ጀርመንና የልማት ዕርዳታ ፖሊሲዋ | ኤኮኖሚ | DW | 08.12.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ጀርመንና የልማት ዕርዳታ ፖሊሲዋ

የበለጸጉ መንግሥታት አዳጊ ለሚባሉት ሃገራት የሚሰጡት ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታ ፍቱንነት ባለፉት ዓመታት ብዙ ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ነው።

default

አሁንም ከሚሊያርድ የሚበልጥ የዓለም ሕዝብ በተለይም በአፍሪቃ በከፋ ድህነትና በረሃብ ይሰቃያል። እስካሁን ሲፈስ የቆየው የልማት ዕርዳታ ከሕዝብ ይልቅ ገዢዎችን ጠቀመ እንጂ ለማሕበራዊ ዕድገት አልበጀም፤ በዚሁ የተነሣም አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ዛሬ አፍሪቃውያን ታዛቢዎች ሳይቀሩ በየጊዜው ያስገነዝባሉ። በዚህ ሊገባደድ ሶሥት ሣምንታት በቀሩት 2010 ዓ.ም. ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ልማት የመሪዎች ጉባዔ ላይም ዓቢይ መነጋገሪያ ርዕስ ነበር። የልማት ዕርዳታው ፖሊሲ ችግሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ፍቱን ሊሆን ይችላል?

ድህነትን በግማሽ መቀነስን የሚጠቀልለውን የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊያከትም የቀሩት አምሥት ዓመታት ብቻ ናቸው። ባለፈው መስከረም ተካሂዶ የነበረው የመሪዎች ጉባዔ ጉልህ እንዳደረገውም ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በግቦቹ አቅጣጫ የተደረገው ዕርምጃ ብዙም የሚያመረቃ አልነበረም። አብዛኞቹ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት አሁንም ከአጠቃላይ ምርታቸው 0,7 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ለማዋል ገና ጥንት የገቡትን ቃል አሟልተው አይገኙም።

በሌላ በኩል የልማት ዕርዳታን ወይም የልማት ተራድኦውን ፍቱን በማድረጉ ረገድ የጀርመን መንግሥት ወደፊት ፖሊሲውን በትብብር ውጤት ላይ ይበልጥ ጥገኛ ለማድረግ ነው የሚፈልገው። የአገሪቱ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል ባለፈው መስከረም ወር በኒውዮርኩ የሚሌኒየም ልማት ግቦች ግምገማ የመሪዎች ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት ይሄው መጠናከሩ የተፋጠነ የዕድገት ዕርምጃ ለማድረግ የሚበጅ ነው።

“የበለጠና የተፋጠነ ዕርምጃን ለማስፈን ምን ማድረግ ይኖርብናል? የዚህ መልሱ ግልጽ ይመስለኛል። መፍትሄው የልማት ፖሊሲያችንን መርህ ፍቱንነት ይበልጥ ማጠናከሩ ነው። ይበልጥ በውጤት ላይ ማተኮር ይኖርብናል። በኔ አመለካከት ይህን መሰሉ በውጤት ላይ የተመሠረተ ዕርዳታ ደግሞ ተሥፋን የሚያዳብር ነው የሚሆነው”

አንጌላ ሜርክል በሚሌኒየሙ ጉባዔ ላይ ንግግራቸውን ባሰሙበት ወቅት የብዙዎችን ትኩረት ነበር የሳቡት። ለዚሁም አንዱ ምክንያት ጀርመን በዶላር ሲተመን በዓለም ላይ አራተኛዋ ታላቅ ለጋሽ አገር መሆኗና ሌላው ምክንያት ደግሞ የጀርመን የልማት ዕርዳታ በብዙ የዓለም አካባቢዎች በአርአያነት መታየቱ ነው። ለምን ቢባል በጀርመን የልማት ፖሊሲ ላይ ለምሳሌ በዩ.ኤስ.አሜሪካ እንደሚታወቀው የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊ ጥቅም ስሌት ሚና ትልቅ አይደለም።

እናም ቻንስለር አንጌላ ሜርክል የግብር ከፋዩን ሕዝብ ገንዘብ ለልማት ትብብር በሚያፈሱበት ጊዜ ተገቢውን ውጤትም ለማየት መሻታቸው ብዙዎችን መማረኩ የሚጠበቅ ነው። በውጤት ላይ የተመሰረተ የልማት ዕርዳታ የሚለውን የወደፊት ጽንሰ-ሃሣብ ከመንግሥት ነጻ የሆኑት የጀርመን የልማት ፖሊሲ ማሕበር አመራር አካል ሊቀ-መንበር ኡልሪሽ ፖስትም መልካም ነገር አድርገው ነው የሚመለከቱት።

“በውጤት ላይ ማተኮሩ በነገራችን ላይ በመንግሥቱ ወገንም ሆነ ከመንግሥት ነጻ በሆኑት ድርጅቶች ተግባር ላይም የራሱ ሚና ይኖረዋል። እኛም እንደ ግል ድርጅቶች በመጨረሻ መለካት ያለብን በሥራችን ውጤት ነው”

ኡልሪሽ ፖስት አያይዘው እንደሚሉት ይህም ከለጋሹ ወገን የሚቀርብ ተገቢ ጥያቄ ነው። ይሁንና በጉዳዩ ከተጋነነ ስጋት ላይ መውደቅም አያስፈልግም።

“በጉዳዩ ሳናመነታ በውጤት ላይ ባተኮረው የአሠራር ዘይቤ ላይ መጽናት አለብን። በውጤት ላይ መመስረት ሲባል በሌላ በኩል አሃዞችን በመከመርና ቢሮክራሲን በማስፋት የሚከተል አደጋን መጋፈጥም ማለት ነው”

ኡልሪሽ ፖስት እንደሚያስገነዝቡት እርግጥ ብዙውን ነገር በተጨባጭ አሃዝ እንዲህ ብሎ መለካቱ ቀላል ነገር አይሆንም። ለምሳሌ በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ ዴሞክራሲን ለማስፋፋት የሚሰጥ ዕርዳታን መጥቀስ ይቻላል። በጎ አስተዳደርንም እንዲሁ በግድ በአሃዝ መለካት የማይቻል ነገር ነው። የሆነው ሆኖ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው የልማት ዕርዳታ ገደብ የለሽ ሆኖ እንደማይቀጥል ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ባይ ናቸው።

“የልማት ዕርዳታ የጊዜ ገደብ ሳይኖረው የሚቀጥል ነገር ሊሆን አይችልም። ቁምነገሩ ውሱን የዕርዳታ ገንዘብን በተቻለ መጠን ጥቅም እንዲሰጥ አድርጎ በስራ ላይ ማዋል ነው። ይህ እርግጥ ያለ በጎ አስተዳደር የተረጂውን አገር የኤኮኖሚ ብቃት የሚያዳብር ሆኖ ሊሰራ የሚችል አይሆንም”

በጎ አስተዳደር እንግዲህ ጀርመን የልማት ዕርዳታ ለመስጠት ከምታቀርባቸው ቁልፍ ግዴታዎች አንዱ መሆኑ ነው። ግማሹ የአገሪቱ የልማት ዕርዳታ በጀት የሚወጣውም ለመንግሥታት የሁለት ወገን ተራድኦ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ለተረጂዎቹ ሃገራት መንግሥታት የሚቀርበው ቀጥተኛ የበጀት ዕርዳታም ከዚህ የሚጠቃለል ነው። ባለፉት ጊዜያት ታዲያ ይሄው የበጀት ዕርዳታ ከሁሉም በላይ በሙስና የተበከሉ ገዢዎችን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ነው የበጀው በሚል ብዙ መተቸቱ አልቀረም። ወደፊት እንግዲህ ይህ እንዳይሆን ገንዘብ ከመፍሰሱ በፊት የመንግሥታቱ ሁኔታ በውል ይጤናል ማለት ነው።

እርግጥ ይህ በእድ በኩል አድናቆት የሚሰጠው ነጥብ ሲሆን በሌላ ግን አደገኛ ሊሆን እንደሚችልም ነው የሚነገረው። ለምሳሌ ስርዓታቸው በተናጋ፤ መንግሥት የተወሰኑ ግዛቶቹን ቁጥጥር ባጣባቸው አገሮች ሕዝብ በጣም የሚያስፈለውን ዕርዳታ ሊያገኝ አይችልም ማለት ነው። ይህ ከሆነ ኡልሪሽ ፖስት እንደሚሉት በነዚህ ዓይነቶቹ ሃገራት የረባ ሚና ሊኖራቸው የሚችሉት ደግሞ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ናቸው።

“ለጋሽ መንግሥታት አገናኝ ማግኘት በሚይችሉባቸው በነዚህ ሃገራት እኛ ብዙ የዕርዳታ መንገዶች አሉን። ግን እንዲህ ሲባል ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች የመንግሥታትን ሚና ሊይዙ ይችላሉ ማለት አይደለም። ይህ ከአቅማችን በላይ ነው፤ የተነሣንበት ተግባራችንም አይደለም። ሆኖም ግን ለምሳሌ ቀውስን በመቋቋም፣ በጤና ጥበቃ መስክና በትምሕርት ዘርፍ ሰፊ አስተዋጽኦ ልናደርግ እንችላለን”

በሌላ አነጋገር የበጎ አስተዳደር መጓደል ያስከተላቸውን ችግሮች በተቻለ መጠን ለማለዘብ ድርሻ ይኖራቸዋል ማለት ነው። እንደ ጀርመኗ ቻንስለር እንደ ወሮ/አንጌላ ሜርክል ከሆነ ደግሞ ከሚሌኒየሙ ግቦች እንዲደረስ ከተፈለገ በተረጂዎቹ አገሮች ልማትን ማራመዱ የራሳቸው መንግሥታት ተግባርና ሃላፊነት ሊሆን ይገባል። ታዳጊዎቹ አገሮች የራሳቸው መሠረታዊ የኤኮኖሚ ዕድገት ካልኖራቸው ከድህነትና ከረሃብ የሚያወጣው መንገድ ዳገታማ ሆኖ ነው የሚቀጥለው።

“ቀጣይነት ያለው የኤኮኖሚ ዕድገት ሳይኖር ከልማት ግቦች ላይ ሊደረስም ሆነ እስካሁን የተገኘውን ጠብቆ ለማቆየት አይቻልም። በመሆኑም ጀርመን በልማት ትብብሩ ረገድ የታዳጊዎቹን የራስ ጥረት የመደገፍ ሃላፊነት የሚሰማት አገር ናት። ይህ አመለካከት ሰፊ ሆኖ በተዘረጋ ሽርክና ላይም ጽናት አለው”

ድሀነትን መታገሉና የልማቱ እንቅስቃሴ እርግጥ በገጠርም መካሄድ ይኖርበታል። ለግንዛቤ ያህል በዓለም ላይ ከአራት ሶሥቱ በከፋ ድሕነት ላይ የሚገኝ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር አካባቢዎች ነው። እና ገጠሩ ሳይለማ እስከ 2015 በዓለምአቀፍ ደረጃ ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ የተያዘው ግብም የማይደረስበት ነገር እንደሆነ ነው የሚቀጥለው። ግን የቀድሞዋ የሚሌኒየም ዘመቻ ሃላፊ ኤቨሊን ሄርፍከንስ እንደሚሉት እክሉ ከበለጸጉት አኳያ በታዳጊዎቹ ላይ ከተደቀነው የንግድ ችግር ጋርም የተሳሰረ ነው።

“የዓለም ባንክ ሳይቀር በእርሻ ልማት ላይ መዋዕለ-ነዋይ ማድረጉ የሃብታም አገሮች የንግድ ፖሊሲ ከንቱ የሚያደርገው በመሆኑ ትርጉም እንደማይሰጥ ሲናገር አሠርተ-ዓመታት አልፈዋል። በእርሻ ልማት ላይ መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ ከፈለግን በቅድሚያ ለተዳጊው ዓለም ገበዮቻችንን ልንከፍትና በአንጻሩም የነርሱን ገበዮች በተደጎሙ ምርቶች ከማውደም ልንቆጠብ የሚገባ ነው”

የመስከረሙ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ጉባዔ ዘገባ እንዳመለከተው የወቅቱ ሃቅ እንደሚከተለው ነው። ሃብታም አገሮች ነዳጅ ዘይትና ማዕድናትን የመሳሰሉትን ጥሬ ሃብቶች በደስታ ወደ አገራቸው ያስገባሉ። በአንጻሩ የእርሻ ምርቶችና ከነዚሁ ተሰርተው ያለቁ ውጤቶችን ግን በከፍተኛ ቀረጥ እንዳይገቡ ያግዳሉ፤ ወይም በተደጎሙ ብሄራዊና የአካባቢ ምርቶች ለፉክክር እንዳይበቁ ያደርጋሉ። ዛሬ ብዙ የምጣኔ-ሐብት ጠበብት እንደሚናገሩት የዚህ ዓይነቱ የአሠራር ዘይቤ መቀየር የልማት ዕርዳታን እስካሁን ባልታየ መጠን ፍቱን ሊያደርግ በቻለ ነበር። ይሁን እንጂ ሃቁ በዚህ ረገድ ፍትሃዊ ንግድን ለማስፈን ከዘጠን ዓመታት በፊት የተጀመረው የዓለም ንግድ የዶሃ ድርድር ዙር እስከዛሬ እንደተንጠለጠለ ያላንዳች ስኬት መቅረቱ ነው።

ይብሰን ሐለ

መስፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ