕከል ስንት በጎ ፍቃደኞች ከሁለት ሳምንታት በኋላ እንደሚያገለግሉ አጠያያቂ ነው። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት የጀርመን ጦርም ይሁን የጀርመን ቀይ መስቀል በቂ በጎ ፍቃደኞችን አላገኘም። ለዚህም ሹልስ አሸ እንደምክንያት የሚያዩት፤ግልፅ የሆነ የአሰራር መመሪያ አለመኖሩን ነው፤ « እንደሚመስለኝ፤ ይህ ያልተሳካ ተግባር ነው። መሆን የነበረበት፣ በቦታው ምን ያህል ሰው እንደሚያስፈልጓቸው በግልፅ ማሳወቅ ነው። በምንከፍተው ጣቢያ የ 12 ወራት አገልግሎት እንድንሰጥ ይህን ያህል ሀኪሞች ፣ ይህን ያህል በሽተኛ ተንከባካቢዎች ያስፈልጉናል ይባላል። 2ኛው ነገር ደግሞ ወደዚህ አካባቢዎች ለሚሄዱት በጎ ፍቃደኞች ግልፅ ያልሆነው ጥያቄ የጤና ዋስትናቸው ጉዳይ ነው።»

ይህ ብቻ አይደለም። አንድ በጎ ፍቃደኛ ሀኪም ለአንድ አመት ስራውን ለቆ ወደ ምዕራብ አፍሪቃ ሲሄድ ከቀጣሪው ጋር የሚኖረውን ውል በተመለከተም እስካሁን ምላሽ አልተገኘም። ከሜዲኮ ኢንተርናሽናል የርዳታ ድርጅት ባልደረባ -አነ ዩንግ ከዚህም ሌላ ርዳታው በተገቢው መንገድ ሊካሄድ ስላልቻለበት ምክንያት ሰፊ ውይይት መካሄድ ያስፈልጋል ይላሉ። እንደ ዩንግ ጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ለዓለም የጤና ድርጅት መክፈል ያለባቸውን ገንዘብ በፍጥነት ባለመክፈላቸው ፤ ዓለም አቀፉ ድርጅት ስራውን በአግባቡ ማከናወን አልቻለም።

ማክስ ብሮቭስኪ/ ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች