ጀርመንና የግብፅ ፍርድ ቤት ዉሳኔ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመንና የግብፅ ፍርድ ቤት ዉሳኔ

የግብፅ ፍርድ ቤት የጀርመኑ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ኮንራድ አደናወር ሁለት ጀርመናዉያን ሠራተኞች ላይ የእስራት ቅጣት መበየኑ የጀርመን ፖለቲከኞች ሲተቹት ተንታኞች ፖለቲካዊ መልዕክት እንዳለዉ ያመለከቱ ነዉ።

ፍርድ ቤቱ ተቀጣሪዎቹ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በእስራት እንዲቀጡ ሲወስን በሌሎች የዉጭ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች ላይም እንዲሁ የቅጣት ብይን ማሳለፉ ከየሃገራቱ ተቃዉሞ ገጥሞታል። መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በዉሳኔዉ እጅግ ማዘናቸዉንም የመንግስት ቃል አቀባይ ሽቴፈን ዛይበርት ረቡዕ ዕለት ሲገልፁ ሁኔታዉ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንደሚጎዳም ጠቁመዋል። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ በተቋሙ ሁለት ሠራተኞች ላይ የእስራት ቅጣት እንዲሁም ካይሮ የሚገኘዉ የጀርመኑ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኮንራድ አደናወር ተቋም እንዲዘጋ የመወሰኑ ዜና እንዳሳዘናቸዉና እንዳስደነገጣቸዉ ነዉ የገለፁት።

Hans-Gert Pöttering Vorsitzender der Konrad-Adenauer-Stiftung

ሃንስ ገር ፖተሪንግ

የኮነራድ አደናወር ተቋም ዋና ኃላፊ ሃንስ ገር ፖተሪንግ በባልደረቦቻቸዉ ላይ የተወሰነዉ ቅጣት እንዳስገረማቸዉ በመግለፅ ርምጃዉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን መብት የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን የግብፅን የሕግ የበላይነት እንደሚጻረር አመልክተዋል።

«ትክክለኛ ሂደት አልነበረም። ከመነሻዉ አካሄዱን አስተዉለናል፤ በሠራተኞቻችንና ካይሮ በሚገኘዉ ጽህፈት ቤታችን ላይ የተሰነዘረዉ ክስም ትርጉም የሌለዉ ነገር ነዉ። ከመንግስት ጋ ተዋዉለን ላለፉት ሠላሳ ዓመታት እዚያ ያከናወነዉን መልካም ሥራ ፍርድ ቤቱ ምንም ስፍራ አልሰጠዉም። ካይሮ ላይ የገጠመን ነገር በጣም አስደንግጦናል።»

ፍርድ ቤቱ በካይሮ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አንድሪያስ ያኮንስ አምስት ዓመት፤ ረዳታቸዉ ደግሞ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ በሌሉበት ወስኗል። ፖተሪንግ ከመንግስታቸዉና ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍና ትብብራቸዉን ማሳየታቸዉ መልካም መሆኑን ገልፀዉ ያ ግን በተለይ ለሁለተኛዋ ተከሳሽ የሚረዳዉ ነገር የለም ይላሉ፤

«መንግስትን በጣም አመሰግናለሁ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ አፋጣኝ ምላሽና ተቃዉሟቸዉን አሰምተዋል። ከመራሂተ መንግስቷ ጽህፈት ቤት ጋም እየተገናኘን ነዉ። ሌሎች ድርጅቶችም አጋርነታቸዉን አሳይተዉናል። ታላቅ ተቀባይነትና ትብብር እያገኘን ነዉ። ሆኖም ይህ ሁሉ ድጋፍ ለጊዜዉ ባልደረባችንን አልረዳልንም፣ እሷ በርሊን ስትሆን ልጆቿ እና ግብፃዊዉ ባለቤቷ ካይሮ ናቸዉ። እንዲህ ባለዉ ሁኔታ በእርግጥም ወደካይሮ አትመለስም።»

Bundestag Reichstagsgebäude

የጀርመን ምክር ቤት/ቡንደስታኽ/

ፖተሪንግ ሁለቱ ጀርመናዉያን የድርጅቱ ሠራተኞች ቅጣት ሲበየንባቸዉ እዚህ በመሆናቸዉ ከእስር ቢያመልጡም ብይኑ ግን ትርጉም የለሽ እና ተቀባይነት እንደሌለዉ ገልጸዋል።በጀርመን ምክር ቤት የዉጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል የሆኑት የክርስቲያን ማኅበራዊ ኅብረት CSU ፖለቲከኛ ፔተር ጋዉቫይለር በበኩላቸዉ ይህ የፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲነሳ ጀርመን መጠየቅ ይኖርባታል ይላሉ።

«ይህ ብይን እንዲነሳ መጠየቅ ይኖርብናል፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ከዚህች አገር ጋ ምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሊኖር አይገባም።»

ጋዉቫይለር እንዲህ ያለዉ ዉሳኔ በሕዝቡና ስልጣን ላይ ባለዉ አካል ስም እንደሚከናወን በማመልከት፤ አመራሩ አካል ከጀርመን ጋ መልካም ግንኙነት እንዲኖረዉ እንደማይፈልግ ካሳየ በርሊን ልትወስድ ይገባታል ያሉትን ርምጃም አመላክተዋል።

«ለአመራሩ አካል በእንዲህ ያለ ሁኔታ ከእኛም ጋ ጤናማ ግንኙነት እንደማይኖር ግልፅ ማድረግ ይገባል። የተለመደዉ የልማት እርዳታ አይኖርም። ለእርዳታ እዚያ የሚገኙ ሰዎቻችን በእስራት ቅጣት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸዉ ይህን አንከፍልም።»

Kairo Prozess gegen NGOs Archivbild 2012 Richter Mohammed Shukri

ዉሳኔዉን ያሳለፈዉ የካይሮዉ ፍርድ ቤት

በጀርመን ማይንዝ የአረቡ ዓለም ጥናት ማዕከል ኃላፊ ጉንተር ማየር በበኩላቸዉ ፍርድ ቤቱ ከሙባረክ ዘመን አንስቶ የነበረ ሕግን ተግባራዊ ማድረጉን ነዉ የሚናገሩት። እሳቸዉ እንደሚሉት በወቅቱ ግብፅ ዉስጥ የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በይፋ መመዝገብ እንደሚኖርባቸዉ ተደንግጓል። በሙባረክ ጊዜ ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑበት ሁኔታ ያን ያህል ጥብቅ ባለመሆኑም ኮነራድ አደናወር ያንን ተግባራዊ አላደረገም ባይናቸዉ። እንዲያም ሆኖ ፍርድ ቤቱ የወሰደዉ ርምጃ ከሕግ ማስከበር ባለፈ ሌላ አንድምታ አለዉ ባይናቸዉ።

«ከዚህ ጀርባ ትኩረት የተደረገበት ጉዳይ በፖለቲካና በሰብዓዊ መብቶች ረገድ ከዉጭ የሚደረገን ትችት ለመቀነስ ነዉ። በዚም ላይ ያለ አንዳች ጥርጥር ይህን የተቃዉሞ ወገኑም የሚለዉ ነዉ፤ ግብፅ ዉስጥ የተጠናከረዉን ፀረ አሜሪካና ፀረ ምዕራብ አመለካከት ለሕዝቡ ለማጠናከር ነዉ።»

ማየር እንደሚሉትም ይህ ስሜትና ርምጃም ከአሜሪካን የመብት ተሟጋቾች ወገን ተመሳሳይ ተቃዉሞ አስከትሎ የገንዘብ ርዳታዉን እንደሚያሳጥር ግልፅ ነዉ። የፍርድ ቤቱ ዉሳኔም ስልጣን የጨበጠዉ ቡድን ትችት የሚሰነዝሩ ሲቪል ማኅበራዊ ድርጅቶችን የማዳከም ርምጃዉ አካል ነዉ። እንዲያም ሆኖ ኮነራድ አደናወር ተቋምን በሚመለከት የተላለፈዉ ዉሳኔ የመጨረሻ እንዳልሆነ ነዉ የተገለፀዉ። የመጨረሻዉ ፍርድ እስኪበየንም ፔተር ጋዉቫይለር ጀርመን በፖለቲካዉ ብቻ ሳይሆን በኤኮኖሚዉም ረገድ ቁጥብነት ማሳየት ይኖርባታል ሲሉ አሳስበዋል።

ከርሽተን ክኒፕ

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic