ጀርመንና የጥሬ ዕቃ ፍጆቷ | ኤኮኖሚ | DW | 05.09.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ጀርመንና የጥሬ ዕቃ ፍጆቷ

ጀርመን በዓለም ላይ ጥሬ ዕቃዎችን በሰፊው ከሚፈጁት ቀደምት ሃገራት መካከል አንዷ ናት። ፍጆቱ በያንዳንዱ የአገሪቱ ዜጋ በነፍስ-ወከፍ ሲሰላ በዓመት አንድ ሺህ ቶን ገደማ ይጠጋል።

ጀርመን በዓለም ላይ ጥሬ ዕቃዎችን በሰፊው ከሚፈጁት ቀደምት ሃገራት መካከል አንዷ ናት። ፍጆቱ በያንዳንዱ የአገሪቱ ዜጋ በነፍስ-ወከፍ ሲሰላ በዓመት አንድ ሺህ ቶን ገደማ ይጠጋል። በጀርመን የማዕድን ከሰል፣ አሸዋና የመሳሰለው በበቂ መጠን የሚገኝ ቢሆንም አገሪቱ በሌላ በኩል እጅግ ጠቃሚ መዳብን፣ ኮባልትን፣ ፕላቲንን፤ በተለይም ለከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚፈለጉ ብርቅዬ ሚነራል ጥሬ ዕቃዎችን በተመለከተ በሌሎች ሃገራት ላይ ጥገኛ ናት።

በጀርመን ጉዳዩ በሚመለከተው ተቋም መረጃ መሠረት አገሪቱ በ 2010 ዓመተ-ምሕረት ከውጭ ገዝታ ያስገባችው ጥሬ ዕቃ ዋጋ ከ 109 ሚሊያርድ ኤውሮ በላይ ያወጣ ነበር። በዓለምአቀፍ ደረጃ ያለው የፍጆት ፍላጎት ሲያድግ ሂደቱ የመጨመር መሆኑም ጨርሶ የማያጠያይቅ ነው። ሁኔታው በተለይ ከበድ ብሎ የሚገኘው ደግሞ የወደፊቱ ነዳጅ ዘይት የሚል ቅጽል ስያሜ እየተሰጠው በሄደው ብርቅዬ ሚነራሎች ዘርፍ ነው።

እነዚህ የኤሌክትሮኒክና የማግኔትነት ባሕርይ ያላቸው 17 ሚነራሎች በሶላር የጸሃይ ሃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂ፣ ለሞባይሎ ስልኮችና ጨረርታማ ማተሚያዎች፣ ለኮምፒዩተርና ለአውቶሞቢል ግንቢያም እጅግ የሚፈለጉ ናቸው። በዓለም ዙሪያ እስካሁን ከሚወጣው የነዚሁ ሚነራሎች ክምችት 95 በመቶው የሚገኘው ቻይና ውስጥ ነው። ቻይና ደግሞ የዚሁኑ ጥሬ ሃብት የውጭ ንግድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰፊው በመገደብ የተጽዕኖ መሣሪያ አድርጋ መጠቀሟ አልቀረም።

ይህም የሚነራሎቹን ዋጋ ከመጠን በላይ ከፍ ሲያደርግ ለጀርመን ኢንዱስትሪዎችም ፈታኝ ሆኖ ነው የሚገኘው። ስለዚህም ጀርመን የቴክኖሊጂ ዕውቀትን በጥሬ ዕቃ በመቀየር ችግሩን ለመቋቋም በመጣር ላይ ትገናለች። በዚሁ መሠረትም የመጀመሪያው የጥሬ ሃብት ሽርክና ስምምነት ባለፈው ጥቅምት ወር ከሞንጎሊያ ጋር መፈረሙ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ጀርመን ከካዛክስታን ጋር ተመሳሳይ ውል አድርጋለች። ግንኙነቱን ለማጠንከር ያለው የሁለት ወገን ፍላጎትም እጅግ ከፍተኛ ነው።

የቀድሞይቱ ሶቪየት ሬፑብሊክ 16 ሚሊዮን ነዋሪዎች ብቻ ቢኖሯትም በስፋቷ ግን ጀርመንን በስምንት ዕጅ የምታጥፍ ናት። የአገሪቱ ኤኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው በተለይም በነዳጅ ዘይት ሃብት ሲሆን ካዛክስታን ከሩሢያና ከብሪታኒያ ቀጥላ ለጀርመን ሶሥተኛዋ ታላቋ ዘይት አቅራቢ ናት። እርግጥ የካዛክስታን ሃብት በነዳጅ ዘይት ብቻ የተወሰነ አይደለም። አገሪቱ ጋዝ፣ ዩራኒየም፣ ብረታ ብረት፣ እርሣስ፣ ዚንክ፣ ብር፣ ወርቅና ብርቅዬው ሚነራሎችም በሰፊው ነው ያሏት።

የካዛክስታን መንግሥት ደግሞ ከዚህ ሁሉ የሚገኘውን ገቢ በመጠቀም አገሪቱን በኢንዱስትሪ ለማበልጸግ ተነሳስቷል። በቅርቡ በርሊን ላይ የተፈረመው የሁለቱ ሃገራት የጥሬ ሃብት ሽርክና ውል በሶሥት ሚሊያርድ ኤውሮ የሚገመት ሲሆን በካዛክስታን የካፒታል ድርሻ የያዙት የጀርመን ኩባንያዎች ከአሁኑ 1200 ገደማ ይጠጋሉ። የሁለቱ መንግሥታት የንግድ ልውውጥም ባለፈው ዓመት ሃያ በመቶ ሲጨምር 6,3 ሚሊያርድ እውሮ ደርሶ ነበር።

የጀርመን መንግሥት የጥሬ ሃብት ፍላጎቱን ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት በተለይም በብርቅዬዎቹ ሚነራሎች ረገድ ከካዛክስታንና ከሞንጎሊያ ጋር ሽርክናውን ሲያጠናክር ጉዳዩ ባለፈው ሣምንት የቻንስለር አንጌላ ሜርክል የቻይና ጉብኝትም በተለይ ከኢንዱስትሪ ተወካዮች አንጻር ማነጋገሩ አልቀረም። ቻይና ይህ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ኢንዱስትሪዎች አጥብቀው የሚፈልጉት ምርት ድርሻዋ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሲሆን ለራሷ ልዕልና ስትል የውጭ ንግዱን መገደቧ በግልጽ የሚታይ ነው። ይሁን እንጂ የሁለቱ ሃገራት ትብብር ጥብቅ መሠረት ያለው መሆኑን ነው ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በፊናቸው የተናገሩት።

«ትብብራችን በሰፊ መሠረት ላይ የቆመ ነው። ከሣይንስ እስከ ኤኮኖሚ ትብብር፣ ከሕጋዊ ስርዓት ውይይት በእርሻ ልማት ላይ እስከሚያተኩሩ ጥያቄዎች በብዙ ዘርፎች ትብብራችንን አጠናክረናል። አንዱ ትልቁ ጉዳይም እርግጥ ከአካባቢ አየር ጥበቃና ከታዳሽ ኤነርጂ አመራረትጋር የተያያዘው የተፈጥሮ ጥበቃ ነው»

የኤኮኖሚው ትብብር እርግጥ የሚነራሎቹ ጉዳይ እንደሚያሳየው ሁሌም ቀላል አይደለም። ምናልባት በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በምሥራቅ አውሮፓ አዳዲስ ምንጮች እስከሚከፈቱ ድረስ አራትና አምሥት ዓመት ጊዜ እንደሚያልፍ ይታመናል። ስለዚህም የጀርመን ፌደራል ኢንዱስትሪ ማሕበር ገደቡ በአማካይ ጊዜ ከባድ ችግር እንደሚፈጥር በማሳሰብ ንግዱ በፍጥነት ነጻ እንዲለቀቅ ነው የሚጠይቀው።

በሌላ አነጋገር ቻይና በምርቱ ረገድ ፖሊሲዋን እንድታለዝብ ይፈልጋል። እርግጥ ጀርመንና ቻይና የጋራ ኮሚሢዮን ፈጥረው ችግሩን ለመፍታት እንደሚጥሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል። የዌን ቀና መሆን እርግጥ ያለ ምክንያት አይደለም። ለምን ቢባል በዓለም ላይ ዋነኛዋ የቻይና የንግድ ሸሪክ አውሮፓ ናት። ጀርመን ደግሞ በአውሮፓ ዋነኛዋ የቻይና የንግድ አበር መሆኗ ይታወቃል።

በአንጻሩም ቻይና ለጀርመን አምሥተኛዋ ታላቅ የንግድ ሸሪክ ናት። የጀርመን የኢንዱስትሪ መኪናዎችና የአውቶሞቢል ኩባንያዎች በቻይና የሚያካሂዱት ንግድ ማበብ በቀውስ በተወጠሩት የአውሮፓ ሃገራት የተፈጠረውን ጉድለት በከፊልም ቢሆን ሊሸፍን በቅቷል። ለጀርመናዊው የቻይና ተመራማሪ ለዜባስቲያን ሃይልማን ኤኮኖሚው በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ ትልቅ ትርጉም ነው ያለው።

«ሁለቱ ሃገራት በወቅቱ ፍላጎታቸውን እርስበርስ ያጣጣሙ ናቸው። ይህም ማለት ጀርመን ቻይናን ሊያስፈልጓት የሚችሉ ነገሮችን ታቀርባለች። ቻይናም ለጀርመን እንደዚሁ! ከዚህ በተጨማሪ በኢንዱስትሪው ዘርፍ አንድ ዓይነት የሥራ ክፍፍል ተፈጥሯል። እናም ጀርመን የከፍተኛ ምርቶችን ድርሻ፤ ማለትም ከፍተኛ ቴክኖሎጂና ዋጋን የሚጠይቁ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ድርሻ ስትይዝ ቻይና ደግሞ በአብዛኛው ራመድ ላሉትና አዳጊ ለሆኑት ሃገራት በሚቀርበው መካከለኛ ዋጋ ያለው ምርት ላይ ታተኩራለች። በዚህ ነው እንግዲህ ፉክክሩ ለዘብ እንዲል የሚደረገው። ግን ይህ በርከት ላሉ ዓመታት የሚቀጥል አይሆንም»

በዓለም ላይ በብዛት በማይገኙት በብቅዬዎቹ ሚነራሎች ላይ መለስ ብለን እናተኩርና ያለነዚህ ነገሮች ታዳሽ ኤነርጂ ሊኖር አይችልም። ለምሳሌ አንድ ዘመናዊ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ለማነጽ እንደ ቴክኖሎጂው ዓይነት ከ 300 ኪሎ እስከ አንድ ቶን ሚነራል ያስፈልጋል። በቻይና ይዞታ ስር የሚገኘው እርግጥ በዓለምአቀፍ ደረጃ አለ ተብሎ ከሚገመተው መጠን 30 በመቶው ብቻ ነው።

ሆኖም ግን ቻይና ከዘጠና በመቶ የሚበልጠው አብዛኛው ብርቅዬ ሚነራሎች ዓመታዊ ምርት ባለቤት ሆና ትገናለች። በውቁቱ እርግጥ ገና የምርቱ እጥረት እንደሌለና ዋጋው እንዲያውም 70 በመቶ መውረዱን ነው የጀርመን ኢንዱስትሪ ፌደራል ማሕበር የጥሬ ዕቃ ጉዳይ ኮሚሢዮን ሊቀ-መንበር ኡልሪሽ ግሪሎ የሚናገሩት። በሌላ በኩል በቤይጂንግ መንግሥት የተጣለው የውጭ ንግድ ገደብ በዓለም ንግድ ድርጅት ዘንድ ክስን አሰነስቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ሆኖም ቻይና ሚነራሉን በርከት አድርጋ እንድትሸጥ ለማስገደድ ባለፈው መጋቢት ወር በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ሕብረትና በጃፓን የቀረበውን ክስ በተፈጥሮ ጥበቃና ዘላቂ ልማት አስባብ መቃወሟ አይዘነጋም። ቻይና እንግዲህ ምርቷን ሃያ በመቶ በመቀነስ፤ እንዲሁም በአምራቾችና በተገልጋይ ኢንዱስትሪዎች መካከል ዋጋ ተማኝ አካል በመሰየም ለአገር ኤኮኖሚዋ ዕድገት በምትፈልገው ስልታዊ ሚነራል ላይ መሉ ቁጥጥር አስፍናለች።

ቤይጂንግ ሚነራሎቹን ለመቀጣጠር ባለፈው ሰንበት ያቋቋመችው የኢንዱስትሪ ማሕበር ዓላማ ዘርፉን ጤናማ አድርጎ ማሳደግና የአካባቢ ተፈጥሮን መጠበቅ ነው የቻይና የኢንዱስትሪና የማስታወቂያ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው። 17ቱ ንጥረ-ነገሮች የተለየ ሙቀትን የመቋቋም ብቃት ሲኖራቸው ከኮምፒዩተር እስከ ሞባይል፤ ከባትሪዎች እስከ ጠፍጣፋ ቴሌቪዥን፤ ከሮኬቶች እስከ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የማይፈለጉበት ቦታ የለም።

የኢንዱስትሪው ማሕበር መሪ ጋን ዮንግ እንደሚሉት የማሕበሩ መቋቋም ዓላማ ጥሩ የዋጋ ፖሊሲን ማራመድ ነው። ይሁን እንጂ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት መንግሥታት በሚነራሎቹ ይዞታ ረገድ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተወሰደ ዕርምጃ ነው ባዮች ናቸው። በጥቅሎ የጀርመንና የቻይና ሁለተኛ የውይይት መድረክ ባለፈው ሣምንት ግልጽነት በሰፈነበት ሁኔታ አልፏል።

መጨው ተከታዩ መድረክ ምን ውጤት እንደሚያስከትል መገመቱ ወይም ጭብጥ ውጤት መጠበቁ ግን በወቅቱ ለመናገር የሚያዳግት ነው። ምክንያቱም ገዢው የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በመጨው በልግ 18ኛ የፓርቲ ስብሰባ የአመራር ለውጥ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑ ነው። የበርሊኑ የፖለቲካ ተመራማሪ ኤበርሃርድ ዛንድሽናይደር እንደሚሉት አስደናቂ ውጤት መጠበቅ በፍጹም አይቻልም።

«በመጪው የመድረክ ዙር አንድ አስደናቂ ውጤት ለመጠበቅ አይቻልም። ቤይጂንግ በወቅቱ በተቀዳሚ የሥልጣን ተተኪውን በመሰየሙ ጉዳይ ተጠምዳ ነው የምትገኘው። ይህ ከሆነ በኋላ አዲስ ዕርምጃ እንደምትወስድ ተሥፋ መጣል ይቻላል»

እንዳለፉት ዓመታት ከሆነ ወሣኝ ዕርምጃ መጠበቁ ጥቂትም ቢሆን መክበዱ አይቀርም። ለዚህም ነው ብዙዎች አገሮች አማራጭ ገበያ መሻት ይዘው የሚገኙት። ጀርመንም ከሞንጎሊያና ከካዛክስታን ጋር የጥሬ ዕቃ ውል መፈራረሟ የዚህ ውጤት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። እንደ ጀርመኑ ኢንዱስትሪ ፌደራል ማሕበር ባልደረባ እንደ ኡልሪሽ ግሪሎ ከሆነ በመሠረቱ የጋራ መፍትሄ መፈለጉ ቻይናንም የሚበጅ በሆነ!

ግሪሎ እንደሚሉት ሕዝባዊት ቻይና ለምሳሌ ዛሬ ጥሬ ብረት ከውጭ ታስገባለች። ታዲያ የራስን ዘግቶ የውጩን መግዛት ከሽርክና ባሕርይ ጋር ግንኙነት የሌለው ነገር ነው። ችግሩን በውይይት ለመፍታት ካልተቻለ በዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ አዲስ ክስ የሚያሰጋ ሲሆን በዚህ ደግሞ ተጠቃሚ ላለመኖሩ አንድና ሁለት የለውም።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 05.09.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/163VL

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 05.09.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/163VL