ጀርመንና የፌደራልዚም ተሐድሶ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 08.03.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመንና የፌደራልዚም ተሐድሶ

የጀርመን ፌዴራዊ መንግሥት እና የፌዴራዊ ክፍላተ ሀገር በሁለተኛው የፌዴራሊዝም ተሐድሶ ላይ ዛሬ እንደገና ድርድር ጀመሩ።

መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል

መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል

በዚሁ ጥያቄ ላይ እጅግ የተለያየ አቋም የያዙት የፌዴራዊው መንግሥትና የክፍላተ ሀገር መሪዎች በድርድሩ ትልቅ ውጤት እንደማይገኝ ሠላሣ ሁለት አባላት ያለው ኮሚስዮን ስብሰባውን ከመጀመሩ በፊት በግልጽ አስታውቀዋል። ምክንያቱም የተሐድሶው ለውጥ የገንዘብና የተፅዕኖ ጥያቄዎችን የሚመለከት ነውና። በድርድሩ ላይ ድሆቹ ክፍላተ ሀገር በሀብታሞቹ አቻዎቻቸው የምሥራቁ ክፍላተ ሀገርም በምዕራባውያኑ፡ የክርስትያን ዴሞክራቶቹ ኅብረትም በሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አንፃር፡ እንዲሁም፡ ፌዴራዊው መንግሥትና ክፍላተ ሀገር ለተጨማሪ ሥልጣን በመታገል ላይ ነው የሚገኙት።
የፌዴራልዚም ተሐድሶ በፌዴራዊው እና በክፍላተ ሀገር መንግሥታት መካከል ገንዘብ የማከፋፈሉ ሥልጣንን የሚመለከት በመሆኑ ይህንን ሥልጣን በውዴታ መተው የሚፈልግ መኖሩን ያጠያየቁት የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ የምክር ቤት አንጃ ሊቀ መንበር ፔተር ሽትሩክ ድርድሩ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀው ገልፀዋል። እርግጥ፡ ብዙው የጀርመናውያኑ የፌዴራሊዝም አሠራር ትክክለኛ ነው፤ ይሁንና፡ በቢሮክራሲያዊው ውጣ ውረድ የተነሳ ውስብስብና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሆኖዋል። በዚሁ አሠራር መሠረት፡ ፌዴራዊው መንግሥት ብዙዎቹን የሀገሪቱን ሕጎች ያወጣል። ነገር ግን ሕጎጩን በተግባር የመተርጎሙ፡ ለዚሁ የሚያስፈልገውን፡ ለምሳሌ ለማኅበራዊው ኑሮ ወይም ለቤት ክራይ ድጎማ፡ ወይም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጠውን የብድር ወጪ የማዘጋጀቱ ኃላፊነት የየክፍላተ ሀገሩን አስተዳደር ይመለከታል። ክፍላተ ሀገሩ ስለሚወጣም ሆነ ስለሚገባ ገንዘብ መወሰን አይችሉም። ይህ ገሀድ ሲታሰብ ታድያ አንዳንድ ክፍላተ ሀገር እና አንዳንድ የከተሞች አስተዳደሮች ክሳራ ላይ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም። ከአሥራ ስድስቱ የጀርመን ፌዴራዊ ክፍላተ ሀገር መካከል አሥራ አንዱ ወጪያቸውን ለመሸፈን ብድር ወስደዋል። በጀታቸው ባንድ በኩል ኢ ሕገመንግሥታዊ፡ በሌላ ወገን ይህ የተሸከሙት የዕዳ ጫና ደግሞ፡ ጀርመን የአውሮጳ ኅብረት ያስቀመጠውን የዕዳ ጣራ መጠን ለብዙ ዓመታት ማክበር ላልቻለችበት ሁኔታ ምክንያት ሆኖዋል።
የክፍላተ ሀገሩን ፊናንስ ሁኔታ ለማስተካከል የሚደረገው ጥረትም ችግር እንደደቀነ ይገኛል። ሀብታሞቹ ክፍላተ ሀገርና ፌዴራዊው መንግሥት ድሆቹን ክፍላተ ሀገር መርዳት ይጠበቅባቸዋል። እዚህም ላይ ነው ልዩነቱ የተፈጠረው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ ርስበርስ የሚታገሉት፡ ድሆቹ ክፍላተ ሀገርም በሀብታሞቹ አንፃር ይታገላሉ። ክርክሩ ከሽያጭ ቀረጥ፡ ከገቢ ግብር፡ ወዘተ፣ የሚገኘውን በብዙ ሚልያርድ የሚቆጠር ገንዘብ ክፍፍልን ይመለከታል። የገንዘብ ሚንስቴሮች እንኳንስ አንድ ሀገር አቀፍ የፊናንስ አስተዳደር ደምብ ይቅርና፡ የተቋማትንና የሚልዮኔሮችን ገቢ በትክክል መቆጣጠር የሚያስችላቸው አንድ የኮምፒውተር ፕሮግራም እንኳን የላቸውም። ብዙው የቀረጥ ገቢ ወደ ፌዴራዊው መንግሥት ካዝና ስለሚገባ ወይም ለክፍላተ ሀገር በጀት ማስተካካያ ስለሚውል ሀብታሞቹ ክፍላተ ሀገር ቀረጥ አሳዶ የመሰብሰብ ፍላጎት የላቸውም። የፌዴራዊውን መንግሥትና የክፍላተ ሀገር ሥልጣን ክፍፍልን በተመለከተ ፌዴራዊው መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ በመጓጓዧው ዘርፍ አንድ ሀገር አቀፍ የቀረጥ ፖሊሲ ለማውጣት ስላቀደ፡ ክፍላተ ሀገሩ የግል ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ቀረጥ እንዲቀር ሀሳብ አቅርበዋል። ከቤንዚንና የጭነት ተሽከርካሪዎች ለመንገድ የሚከፍሉት ቀረጥም በጠቅላላ የሚገባው ፌዴራዊው መንግሥት ካዝና ነው። ከዚህም በመነሳት የሀገሪቱን የፊናንስ አውታር ለማስተካከል ጊዜው አሁን አመቺ መሆኑ ተገልፆዋል። ምክንያቱም የሀገሪቱ ፌዴራዊ መንግሥት በትልቆቹ ፓርቲዎች ጥምር አስተዳደር ሥር ነው የሚገኘውና። የሀገሪቱ ፊናንስ አውታው ማስተካከሉ ተግባር ቀጣዩ የሀገሪቱ ፌዴራዊ ምክር ቤታዊ ምርጫ እአአ በ 2009 ዓም ከመደረጉና የውልታን ለውጥ ከመፈጠሩ በፊት ቢከናወን ይመረጣል።