ጀርመንና የአውሮጳ ህብረት የጋራ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.07.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመንና የአውሮጳ ህብረት የጋራ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ

ጀርመን በወቅቱ የአውሮጳ ህብረት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣንዋ አሳካለሁ ብላ ያቀደችው የህብረቱ የጋራ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ የፊታችን መስከረም ለህብረቱ አባል ሃገራት ሊቀርብ እንደሚችል የህብረቱ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ኢልቫ ጆአንሰን አስታውቀዋል።ምክር ሃሳቡን የህብረቱን አባል ሃገራት እንዲቀበሉ ማድረጉ ለጆአንሰን ፈታኝ መሆኑ አይቀሬ ነው። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:56

የአውሮጳ ህብረት የጋራ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ

 በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ከመኖሪያ ቀያቸው የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከመቼውም በላይ ከፍተኛ ነው።በተመድ ግምት የተሰዳጆች ቁጥር አሁን በአጠቃላይ ወደ 80 ሚሊዮን ይጠጋል።ይኽም ከዓለማችን ሕዝብ አንድ በመቶኛው ወይም ደግሞ ከጀርመን ሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ነው።የሰዎች እንቅስቃሴ በአብዛኛው በተገደበበት በአሁኑ የኮሮና ዘመን ሳይቀር በተለያዩ ምክንያቶች መኖሪያቸውን ለቀው የሚሰደዱት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።ከመካከላቸው በብዙ ስቃይና መከራ ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩት ይገኙበታል።አሊ ከትንሽትዋ ምዕራብ አፍሪቃዊት አገር ቶጎ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ፣ ሞሮኮ የተሰደደ በ30ዎቹ መጀመሪያ እድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነው።ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የለውም።በሞሮኮ ዋና ከተማ በራባት ከብዙ ስደተኞች ጋር በሚጋራት በአንዲት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ነው የሚኖረው።አሊ ዓለምን ያስጨነቀው ኮሮና ኑሮውን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎበታል።ችግሩ የከፋበት አሊ በሜዴትራንያን ባህር አድርጎ ወደ አውሮጳ መሻገር የቀረው የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን ይናገራል። 
«አንዳንድ ጊዜ ሙሉ ቀን የምንበላውም ሆነ የምንጠጣው አይኖረንም፤ ከውሃ በስተቀር።ቤት ክራይ የምከፍለው ገንዘብ የማገኝበት አነስተኛ ሥራም የለኝም።እዚህ ሰው ምን ዓይነት ተስፋ ይኖረዋል።እናም ብሞትም ባልሞትም በሜዴትራንያን ባሕር ወደ አውሮጳ ለመሄድ እያሰብኩ ነው።»

አሊ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ ሞሮኮ ያሉ ስደተኞች ማሳያ ነው።ሞሮኮ ሊቢያ እና ቱኒዝያን በመሳሰሉ የሰሜን አፍሪቃ ሃገራት የሚገኙ በርካታ ስደተኞች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ አውሮጳ ለመሻገር ነው የሚፈልጉት።ግን እንዴት አድርገው?ኮሮና በዓለማችን ከተዛመተ ወዲህ ወደ አውሮጳ የሚመጣው ስደተኛ መቀነሱን የአውሮጳ ድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት በምህጻሩ ፍሮንቴክስ ባለፈው ሚያዚያ አስታውቋል።ድርጅቱ እንደ ምሳሌ የጠቀሰው ከጥር እስከ ግንቦት  በሜዴትራንያን ባህር አድርገው ከሞሮኮ ወደ ስፓኝ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ነው።በዚህ ጊዜ ውስጥ ስፓኝ የገቡት 3812 ስደተኞች ናቸው።ይህም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ስፓኝ ከገባው ስደተኛ ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያንሳል።ምንም እንኳን በባሜዴትራንያን ባህር አድርገወ አሁን ወደ አውሮጳ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም በአፍሪቃ የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተላቸው ተጽእኖዎች ምክንያት ወደ አውሮጳ ለመሰደድ የሚፈልጉት ቁጥር ይጨምራል የሚል ግምት አለ።

የስደተኞች ጉዳይ ኮሮና ከምምጣቱም በፊት በአውሮጳ አነጋጋሪና አጨቃጫቂ ሆኖ እስካሁን የዘለቀ ጉዳይ ነው።አለመግባባቶች የሚያመዝኑበት ይህ ጉዳይ በቅርብ ዓመታት የህብረቱን ህልውና እስከመፈታተንም ደርሶ ነበር።የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ወደ ክፍለ ዓለሙ የሚመጡ ተገን ጠያቂዎችን የሚያስተናግዱበት ግልጽ ደንቦች እና መመሪያዎች አሏቸው። በጎርጎሮሳዊው 2013 የጸደቀው የደብሊኑ ስምምነት  በጄንቫ ስምምነት መሠረት ዓለም አቀፍ ጥበቃን የሚጠይቅ የተገን  ማመልከቻን የትኛው የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገር መመርመር እንደሚችል የተወሰነበት ነው።በስምምነቱ መሠረት የአንድ ተገን ጠያቂ ማመልከቻ መጀመሪያ በረገጠው የአውሮጳ ሃገር ነው የሚታየው።በደብሊኑ ስምምነት ህብረቱ ሕገ ወጥ የሚላቸው ስደተኞች አሻራ በአውሮጳ

አቀፍ ደረጃ ይከማቻል። ሆኖም ከ2015 ዓም በኋላ በአውሮጳ የተከሰተው የስደተኞች ቀውስ 
የህብረት ደቡባዊ ድንበር በሆኑት ሃገራት ላይ ያሳደረው ተጽእኖ አባል ሃገራትን እኩል የሚያሳትፍ የጋራ የተሻለ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ የማውጣት አስፈላጊነትን አጉልቶ ጥረቶች ቢደረጉም ሃሳቡ ሳይሳካ ቀርቷል።የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ሂደቱን እንዲህ ያስታውሳል።

አባል ሃገራት ወደ ደቡባዊ አውሮጳ የጎረፉትን በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንዲከፋፈሉ ሲጠየቁ ፈቃደኛ የሆኑት የተወሰኑት ብቻ ነበሩ።በተለይ የምሥራቅ አውሮጳዎቹ ሃገራት ፖላንድ ሃንጋሪ ቼክ ሪፐብሊክ እና ስሎቫክያ ስደተኛ አንወስድም በሚለው እምቢተኛ አቋማቸው እስካሁንም እንደጸኑ ነው።ሆኖም ከ2015 ዓም በኋላ በየጌዜው ሲነሳ ሲጣል የቆየው የስደተኞች ጉዳይ

በአሁኑ የጀርመን የፕሬዝዳንትነት ሃላፊነት ፍጻሜ ሊያገኝ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።የዚህ ምክንያት ደግሞ ገበያው እንደሚለው ጀርመን በስደተኞች ጉዳይ ያዳበረችው ልምድ፣ያላት አቅምና ኃይል ነው ።

በዙር የሚደርሰው የአውሮጳ ህብረት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጀርመን እንደምትለው የእስካሁኑ የአውሮጳ ህብረት የተገን አሰጣጥ ደንብ ከአሁን ወዲያ የማይሰራና ሊጠገንም የማይችል ነው።በዚህ መነሻነትም በአስቸኳይ የተሻሻለ የጋራ የስደት ፖሊሲ የሚወጣበት አዲስ ሙከራ እንደምታደርግ ነው ያሳወቀችው።ታዲያ እስካሁን  ስደተኞችን አንወስድም የሚሉት የምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት ግትር አቋምና  የጀርመን እቅድ እንዴት ይታረቅ ይሆን? ገበያው


የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ተገን ሊሰጣቸው የሚገባ ስደተኞች የሚለዩበት የተገን ጠያቂዎች ማቆያ ማዕከላት በህብረቱ ድንበሮች ላይ እንዲሰሩ ይፈልጋሉ።በነዚህ ማዕከላትም የስደተኞቹ ጉዳይ እንዲታይ ፣ተቀባይነት ያገኙት በየሀገሮች ሲከፋፈሉ ጥያቄአቸው ውድቅ የተደረገው ደግሞ ወደ ሃገራቸው የሚመለሱበት መንገድ እንዲፈለግ ሃሳብ አቅርበዋል።በዜሆፈር እምነት ይህ ዓይነቱ አሰራር ወደ አውሮጳ የሚገቡትን ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ለመቀነስ ይረዳል።የስደተኞች መብት ተከራካሪዎች የዜሆፈርን ሃሳብ የተገን ጠያቂዎችን መብት የሚጋፋ የአውሮጳ ህብረትንም መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የሚፃረር ሲሉ ተቃውመዋል።የተገን ጠያቂዎች ማመልከቻዎች የህብረቱ ድንበር ላይ በሚደረግ ምርመራ ሳይሆን የጠያቂው መብት ተከብሮ ሊስተናገድ ነው የሚገባው ሲሉም እየተከራከሩ ነው። 
ጀርመን በወቅቱ የአውሮጳ ህብረት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣንዋ አሳካለሁ ብላ ያቀደችው የህብረቱ የጋራ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ ምናልባትም የፊታችን መስከረም ለህብረቱ አባል ሃገራት ሊቀርብ እንደሚችል የህብረቱ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ኢልቫ ጆአንሰን አስታውቀዋል። በምክር ሃሳቡ ላይ የህብረቱ አባል ሃገራት እንዲስማሙበት ማድረጉ ለጆአንሰን ወሳኝ እና ፈታኝ ተግባር መሆኑ አይቀሬ ነው። 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች