ጀርመንና የኤሌክትሪክ አውቶሞቢል፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 02.12.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ጀርመንና የኤሌክትሪክ አውቶሞቢል፣

ፕላኔታችን ከተቀጣባት የጥፋት አደጋ እንድታመልጥ፣ አየሩን የብሱንና ባህሩን ከብክለት ለመከላከልም ሆነ ለማጽዳት፤ በአጭሩ የተፈጥሮ አካባቢን ለመጠበቅ፣ ይበጃሉ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ፣ ዓለም አቀፍ ጠበብትና ውሳኔ ሰጪ መሪዎች በየጊዜው በጋራ ከመምከር አለመቦዘናቸውን እንሰማለን።

ጀርመንና የኤሌክትሪክ አውቶሞቢል፣

በ ላይፕሲኽ የባየር የሞተር ሥራ ድርጅት(BMW ) ያቋቋመውን አዲስ የኤልክትሪክ መኪና መሥሪያ ኢንዱስትሪ፤ መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሲጎበኙ፣

በጋራ መፍትኄ መሻቱ የሚበጅ ቢሆንም፣ በተናጠል እያንዳንዱ ሀገር የራሱን የቤት ሥራ ለማከናወን መነሳሳቱ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።

ባለፈው ሳምንት ዝግጅታችን፣ ንፁህ የሚጠጣ ውሃ ማግኘት ለተሣነው በዓለም ዙሪያ፣ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ለሚሆነው ህዝብ በተለይም ደግሞ ፣ በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም 300 ሚልዮን ለሚሆኑ ጎስቋሎች፣ ተስፋ አስጨባጭ ስለሆነው በቀላል ዘዴና ዋጋ የቆሸሸ ውሃ ስለሚያጣራው የደቡብ አፍሪቃ እስቴሌንቡሽ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም፣ የምርምር ውጤት ማውሳታችን ይታወስ ይሆናል።

የውሃ ማጣሪያው ፤ ለአንድ ብርጭቆ ሻይ የሚውል ንዑስ የሻይ ከረጢት በሚመስል ልዩ ንዑስ ከረጢት የሚታሸግ፤ የላመ ጥቁር ድንጋይ የተቀላቀለበት ማዕድናዊ ቅመም ሲሆን፣ ውሃውን ሲያጣራ፣ በዐይን የማይታዩ አደገኛ ተኀዋስያንን ቅመሙ ለይቶ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን በሽታ እንዳያስተላልፉ ቀስ-በቀስ ይገድላቸዋል።ደቡብ አፍሪቃውያኑ የሥነ ፍጥተትና ሥነ ቅመማ ጠበብት ውሃን የሚያጣራ ማዕድናዊ ቅመም ሲቀምሙ፣

በአውሮፓ ክፍለ ዓለም የቼክ ሪፓብሊክ ተመራማሪዎች፣ አየርን ከብክለት ሊያጸዱ ተናሳስተዋል።

ሳይንቲስቶችና ኩባንያዎች፣ ሳይንስ ድንበር ሳይገድበው፣ በዕለታዊ ኑሮ ላይ ለውጥ ሊያስገኝ እንደሚችል ፣ በአሁኑ ጊዜ የተረባረቡበት አስደማሚ የረቂቅ ሥነ ቴክኒክ የፈጠራ ውጤት እያሠመሠከረ መሆኑም በመነገር ላይ ነው። አንድ የቼክ ኢንዱስትሪ ኩባንያ፤ የቀመመው ልዩ የቤት ቀለም፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ፤ አየሩን፤ ከሲጋራ ሽታ የሚያፀዳ፣ በሽታ አስተላላፊ ተኀዋስያንን በደቂቃዎች ውስጥ የሚያጠፋ ሆኖ ተገኝቷል። የቼክ ሪፓብሊክ የሳይንስ ምሁራን ከፍተኛ ማኅበር ፣ ረቂቅ ሳይንስን ለህዝብ ጠቀሜታ ማዋል የሚቻልበትን ተጨባጭ የአሠራር ስልት ለማስተዋወቅ አዲስ የረቂቅ ሳይንስ የምርምር ማዕከል የተሰኘ ተቋም ገንብተዋል።

በሰሜናዊው የፕራግ መዳረሻ፤ በአንድ ኅንጻ፣ 6ኛ ፎቅ ላይ ፣ የሚገኘው የሄይሮቭስኪ የፊዚክስና ሥነ ቅመማ ተቋም፣ እጅግ በጣም ንዑስ ከሚሰኙ ቁሳቁሶች፣ አስደናቂ ነገሮች እየተሠሩ ነው። ከአንድ ወር ተኩል ገደማ በፊት የተቋቋመው የረቂቅ ሳይንስ ማዕከል ከፊሉን የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው ከአውሮፓው ኅብረት ነው። የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዪሪ ራቱስኪ ስለአንድ ወፈር ያለ የግድግዳ ቀለም ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል።

«ለምሳሌ ያህል፤ ስስ ጣውላ መሰል መስታውቶችን በጥቂቱ ቲታንያም ዳይኦክሳይድ የተሰኘው ጋዝ ያለበትን ቀለም እንቀባቸዋለን። ቲታንየም ዳይኦክሳይድ ከብርሃን ጋር ተቀላቅሎ ፈጣን የቅመማ ለውጥ እንዲከሠት የሚያደርግ ነው። በእንዲህ ሁኔታ ፣ ከብርሃን ጋር የተቀላቀለ ቀለም ፣ በአንድ ክፍልም ሆነ አዳራሽ ውስጥ የአየር ዝውውርን ለማስተካከል፣ አየሩን ከብክለት ለመከላከልም ሆነ ለማጽዳት ፣ በብርሃኑ አማካኝነትም በካዮቹን ነገሮች ለማጥፋት ይውላል። »

በ«ቲታንየንም ዳይኦክሳይድ» ዪሪ ራቱስኪ ብቻ አይደሉም የሚመራመሩትም ሆነ በሥራ ላይ የተሰማሩት።

2,(ድምፅ SFX)----------

«ዘመናዊ ቁሶች» በሚላቸው መሣሪያዎች የሚገለገለው የያን ፕሮሃስካ ኩባንያ፣ በፕራግ መዳረሻ ፍርስራሽ በሚበዛበት አካባቢ ነው የሚገኘው ። ፕሮሃስካና ራቱስኪ ትኩረታቸው በቲታንዬም ኦክሳይድ ላይ ቢሆንም አብረው አይደለም የሚሠሩት። የፕሮሃስካ ኩብንያ፤ ከብርሃን ጋር ሲገናኝ የለውጥ ሂደት የሚታይበትን የግድግዳ ቀለም ሥራ ላይ የሚያውል ሲሆን ቀለሙለምሳሌ ያህል በመኖሪያ ክፍል ውስጥ፣ ከተኀዋሲ አንስቶ እስከ ሲጋራ ጢስ የሚያስወግድ ነው። በአንድ 20 ካሬ ሜትር ገደማ በሚሆን መደበኛ የመኖሪያ ክፍል ብርሃን ሲያርፍበት ለውጥ የሚያሳየው ቀለም፤ በ 20 ደቂቃ ገደማ ነው፣ የሲጋራ ጢስን የተበከለ አየርንና መጥፎ ሽታ ጠረርጎ የሚያስወግደው።

4,« አዎ፣ 90 ከመቶ እንበል አየር የሚበክል ጢስና መጥፎ ሽታ ሁሉ በ 24 ሰዓት ውስጥ ፈጽሞ ይጠፋል፤ ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይህ ሊከናወን ይችላል ፤ ይበልጥ አስተማኝነቱን ለመግለጽ ነው 24 ሰዓት ያልኩት። »

በግድግዳ መቀቢያው ቀለም ውስጥ «የቲታንዬም ዳይኦክሳይድ» ኢምንት ጠብታዎች ከፀሐይ ከሚፈነጠቁ እጅግ አደገኛ ከሚባሉ የጨረር ዓይነቶች ወይም የልዩ መብራቶች ብርሃን ጋር ሲገናኙ ጢሱንም ሆነ ተኀዋስያኑን ያወድሟቸዋል። ከዚያም የሚቀረው ውሃና የተቃጠለ አየር ነው። ይኸው ቀሪ ንጥር ሊጠጣ እንደሚችልም ያን ፕሮሃስካ ይገልጻሉ። ብርሃን የባኅርይ ለውጥ እንዲያደርግ የሚያስገድደው የግድግዳ ቀለም፣ ከታወቀ ጊዜው ረዘም ቢልም፣ በየጊዜው ከመቶ ጊዜ ባላነሰ ሙከራ እንዲሻሻል ፣ ይበልጥ ጠንካራና አስተማማኝ እንዲሆን ተደርጓል።

«ዘመናዊ ቁስ፣» እያለ ራሱን የሚጠራው የቼክ ኩባንያ፤ ውጤቱን ወደ እስፓኝ፣ ደቡብ አፍሪቃና ኒው ዚላንድ መላክ ጀምሯል። ሌሎች አገሮችም ፈቃድ ለማግኘት በመሞከር ላይ ናቸው። ይኸው ኩባንያ የሚያከናውነው ተግባርና የሚያመርተው ቲታንየም ዳይኦክሳይድ፣እንዲሁም የ ረቂቅ ሥነ ቴክኒክ ማዕከል በፕራግ መቋቋም፣ አንዳንድ የቼክ መገናኛ ብዙኀን እንደሚያስተጋቡት ፣ አገሪቱ በአውሮፓ አንደኛዋ የረቂቅ ሥነ ቴክኒክ ማዕከል እንድትሆን ሳያበቃት አይቀርም።

የኤልክትሪክ አውቶሞቢል ዕጣ በጀርመን፤

በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፣ እ ጎ አ በ 1769 ዓ ም በውሃ እንፋሎት ኃይል የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ይሠራ እንጂ፤ በዓለም ዙሪያ ከ 125 ዓመታት ገደማ በፊት አንስቶ ፣ ሞተሩ በነዳጅ ዘይት ወይም ቤንዚን የሚንቀሳቀሰው መደበኛው ተሽከርካሪ የተፈለሰፈው በጀርመን ሀገር ማንሃይም በተባለችው ከተማ ኒኮላስ ኦቶ እንዲሁም በናፍጣ የሚሠራ ሞተር በፈለሰፉት ሌላው ጀርመናዊ ሩዶልፍ ዲዘል ነው። በሃድሮጂን ጋዝ የሚሽከረከር አውቶሞቢል ለመጀመሪያ ጊዜ እ ጎ አ በ 1938 የፈለሰፉትም ሌላው ጀርመናዊ ክርስቲያን ፍሪድሪኽ ሾዖንባይን ናቸው።

በአመዛኙ፤ የዘመናዊ አውቶሞቢል ፈልሳፊ የሚባሉት እ ጎ አ በ 1886 ዓ ም፣ የፈጠራ ውጤት የምሥክር ወረቀት ለማግኘት የበቁት ጀርመናዊው እንጂኔር ካርል ቤንዝ ናቸው። በ 20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ በኤልክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ቢሞከሩም እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ችላ ተብለው መቆየታቸው የሚታበል አይደለም። ይሁንና ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ተስማሚ ተሽከርካሪ በሚፈለግበት በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሽከረከሩ አውቶሞቢሎች ዐቢይ ግምት ተሰጥቶአቸዋል። በሥነ ቴክኒኩ ረገድ የሆነው ሆኖ ብዙ ይበል የሚሻሻሉ ነገሮች አሉ በመባሉ የጀርመን የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪዎች፣ ሳይንቲስቶችና ፖለቲከኞች በዚህ ረገድ ተስማምተው ሊገፉበት ሳይነሳሱ አልቀሩም። የባየር የሞተር ሥራ ድርጅት (BMW)፣ በላይፕትዚኽ ከተማ ፣ 400 ሚሊዮን ዩውሮ ገንዘብ የመደበ ሲሆን፣ እ ጎ አ ከ 2013 ዓ ም አንስቶ በኤልክትሪክ ለሚሽከረከሩ አውቶሞቢሎች የሚሆን የኤልክትሪክ ሞተሮችን እየሠራ ያቀርባል። ሜርሰድስ ቤንትዝ፣ አውዲና ቮልክስቫገንም ተመሳሳይ ውጥኖች አሏቸው። የተሽከርከሪ ተፈላጊ ክፍሎችን የሚያቀርቡት፤ «ቦሽ፣» BASF «ኢቮኒክ»፤ ወይምየተሽከርካሪዎች መብራት አቅራቢው ኢንዱስትሪ ኩባንያ «ሊቴክ፣» በ 3 ደረጃ ገንዘብ በማውጣት፣ የወደፊቱ የኤሌክትሪክ አውቶሞቢል አሠራር ፣ እንዲያምር -እንዲሠምር የሚመክር የጋራ የምክክር ኮሚቴ አቋቁመዋል። በዛ ያሉ የምርምር ተቋማትም ኃይላቸውን ለዚሁ ዓላማ በማስተባበር ላይ ናቸው። ውሎ አድሮ በቢሊዮን ዩውሮ የሚቆጠር ትርፍ የሚያስገኘውን ገበያ የጀርመን መንግሥት በጥሞና ከመከታተልም በጉጉት የሚጠበቅ አቅድ እንዳለው አስታውቋል። የጀርመን የኤኮኖሚ ሚንስትር ራይነር ብሩደርለ---

«በጋራ ተባብረን መሥራት አለብን። የገበያው መሪ መሆን እንሻለን። በዓለም ዙሪያ የኤሌክትሪክ አውቶሞቢል መሪ አቅራቢዎች መሆን እንፈልጋለን። ግባችን፣ እ ጎ አ እስከ 2020 በጀርመን አውራ ጎዳናዎች አንድ ሚሊዮን ያህል የኤልክትሪክ አውቶሞቢሎች እንዲሽከረከሩ ማብቃት ነው። ይህም የጀርመንን ኢንዱስትሪ ጠንካራ የውድድር ችሎታ የሚጠይቅ ነው።»

ከ 125 ዓመታት ገደማ በፊት በዓም ውስጥ ጀርመን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አውቶሞቢል መሥራቷን የጠቀሱት ብሩደርለ፣ አሁንም በሥነ ቴክኒክ የመሪነቱን ቦታ ይዘን እንቀጥላለን ማለት፣ ከባድ ነው፤ ከሥራው መናገሩ ይቀላል ብለዋል። ዩናይትድ እስቴትስ፤ ጃፓን ፣ ቻይና ኮሪያ እንዲሁም ፈረንሳይ ፣ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ የኤልክትሪክ አውቶሞቢል ለመሥራትና ለገበያ ለማቅረብ የተነሳሱ በመሆናቸው ውድድሩ እጅግ ከባድ መሆኑ እንዳማይቀርም ነው ጨምረው የገለጹት። የብሔራዊው የተንቀሳቀሽ ኤልክትሪክ ሞተር መድረክ የተሰኘው ድርጅት ሊቀመንበር ሄኒንግ ካገርማን

በዚህ ረገድ የሚጠበቀው ተግባር በአፋጣኝ ሊከናወን ይገባል ከማለታቸውም ሌላ፣

«በሥነ ቴክኒክ የመሪነቱን ሥፍራ የመያዙ ጉዳይ ክፍት ሆኖ ያለ ጥያቄ ነው። በአፋጣኝ ዒላማ አድረገን መነሣት አለብን። ይህን ካደረግን፣ በዚህ ወሳኝ የሥነ ቴክኒክ ሂደት በ 2020 ዓ ም የመሪነቱን ቦታ ልንይዝ እንችላለን። እዚህ ላይ ምርምርና መፈልሰፍ ባቻ አይደለም የሚፈለገው። የማምረቻው ሥነ ቴክኒክ ይዞታም ሊታሰብበት የሚገባ ነው። በባብዛት በማምረት ዋጋውን መቀነስ መቻል ይኖርብናልና! እናም ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ የመጨረሻው ግብ ይሆናል።»

ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ፣ የመሪነቱን ሥፍራ በመያዝ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው የሥነ ቴክኒክ ውጤት ማቅረብ ማለትም በኤልክትሪክ የሚሽከርከር አውቶሞቢል ለገበያ ማቅረብ የፈጠራ ችሎታው አላት። እንደገና በፋክስ መሳሪያ MP 3 Player በመሳሰለ መሣሪያ አቅርቦት ብቻ መርካት የለብንም ሲሉ የኤኮኖሚ ሚንስትሩ አስገንዝበዋል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ