ጀርመን ለኢራቅ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ልትሰጥ ነው | ዓለም | DW | 04.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ጀርመን ለኢራቅ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ልትሰጥ ነው

የጀርመን መንግሥት እራሱን እስላማዊ መንግሥት እያለ የሚጠራዉን አሸባሪ ቡድን ሰሜን ኢራቅ ውስጥ ለማጥቃት የሚደረገዉን ጥርት እያጠናከረ መሆኑ ተዘገበ። የጀርመኑ መከላከያ ሚኒስቴር ተልዕኮዉ በምን ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል እየተጤነ እንደሆነም ተገልፆአል።

IS በሚል ምህጻር የሚታወቀዉን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት ሊደረግ በታቀደዉ ተልኮ ከቀረቡት ጭብጥ ሀሳቦች መካከል፤ አንድ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በኢራቅዋ የኩርዶች መዲና በኤርቢል ላይ ማቋቋም የሚል ይገኝበታል። ከዚህ ሌላ በወታደራዊ ስልጠናዉ የኢራቅ ወታደሮችን ማሳተፍ እንዲሁም የጀርመን መኮንኖችን በመሪነት ማሰለፍ ሊሆን እንደሚችል፤ የጀርመንዋ መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ገልፀዋል። ዩኤስ አሜሪካ እራሱን እስላማዊ ቡድን ብሎ የሚጠራዉን አሸባሪ ቡድን ለማጥቃት የጀመረችዉን ዘመቻ በያዝነዉ ሳምንት ይበልጥ ማጠናከርዋም ተነግሮአል። የጀርመን ጦር ለበርካታ ቀናት ለኩርድ ፔሽሜርጋ ወታደሮች የጦር መሳርያ መስጠቱ እንዲሁም፤ ፈረንሳይ 32 ኩርዳዉያን ወታደሮችን የታንክ አጠቃቀም ማሠልጠንዋ ተዘግቦአል።
በተያያዘ ዜና፤ ከአንድ ዓመት በፊት ሶርያ ዉስጥ የታገተዉ እንግሊዛዊ በአሸባሪዎች መገደሉ ተሰማ።

እራሱን እስላማዊ መንግሥት እያለ የሚጠራዉ ቡድን ከዚህ ቀደም እንዳደረገዉ ሁሉ ከአንድ ዓመት በፊት አግቶ ያቆየዉን የ47 ዓመት እንግሊዛዊ አንገት ቀልቶ መግደሉን የሚያሳይ ቪዲዮ በብዙኃን መገናኛ አሰራጭቶአል። በሰሜናዊ ብሪታንያ ታክሲ ነጅ የነበረዉ ሟቹ እንግሊዛዊ አለን ሄኒግ፤ በሶርያ የህክምና ርዳታን በሚሰጥ ተሽከርካሪ ላይ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ተዘግቦአል። የዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ያደረገዉን ተግባር በፅኑዕ በማዉገዝ፤ ከብሪታንያ የደኅንነት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የሟቹን እንግሊዛዊና ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ አንገታቸዉ ተቀልቶ የተገደሉትን ሦስት ግለሰቦች ገዳይ ማንነት እናጣራለን ብለዋል።

ይህን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት የተጀመረዉም ጥቃት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በበኩላቸዉ፤ ይህ አስከፊ የግድያ ተግባር እስላማዊ መንግሥት ብሎ ራሱን የሚጠራዉ ቡድንን አረመኔነት የሚያሳይ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ