ጀርመንና የሶሪያ ስደተኞች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመንና የሶሪያ ስደተኞች

ጀርመን ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት በግንባር ቀደምትነት በዚህ ዓመት 5 ሺህ የሶሪያ ስደተኞችን ለመውሰድ ቃል ገብታለች ። በጀርመን ፌደራል መንግሥት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ኦለ ሽሮደር እንደተናገሩት ጀርመን ከለላ የምትሰጠው ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሶሪያውያን ብቻ ነው ።

default

የሶርያ ስደተኞች በቱርክ

የተባበሩት መንግሥትት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ UNHCR እንዳስታወቀው በሶሪያው የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከሃገራቸው የሸሹ ሶሪያውያን ቁጥር ወደ 2 ሚሊዮን ይጠጋል ። ከነዚህም አብዛኛዎቹ በጎረቤት ሃገራት ነው የሚገኙት ። ከሶሪያ ስደተኞች አብዛኛዎቹ ሶሪያን በስተሰሜን በምታዋስናት በቱርክ ነው የተጠለሉት ። UNHCR እንደሚለው አሁን ቱርክ የሚገኙት የሶሪያ ስደተኞች ቁጥር ወደ 50 ሺህ ተጠግቷል ። ባለፈው ሳምንት ብቻ ቱርክ የገቡት የሶሪያ ስደተኞች ቁጥር 6 ሺህ ይደርሳል ። ይህ አሃዝ UNHCR የመዘገበው ሲሆን የማያውቃቸው ወይም ያልተመዘገቡ ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ይሆናል የሚል ግምት አለ ። አነዚህ ቱርክ የገቡት ስደተኞች ሲሆኑ በሌሎች ጎረቤት አገራት እንዲሁም በአውሮፓ ና በሌላውም የዓለም ክፍል የተበተኑት ሶሪያውያን ብዙ ናቸው ። አውሮፓ የሚገኙትን ብቻ እንኳን ብንመለከት የአውሮፓ ህብረት የስታትስቲክ ፅህፈት ቤት እንደሚለው ባለፉት 12 ወራት ብቻ 30 ሺህ ሶሪያውያን በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ተገን እንዲሰጣቸው ማመልከቻ አስገብተዋል ።

Syrische und irakische Flüchtlinge

የሶሪያና የኢራቅ ስደተኞች

ባለፈው ሐምሌ የጀርመን ፌደራል የስደትና የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ተገን ጠያቂዎችን ማመልከቻ መቀበሉን አስታውቋል ። እስከ ዛሬ የሶሪያ ስደተኞችን ለመቀበል ስታንገራግር የቆየችው ጀርመን ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት በግንባር ቀደምትነት በዚህ ዓመት 5 ሺህ የሶሪያ ስደተኞችን ለመውሰድ ቃል ገብታለች ። በጀርመን ፌደራል መንግሥት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ኦለ ሽሮደር እንደተናገሩት ጀርመን ከለላ የምትሰጠው ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሶሪያውያን ብቻ ነው ።
« ተገን የማግኘት መብት የሚሰጠው ከሚኖሩበት አገር በፖለቲካ ምክንያት ከሃገራቸው ለሚሸሹ እንጂ የተሻለ ኑሮ ተስፋ አድርገው ለሚሰደዱ አይደለም »
በሽሮደር አገላለጽ ጀርመን የምታስጠጋው ሶሪያ አቅራቢያ በሚገኙ የስደተኖች መጠለያዎች ውስጥ ለከፋ አደጋ የተጋለጡ ሶሪያውያንን ነው ። የስደተኞቹ ቤተሰቦችም ጀርመን የመምጣት ዕድል ይሰጣቸዋል ። የጀርመን መንግሥት 5 ሺህ ሶሪያውያንን ለማስጠጋት ቃል መግባቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን በመሳሰሉ ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋቾች ተወድሷል ። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የተገን አሰጣጥ መርህ አጥኚ ፍራንቼስካ ቪልማር የጀርመንን እርምጃ አድንቀዋል ።
« ጀርመን ግንባር ቀደም በመሆን 5 ሺህ ስደተኞች ለመቀበል ማቀዷ እኔ እንደሚመስለኝ ጥሩ ምልክት ነው ። »

Syrien Flüchtlinge Idlib

የሶሪያ ስደተኞች ቱርክ ድንበር ላይ


ምንም እንኳን ጀርመን እነዚህን ስደተኞች ለመቀበል ማቀዷ የሚወደስ እርምጃ ቢሆንም ከሶሪያ ስደተኞች ብዛት አንፃር ሲታይ ግን አባይን በጭልፋ የማለት ያህል ነው ። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ኦሌ ሽሮደር በዚህ አባባል ቢስማሙም ጀርመን ግን የአቅሟን እንጂ ከአቅሟ በላይ እንድታደርግ መጠበቅ የለበትም ይላሉ ። ከዚያ ይልቅ የመንግሥታቸውን እርምጃ ሌላውም በአርአያነት እንዲከተል ነው ያሳሰቡት ።
« በሶሪያ አጎራባች ሃገራት ውስጥ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ልንወስድ አንችልም ። ያን የምናደርግ ከሆነ ጀርመን በስደተኞች ትጥለቀለቃለች ሁኔታውም ፍትሃዊም አይሆንም ። ምክንያቱም ብዙዎቹ በርግጥ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሃገራቸው መመለስ ይፈልጋሉና ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የጀርመንን ፈለግ በመከተል ለስደተኞች ከለላ የመስጠት መርሃ ግብርን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀናል ። ኮሚስዮኑ ግን ይህን አላደረገም ። ጀርመን አሁን የወሰደችው እርምጃ ጥሩ ምሳሌ ነው ። »
5 ሺህ ሶሪያውያን ስደተኞችን ለመውሰድ ቃል የገባችው ጀርመን እስከ መጪው ዓመት ታህሳስ ድረስ ደግሞ ከመላው ዓለም የምትቀበለው ስደተኛ ቁጥር ከፍ እንደሚልም አስታውቃለች ። እንደገና ሽሮደር
« በኦለም ውስጥ የሚደርሰውን ስቃይ ስንመለከት እኛ የምንቀበላቸው ሰዎች ቁጥር ከባሊ ውሃ ጠብታን የመውሰድ ያህል ነው የሚቆጠረው ። በሌላ በኩል ደግሞ በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ዓም መጨረሻ ከዓለም ዙሪያ 100 ሺህ ስደተኞችን ለማስገባት አቅደናል »
ከሶሪያም ሆነ ከሰሜን አፍሪቃ ሃገራት የሚሰደዱ ሰዎች ከየጎረቤት ሃገራቱ አልፈው አውሮፓ ደጃፍ መፍሰስ ከጀመሩ ብዙ ጊዜያት ተቆጥረዋል ። የሜዴትራንያን ባህር አዋሳኝ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በስደተኞች መጨናነቅ ሲወሳ ዓመታት ተቆጥረዋል ። UNHCR እንደሚለው ማልታ ቆጵሮስ ኢጣልያ ግሪክ ሃንጋሪና ቡልጋሪያ ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ለመግባት ለሚፈልጉ የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪቃ ስደተኞች በራቸውን አጥበዋል ፤ ካስገቧቸውም በአግባቡ አያስተናግዷቸውም ።

Ole Schröder Staatssekretär des Inneren

ኦለ ሽሮደር

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችም የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራትን በአጠቃላይ ስደተኞች እንዳይገቡ በራቸውን በማጠርና ለስደተኞች ከለላ መስጠትን የተመለከቱ ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችን ባለማክበር በተደጋጋሚ ይወቅሳሉ ። ከተወቃሾቹ አንዷ ግሪክ ናት ። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰደተኞች ጉዳይ አጥኚ ቪልማር ግሪክ ከቱርክ ጋር የሚያዋስናት ድንበር እንዳይታለፍ አድርጋ በማጠሯ ስደተኞች ግሪክ ለመድረስ አደገኛውንና ህገ ወጡን የባህር ላይ ጉዞ ከመጠቀም ውጭ ሌላ አማራጭ ማጣታቸውን ይናገራሉ ። በዚህ የተነሳም ብዙ ስደተኞች የባህር ሲሳይ ሆነው ቀርተዋል ። ግሪክን የመሳሰሉት ሃገራት ስደተኞችን ላለማስገባታቸውና በአግባቡ ላለመያዛቸው ምክንያት የሚያደርጉት ውሳጣዊ ችግሮቻቸውን ነው ። ሆኖም ይህ አጥጋቢ ምክንያት አይደለም ይላሉ ቪልማር ። ግሪክ የኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መሆኗ ይታወቃል ያሉት ቪልማር ይህ ችግር ስላለ ብቻ ስደተኞችን ሰብዓዊነት በጎደለው ባህርይ ማስተናገዷ ተቀባይነት አይኖረውም ። በቪልማር አስተያየት በስደተኖች ብዛት የሚማረሩት እንደ ግሪክ አቅመ ደካማ የሆኑት አገሮች ብቻ አይደሉም አቅሙ ያላቸው እንደ ጀርመን ያሉ ሃገራትም ጭምር እንጂ ።
« ልንቆምላቸው የሚገባ ከለላ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ሰዎች አሉ ። ጉዳዩ አይተን እንዳለ ልናልፈው አንችልም ። ሁላችንም በአንድ ላይ የሚቻለንን ሁሉ ማድረግ ይገባናል ። የበለጠ የኤኮኖሚ ኃይል እያላቸው አሁን ጀርመን እንደምታደርገው በተገን ጠያቂዎች ቁጥር የሚማረሩም አሉ ።»
ቪልማር ጀርመን በሰብዓዊነት ሶሪያውያን ስደተኞችን ለማስጠጋት መወሰኗ እስየው የሚያሰኝ ቢሆንም ይህ ብቻውን በቂ አለመሆኑ ግልፅ ነው ይላሉ ። በርሳቸው አስተያየት ጀርመን ስደተኞቹን ለመቀበል አቀደች እንጂ ስደተኞቹን መውሰድ አልጀመረችም ። የዚህም ዋነኛው ምክንያት ወደ ጀርመን የሚመጡት ሶሪያውያን ስደተኞች በምን ዓይነት መንገድ እንደሚመረጡ ገና ውሳኔ አለማግኘቱ ነው ። እናም ስደተኞቹ አንገብጋቢ ሁኔታ ላይ እንደመገኘታቸው እዚያ ሊከናወን የሚገባው ሂደት ሊፋጠን ይገባል የሚል እምነት አላቸው
የጀርመን መንግሥት በበኩሉ የስደተኞችን ችግር ለመፍታት እያንዳንዱ አባል ሃገር ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሬ አስተላልፏል ። ኦለ ሽሮደር
«ሰብዓዊ መብት በገንዘብ የሚለካ አይደለም ። ሰብዓዊ መብት ሁሉንም የሚያጠቃልል በተሟላ መልኩ መታየት ያለበት ነው እናም እያንዳንዱ አባል ሃገር የሰብዓዊ መብት ይጠበቅ ዘንድ ድርሻውን መወጣት አለበት ሸክሙን መሸከም አለበት ።

Franziska Vilmar Expertin für Asylpolitik bei Amnesty International

ፍራንቼስካ ቪልማር


በአምነስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ቪልማር አስተያየት ዘላቂ መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው መሃል አውሮፓ በሚገኙት በህብረቱ አባል ሃገራት ትብብር ነው ። ከህብረቱ አባል ሃገራት በርካታ ስደተኞችን የምትቀበለው ማልታ ናት ። መሃል አውሮፓ የሚገኙት እንደ ጀርመን የመሳሰሉ ሃገራት በቪልማር አስተያየት ከሃላፊነታቸው እየሸሹ ነው ። ለዚህ ያመቻቸውም በአውሮፓ ህብረት ደንብ መሰረት የአንድን ስደተኛ ጉዳይ መከታተል ያለበት መጀመሪያ የገባበት የአውሮፓ ህብረት አባል ነው የሚለው የህብረቱ መመሪያ ደንብ ነው ።
ይሁንና ኦሊ ሽሮደር ህብረቱ በተለይም መሃል አውሮፓ የሚገኙ አገሮች ችግሩን አይጋሩም ሃላፊነት ይሸሻሉ በስደተኛ የተጨናነቁ አባል ሃገራትንም አይረዱም በሚል የቀረበባቸውን ወቀሳ አይቀበሉም ። ማልታን እንደ ምሳሌ ያነሱት ሽሮደር ሃገራቸው ም ሆነ የአውሮፓ ህብረት ሃገሪቱ ችግሩን ለብቻዋ ትወጣው ብለው እንዳልተዋት ነው የተናገሩት ።
« አዎ ማልታ እጎአ ከ 2007 ዓም አንስቶ 85 ሚሊዮን ዩሮ ተቀብላለች ። አዲሱ የስደተኖች ድጋፍ ሰጪ ቢሮ ፅህፈት ቤት የሚገኘውም ማልታ ነው ። ለዚህች ሃገር ድጋፍ አትሰጡም ተብለን መወቀስ አንችልም »
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ቪልማር ግን ይህ በራሱ በቂ አይደለም ይላሉ
« ገንዘብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይዛወር በሚል ቢሮክራሲ ከማብዛት ይልቅ ሰዎቹ ባሉበት ቦታ ያለውን አሳሳቢ ችግር ለማስወገድ ድጋፍ ከመስጠት ሌላ የተሻለ ነገር የለም »
እስካሁን በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ተገን ከጠየቁ ሶሪያውያን አብዛኛዎቹ ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ ከለላ ተሰጥቷቸዋል ። የ11 በመቶው ማመልከቻ ብቻ ነው ውድቅ የሆነው ። በዚህ ዓመት በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ተገን በመጠየቅ ሶሪያውያን ስደተኖች 2ተኛውን ደረጃ ይይዛሉ ። ከሶሪያውያን የቀደመውን ቦታ የሚይዙት ከሩስያ ፌደሬሽን የሚመጡ ስደተኞች ናቸው ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic